Connect with us

ሰው ሳይሆኑ ፖሊቲከኛ!

ሰው ሳይሆኑ ፖሊቲከኛ!
Photo: ESAT

ፓለቲካ

ሰው ሳይሆኑ ፖሊቲከኛ!

ሰው ሳይሆኑ ፖሊቲከኛ!
ነጻ ሳይወጡ ነጻ አውጪ!
መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2012

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ሰው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረ ነው፤ እነዚህ ባሕርያት የሚከተሉት ናቸው፤ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ፡ መሬት — ነፋስ — እሳት — ውሀ ናቸው፤ የሰው ነፍስ ሦስት ባሕርያት አሏት፤ ነባቢት፤ ለባዊትና ሕያው ይባላሉ፤ ነባቢት ማለት የምትናገር ነው፤ ለባዊት ማለት የምታስብ ነው፤ ሕየው ማለት የማትሞት ማለት ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ለየብቻው የባሕርያተ ነፍስ ባለቤት ነው፤ ሳርትር የሚባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ ‹‹ሰው ነጻነት ነው፤›› ይላል፤ ማናቸውም የእንስሳ መንጋ የነጻነት መልክ የለውም፤ አንድ ሰው ጅራፍ ይዞ እንደፈለገ የሚነዳው የእንስሳ መንጋ ሰው ሊባል አይቻልም፤ ሰው አእምሮ ያለውና የሚያስብ፣ አንደበት ያለውና ሀሳቡንና ስሜቱን በንግግር የሚገልጽ፣ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን የሚያመዛዝንና ለይቶ የሚያውቅ ነው፡፡

ከስንት ዘመናት በፊት ዳዊት ‹‹ሰው ክቡር መሆኑን ስላላወቀ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት ሆነ፤›› ይላል፤ ኃላፊነት እንደማይሰማው መንጋ  ከላይ የተገለጹት ባሕርያት ከሰው ልጅ እድገትና መሻሻል ጋር የተያያዙ ናቸው፤ ልጅ በአካሉ እያደገ ዳዴ እያለ በአራት እግሩ ከመሄድ በሁለት አግር ወደመሄድ ይሸጋገራል፤ በእጆቹም በዙ ነገሮችን ይሠራል፤ በአቅሙ እየጠነከረ ይሄዳል፤

በትምህርት ይጎለብታል፤ በአስተሳሰቡ ትክክለኛና በአነጋገሩ የታረመና የሰከነ ይሆናል፤ ማኅበረሰቡ ለእድገቱ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ተገንዝቦ እሱም በበኩሉ ለማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልና ኃላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ ይሆናል፤ ሕጻናት፣ የአእምሮ ሕሙማንና የጃጁ ሰዎች ኃላፊነት አይሰማቸውም፣ እዚህ ውስጥ የሥልጣን ጥም ያሰከራቸውንም ልንጨምር የምንችል ይመስለኛል፤ ይህንን መስፈርት የሚያሟሉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ ይቀርባሉ፤ ይጸድቃሉ፤ ወይም ይኮነናሉ፤ የማኅበረ ሰቡን ሕግ ከጣሱም በሕጋዊ ፍርድ ቤት ዋጋቸውን ያገኛሉ፤ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር በላይ፣ ከማኅበረ ሰቡ በላይ፣ ከሕጋዊ ሥርዓት በላይ፣ ከይሉኝታ በላይ፣ ከሕጋዊ ሰላም በላይ፣ ከፍቅርና ከስምምነት በላይ፣ ከትብብር በላይ አድርገው እጃቸው ላይ በገባላቸው ዱላ እየተጠቀሙ አለኛ ሰው የለም የሚሉ ከማኅበረሰባዊ ሕግ ውጭ በሕገ አራዊት ሰውን ለመግዛት የሚፈልጉ ናቸው፡፡

ጎሣ፣ ቋንቋ፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ሕጋዊ ሥርዓት የሰዎችን ግንኙነት ለማቃለልና ለማፋጠን የሚበጁ እንጂ እንቅፋት እንዲሆኑ ሰውም ተፈጥሮም አላቀደም፤ ዛሬ በምድረ ኢትዮጵያ እንደአሸን የፈሉት የጎሣና የመንደር ድርጅቶች ራሳቸውን በተለያዩ የሹመት ወንበሮች ላይ አስቀምጠው እንደነሱ ያልበሰሉና የተወናበዱ ሰዎችን ሰብስበው የሚያስጮሁ ናቸው፡፡

ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ከማኅበረሰባዊ አጠቃላይ እድገት ውጭ የተለየ ትርጉም የለውም፤ ነጻነት የሥልጣን ጥመኞች የፖሊቲካ ሰንሰለት አይደለም፤ ዴሞክራሲ ሁሉም እንደልቡ የሚፈነጭበት ስድነት አይደለም፤ ቋንቋ፣ ጎሣ፣ ሃይማኖት፣ ከሰዎች በላይና ከሰዎች ውጭ ያሉ ፖሊቲከኛ ነን ባዮች እያጦዙ ሕዝብን የሚያተራምሱባቸው መሣሪያዎች አይደሉም፤ የምናስብ ሰዎች ከሆንን ሰው የፈጠረውንና በተፈጥሮ ያገኘውን ለይተን ማወቅ ይበጀናል፤ ማኅበረሰቡን የመጨረሻ ዓላማ አድርገን ለጎሣ፣ ለቋንቋ፣ ለሃይማኖት ትክክለኛ ቦታቸውን ስንወስን፤ ጨለማውን ያበራልናል፤ ቋንቋ ለማኅበረ ሰቡ መሣሪያ ነው እንጂ ማኅበረሰቡ የቋንቋ መሣሪያ አይደለም፤ ሃይማኖት በመሠረቱ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት የሚደነግግ ሥርዓት ነው፤ ቋንቋንና ሃይማኖትን በአሜሪካ (ሰሜንም ደቡብም)፣ ሚኔሶታንም ጨምሮ! በእስያ፣ በአፍሪካ በተለይ በሰሜን አፍሪካ ጎሣንና ቋንቋን ታሪክ ዝብርቅርቃቸው እንዳወጣ ማስተዋል ከስሕተትና ከጥፋት ያድነን ነበር፡፡

ከሁሉም የሚያስደንቀው ተማርኩ የሚለውና የራሱን ማኅበረሰብና ወገኑን ከድቶ በባዕድ አገር የሙጢኝ ብሉ በጥገኝነት የሚኖረው ጥሎት ለሄደው አገር ባለቤት መስሎ ሲከራከር ነው፤ ከሱም የበለጠ የሚያስደንቀው ሰሚና ተከታይ ማግኘቱ የኋላ-ቀርነት ዋና መግለጫ ነው፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top