የተዘጉ የማዕድን ኩባንያዎች ወደ ሥራ ሊመለሱ ነው
~ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚድሮክ ወርቅ ላይ የባለቤትነት ድርሻ ጠይቋል
በአገሪቱ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉ የማዕድን ኩባንያዎች ወደ ሥራ ሊመለሱ ነው፡፡
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማምጣት የሚታወቁት የሚድሮክ ወርቅ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻና የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ልማት ኮርፖሬሽን፣ የቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማውጫ ከአካባቢ ብክለት ጋር፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተፈጠረ ግጭት ምርት ካቆሙ ሁለት ዓመት አልፏቸዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በኩባንያዎቹ ላይ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ፈቃዳቸው እንዲታገድና ጉዳዩ በሳይንሳዊ ጥናት እንዲጣራ በወሰነው መሠረት፣ ኩባንያዎቹ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ምርት አቋርጠዋል፡፡
አዲሱ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የ2013 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም አስመልክቶ፣ በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ፣ የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻና ሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች ምርት ያቋረጡ ኩባንያዎች ችግሮች ተፈትተው፣ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአንዳንድ ቦታዎች ኩባንያዎች ምርት አቁመዋል፡፡ ወደ ሥራ የሚገቡበት አሠራር እንዘረጋለን፡፡ ከክልል ጋር መነጋገር ጀምረናል፡፡ የተዘጉ ኩባንያዎች ወደ ምርት ይገባሉ፤›› ያሉት ታከለ (ኢንጂነር)፣ የማዕድንና ነዳጅ ሀብት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም አንቀሳቃሽ ሞተር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የሚድሮክ ወርቅ ጉዳይ በካናዳ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በታወቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢና ጤና ባለሙያዎች፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ፣ የፌዴራል የምግብና መድኃኒት አስተዳዳርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች የተሳተፉበት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚመራ ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት ጥናት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እኔም ከመጣሁ በኋላ ክለሳውን ዓይተናል፡፡
በጥናቱ ላይ ክልሉና ሚድሮክ ወርቅ ልዩነት የላቸውም፡፡ የተጎዱ ሰዎች አሉ፡፡ የአካባቢ ጉዳዮችና የመፍትሔ ሐሳቦች ተጠንተው በወረቀት ሰፍረዋል፤›› ብለዋል፡፡
ሚድሮክ የለገደንቢ ወርቅ ማውጫ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ በጨረታ 172 ሚሊዮን ዶላር በ1987 ዓ.ም. እንደገዛው ይታወሳል፡፡ የለገደንቢ ወርቅ ማውጫ በመንግሥት እጅ በነበረበት ወቅት፣ ወርቁን ለማጣራት ይጠቀሙበት የነበረው ሜርኩሪ የተባለ አደገኛ ንጥረ ነገር እንደነበር አውስተው፣ የለገደንቢ የአካባቢ ብክለት ረዥም ታሪክ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
‹‹የሜርኩሪ ጉዳት በአንድ ጊዜ የሚታይ ሳይሆን ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ሚድሮክ ከመጣ በኋላ የሚጠቀመው ሳይናድ ነው፡፡ ክስተቱ የረዥም ጊዜ ድምር ውጤት ነው፡፡ ሚድሮክ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም እጅ አለበት፡፡ ኬሚካሎቹ ያስከተሉት ጉዳት ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡
ሜርኩሪ የሚጠቀሙ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳቱ የድምር ውጤት በመሆኑ የትኛው ኬሚካል የትኛውን የጤና ችግር ፈጠረ የሚለው የዘረመል ጥናት ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
የተጎዳውን አካባቢና ማኅበረሰብ መልሶ ማቋቋም ጉዳይ በፌዴራል መንግሥት፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በሚድሮክ ወርቅ መካከል የጋራ መግባባት እንደተደረሰ ታከለ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ ከጉጂ አካባቢ የመጡ አባ ገዳዎች ጋር ውይይት እንደተካሄደም ጠቁመዋል፡፡
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አዲስ ባዘጋጀው የማዕድንና ነዳጅ ፖሊሲና ሕግ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ክልሎችና ወረዳዎች የሮያሊቲ ክፍያ እንዲያገኙ ማዕድኑ በሚወጣበት አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሠራር እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ትልቁ ችግር የነበረው ከለውጡ በፊት ሲነሳ የነበረው የተጠቃሚነት ጥያቄ ነበር፡፡
ከአንድ አካባቢ በሚወጣው ማዕድን ተጠቃሚው ኩባንያውና በሕጋዊ አሠራር ቢሆንም፣ ክፍያ የሚሰበስበው የፌዴራል መንግሥት ነበር፡፡ አሁን እየዘረጋን ያለነው አሠራር ክልሎች፣ ወረዳዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሮያሊቲ ክፍያ ብቻ ሳይሆን በሚድሮክ ወርቅ ላይ የባለቤትነት ድርሻ እንደሚገባው ጥያቄ ማቅረቡን፣ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ ኩባንያው፣ ክልሉና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በባለቤትነት ድርሻ ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛም ተገቢ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን፡፡
የኢንዱስትሪ ሰላምና የአካባቢ ደኅንነት ለማስጠበቅ ጠቃሚ ስለሆነ፣ ያለውን የፀጥታና የመሠረተ ልማት ችግር ክልሉና ኩባንያው እየተነጋገሩ ይፈታሉ፤›› ብለዋል፡፡
በፀጥታው ዙሪያ የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች የፀጥታ ኃይል ጋር ተናበው የሚሠሩበት አሠራር እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ለገደንቢና ቀንጢቻ ብቻ ሳይሆን በቤኒሻንጉል ጉምዝና በሌሎች ቦታዎች የተዘጉ ኩባንያዎች ወደ ሥራ በቅርቡ ይገባሉ፡፡ አዳዲስ ኩባንያዎችም በወርቅ፣ ታንታለም ዕምነበረድና የድንጋይ ከሰል ፍለጋና ምርት ሥራ ይሰማራሉ፤›› ብለዋል፡፡
ተዳክሞ የከረመው የማዕድን ኤክስፖርት ባለፉት ሦስት ወራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን፣ በተለይ የወርቅ ኤክስፖርት መሪነቱን ከግብርና ውጤቶች ኤክስፖርት መረከቡን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት የተለያዩ ማዕድናትን በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ178 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ እንደተገኘ ተገልጿል፡፡ ወርቅ፣ ታንታለም፣ ኳርትዝ፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየርና ዕምነበረድ ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪ ካስገኙ ማዕድናት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
(ቃለየሱስ በቀለ ~ ሪፖርተር)