‹‹የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ በዝግ መመስከር የለባቸውም››
እነ እስክንድር ነጋ
ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ሁከትና ግጭት ምክንያት በማድረግ ወገን በወገን ላይ እንዲነሳና የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳ በማድረግ፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማቀድና በመዘጋጀት ወንጀሎች ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ እስክንድር ነጋ (አራት ሰዎች)፣ የዓቃቤ ሕግን ክስ በመቃወም ያቀረቡትን መቃወሚያ ፍርድ ቤት ውድቅ እንዲያደርግለት ዓቃቤ ሕግ በምላሹ ፍርድ ቤትን ጠየቀ፡፡
ዓቃቤ ሕግ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240(1)ን በመጥቀስ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾቹ 14 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲሞቱ ስለማድረጋቸው ባቀረበው ክስ ላይ፣ ተከሳሾቹ ሰዎቹን የገደሉበት ምክንያት፣ ሰዓት፣ ቦታ፣ ማን እንደገደላቸውና የእነሱ አስተዋጽኦ ምን እንደሆነ እንዲገለጽላቸው፣ መቃወሚያቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት ጉዳዮችና የሽብርተኝነት አንደኛ ወንጀል ችሎት አቅርበው ነበር፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ተከሳሾች ያቀረቡት መቃወሚያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240(1) ጽንሰ ሐሳብን በተረዳ መንገድ አይደለም፡፡ አንቀጹ ሦስት ዓይነት የወንጀል ተሳትፎዎችን ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ የቀረበው ክስ ወንጀሉን በማደራጀትና በመምራት፣ አንዱ ወገን በሌላኛው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ፣ ባነሳሱት ዓመፅ 14 ሰዎች እንዲገደሉ ስለማድረጋቸው እንጂ፣ በክሱም ላይ ተከሳሾች በቀጥታ ገድለዋል የሚል እንዳልሆነ በምላሹ አስረድቷል፡፡
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 240(4) ድንጋጌ መሠረት ክስ ባላቀረበበት ሁኔታ ክሱን የተቃወሙበት ሒደት ከሕጉ ዓላማና መንፈስ ውጪ መሆኑን በመጥቀስ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
እነ አቶ እስክንድር ሌላው ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ፣ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ ላይ ፌስቡክና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ስም ስለማጥፋታቸው መሆኑን በመጠቆም፣ ስማቸውንና አካውንታቸውን ጠቅሶ እንዲያቀርብ ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ተከሳሾቹ ለአባሎቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ድርጊቱን እንዲፈጽሙ (ስም የማጥፋት) አደረጉ እንጂ፣ ራሳቸው ሐሰተኛ የፌስቡክ አካውንት ተጠቅመው፣ ስም የማጥፋትና ጥላቻን የማስረፅ ሥራ ሠርተዋል የሚል ክስ አለማቅረቡን ገልጾ፣ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ተከሳሾች ስልጤ ሠፈር በመሄድ፣ አንዱ ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ ሲቀሰቅሱ እንደነበር በክሱ ላይ ከመጥቀስ ባለፈ፣ የትኛው ብሔር ከየትኛው ብሔር ላይ እንዲነሳ እንዳደረጉ አለመግጹን ጠቁመው፣ ግልጽ አድርጎ እንዲያቀርብ ላቀረቡትም መቃወሚያም ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በምላሹ እንደገለጸው፣ ተከሳሾች ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ (ስልጤ ሠፈር) ሄደው በሕገወጥ ግንባታ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦችን፣ ‹‹እንዲፈርስ ያደረገባችሁ ታከለ ኡማ ነው፡፡ እናንተን አስነስቶ ከሶማሌ የተፈናቀሉ ኦሮሚያዎችን ለማስፈር ነው፤›› በማለት ሌሎች ብሔሮች የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ እንዲነሱ ማድረጋቸው ግልጽ በመሆኑ፣ ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቁሞ ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
አቶ እስክንድር፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮልና ወ/ሮ ቀለብ ሥዩም ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ ክፍላተ ከተማ ያሉ አባላትን ጠርተው ተልዕኮ እንደሰጡ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ቢገልጽም፣ ቦታው የት እንደሆነ እንዳልገለጸ በመጠቆም ላቀረቡት ተቃውሞም፣ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በምላሹ እንዳብራራውም፣ ተከሳሾቹ ተልዕኮውን የሰጡት በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት መሆኑንና አራተኛ ተከሳሽ አስካለ ደምሌ ከተልዕኮ ተቀባዮቹ አንዷ መሆኗን አስረድቷል፡፡
አስካለ ደምሌ ተልዕኮ የሰጠቻቸው ወጣቶች ዱላ፣ ገጀራና ፌሮ ይዘው የወጡበት ቦታ ስላለመገለጹ ተከሳሾች በመቃወሚያቸው መግለጻቸውን በሚመለከትም፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አጠና ተራ፣ የጦር ኃይሎች ታክሲ መያዣ አካባቢ በሚገኝ ካፌ ውስጥ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በወቅቱ ረብሻ የተነሳውም ጦር ኃይሎች መንገድ ልኳንዳና አጠና ተራ መሆኑን ገልጾ፣ ዝርዝር ማብራሪያው በምስክሮች የሚብራራ መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ ገልጾ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌን በመተላለፍ፣ የቀድሞውን አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ግለሰቦችን ለማስገደል አሸባሪ ቡድን በማሠልጠን፣ ከአዲስ አበባ እስከ አማራ ክልል የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ሲሰናዱ እንደነበር ገልጾ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው ክስ ላይም መቃወሚያ አቅርበው ነበር፡፡
ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ በማቃጠል፣ የሰው ሕይወት በማጥፋት፣ ንብረት በማውደምና አገርን በማሸበር መንግሥትን አስገድደው በመጣል የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስና የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት የሚለው ክስ ‹‹ተመሳሳይ ወንጀሎች›› ስለሆኑ ተጠቃሎ እንዲቀርብላቸው መቃወሚያ አቅርበው ነበር፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ክሱ ይቀላቀል ቢባል እንኳን በአቶ እስክንድር ተመልምለው ሥልጠና የወሰዱትና ሽብር ለመፈጸም ተሰናድተው የነበሩት አሸናፊ አወቀ (ስድስተኛ ተከሳሽ) እና ፍትዊ ገብረ መድኅን (ሰባተኛ ተከሳሽ) ባልተሳተፉበት ሁኔታ እነ አቶ እስክንድር በተከሰሱበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240 (1) ተጠቅሶ እያለ ተመሳሳይ ነው መባሉ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡
እነ አቶ እስክንድር በተከሰሱበትና የ14 ሰዎች ሕይወት ባለፈበት የወንጀል ድርጊት ተጠያቂ ይሁኑ ማለት ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ሰዎች ባልፈጸሙት ወንጀል ኃላፊ የሚያደርግ ትልቁን የወንጀል መርህ የሚጥስ፣ ከሕግ፣ ከሕግ ፍልስፍናና ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚቃረን መሆኑን በመግለጽ መቃወሚያው ውድቅ እንዲደረግለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የቆጠራቸው 21 ምስክሮች፣ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 6(1ለ) ድንጋጌ መሠረት፣ 16 ምስክሮች ምስክርነታቸውን በዝግ ችሎትና አምስቱ ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ያቀረበውን ጥያቄ ተከሳሾቹ ተቃውመዋል፡፡
ተከሳሾቹ በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መቃወሚያ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ሕግም ሆነ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ኮንቬንሽኖች፣ ብሔር ከብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት ወይም በዘር ማጥፋት ወይም በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crime Against Humanity) በሚባሉት የሕግ ማዕቀፎች ሥር የሚታዩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ክሶችን በመመልከት ደግሞ ተሞክሮን በተግባር ከቀሰሙት አገሮች መካከል የምትመደብ መሆኗ ይታወቃል፡፡
የቀይ ሽብር ወንጀሎች በፈጸሙ የደርግ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የተቆጠሩ ምስክሮች በግልጽ ችሎት መስክረው፣ ማንነታቸውና ምሥላቸው በመገናኛ ብዙኃን እንዲተላለፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ በምስከሮቹ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃትም ሆነ ጉዳት እንዳልደረሰባቸውና ተከሳሾቹም ቅጣታቸውን ጨርሰው ሲፈቱ ከምስክሮቹ ጋር በሰላም እየኖሩ ከመሆኑ አንፃር፣ በምስክሮች ላይ የበቀል ዕርምጃ የመውሰድ ባህል አለመኖሩን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ እውነታ መረዳት የሚቻለው እነሱ በተከሰሱበት የሚቀርቡ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች፣ ከመጋረጃ ጀርባና በዝግ ችሎት እንዲሰሙ የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ በቅንነት የቀረበ ነው ቢባል እንኳን፣ በላቲን አሜሪካ በአደንዛዥ ዕፅ ክሶች ዙሪያ ያሉ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን እንደሚያሳይ አቶ እስክንድር ተናግሯል፡፡
ይኼ ደግሞ ከዓውዱ ውጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው በጀርመንና በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በፈጸሙ ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ክሶች ሙሉ ለሙሉ በግልጽ ችሎት የተካሄዱ መሆናቸውን ዓለም እንደሚያውቀውም በምሳሌነት ጠቅሰው፣ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በጀርመንም ሆነ በሩዋንዳ በምስክሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖና የደኅንነት ችግር የነበረ ቢሆንም፣ የተመሠረተው ክስ ፋይዳ የሚኖረው፣ በአንድ በኩል በጥፋተኞች ላይ አስተማሪ ቅጣት ለመበየንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሕዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጸም ማስጠንቀቂያ እንዲሆን አስፈላጊነቱ ታምኖበት፣ የሙግቱ ሒደት ሙሉ በሙሉ በግልጽ ችሎት እንዲታይ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ይኼ የሆነውም ከየትኛውም ወገን ጥርጣሬና የሴራ መላ ምት እንዳይኖር ማድረግ አማራጭ የሌለው ዕርምጃ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን እነሱን የከሰሳቸው ዓቃቤ ሕግ የመረጠው ከዚህ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በተቃራኒ መጓዝን መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ይኼ ደግሞ ብዙ ጥያቄ ያለበትን የኢትዮጵያን የፍትሕ ሥርዓት ይበልጥ የሚጎዳና ጥርጣሬ ላይ የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ሁኔታዎች አስገዳጅ ስለሆኑበት እንጂ፣ ሁሉም ነገር ሥውር ሆኖበት እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ በቅድመ ምርመራ ወቅት ምስክሮች በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ የተሰሙ ቢሆንም፣ አሁን ባቀረበባቸው ክስ ላይ የሚሰሙት ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንደሚሰሙ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ሲከፍት መናገሩን አስታውሰው፣ ቃሉን አጥፎ በዝግ ችሎትና በመጋረጃ ጀርባ እንዲታዩለት ጥያቄ ያነሳው፣ በቅድመ ምርመራ ወቅት በዝግ ችሎት ባቀረባቸው ምስክሮች ብቃት ላይ ካለው ሥጋት አኳያ መሆኑን እንደተረዱም ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ተከሳሾቹ ለቅድመ ምርመራ ተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ ባያቀርቡም፣ ፍርድ ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት ባቀረበላቸው የማጣሪያ ጥያቄ ላይ መመለስ አቅቷቸውና ተቸግረው ዓቃቤ ሕግም ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በቀረበባቸው ክስ ላይ ፍትሕን ባማከለ መንገድ እንዲሄድና ውጤቱም በሕዝብና በታሪክ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማስቻል፣ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት ለምስክሮች ጥበቃ የመስጠት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሆንም፣ በፍትሕ አሰጣጡ ላይ ተፅዕኖ አሳድረዋል ብሎ ሲያምን፣ ፍርድ ቤቱ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዳይወስድ አለመከልከሉን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የቀረበባቸው ክስ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የክርክሩ ሒደት ሙሉ በሙሉ በግልጽ ችሎት እንዲደረግና ለዓቃቤ ሕግም ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም ያለ ምንም ተፅዕኖ በነፃነት እንዲዘግቡ የተጣለባቸው ገደብ እንዲነሳም ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ አሸናፊ አወቀና ፍትዊ ገብረ መድኅን የተባሉ ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ የታዘዘውን ለምን እንዳልፈጸመ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ጌትነት በቀለ የተባለው ተከሳሽ የክስ መቃወሚያውን ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በጽሑፍ እንዲያቀርብና ዓቃቤ ሕግ ምላሹን ለጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያቀርብ በመንገር፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲያሰማ ባቀረበው መግለጫ ላይ ብይን ለመስጠት ለኅዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ (ታምሩ ጽጌ – ሪፖርተር)