መምህር የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ደራሲ የነበሩት ነፍስ ሔር ኘሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም (1922-2013) ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሙያ አጋሮቻቸው፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አክባሪዎቻቸው በተገኙበት የፊታችን ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም ይሸኛሉ።
የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ስርዓተ ቀብር የሚፈፀመው በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው ተብሏል።
በመምህርነትና ተመራማሪነት ያገለገሉበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለክብራቸው በሚመጥን መልኩ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ከግብዐተ መሬታቸው መርሐ ግብር አስቀድሞ ልዩ የስንብት ፕሮግራም ማዘጋጀቱ ታውቋል።
ኘሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ማንናቸው?
ተከታዩ የሔኖክ ያሬድ (ሪፖርተር ጋዜጣ) ዘገባ የሚነግረን ይኖራል።
“አንድ ትውልድ ይወለዳል፣ በጊዜው እንደጊዜው ያድጋል፣ ያልፋል፣ በሌላ ትውልድ ይተካል፡፡ አዲሱም ትውልድ የተረከበውን ቅርስ ይዞ ይነሳና በራሱ ጥረት አዳዲስ ሥራዎችን ሠርቶ ይጨምርበትና ያድጋል፣ አዲስ ነገርን ትቶ ያልፋል፡፡ የቀደመው ትውልድ ተፈጥሮና ኑሮው ከሚያስገድደው በላይ ለሚቀጥለው ትውልድ መስዋዕት መሆን አይችልም፣ አይጠበቅበትምም፡፡ በምፅዋትና በሞግዚት አስተዳደር የሚኖር ትውልድ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዕዳ ብቻ ነው፣ ዕዳን በውርስ ተሸክሞ የሚፈጠር ትውልድ ያለምርኩዝ መንቀሳቀስ አይችልም፣ ምርኩዝ ሊሆኑት የሚችሉት እነዚያው የዕዳው ባለቤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ከዕዳና ከምፅዋት አዙሪት አይወጣም፡፡”
ይህን ጠሊቅ ዕይታ የትውልድ ቅብብሎሽ አንፃራዊ ገጽታና ትችት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ትውልዶች” በሚል ርዕስ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ዜና ዕረፍታቸው ከመሰማቱ ከአሥር አምስት ቀናት በፊት የከተቡት ሊቁ መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን ለማንፀባረቅ ችላ የማይሉ፣ ዕውቀታቸውንና ምልከታቸውን በአደባባይ ለማስተጋባት የሚተጉ ነበሩ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፡፡ “ነፃ ሐሳብ ለነፃ ሕዝብ” የሚል አስተምህሮ የነበራቸው ያንንም ለመተግበር ዕውንም ለማድረግ ወደ ኋላ ማለት ማፈግፈግን ዞር በል የሚሉ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከሦስት አሠርታት ወዲህ ኢሰመጉን በመመሥረት ያሳዩት ተላሚነት ይበልታን አስገኝቶላቸዋል፡፡
ከዘውዳዊው ሥርዓት እስከ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ ከሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊኩ እስከ አሁን ዘመኑ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥታት ድረስ የሽግግር ዘመኑንም ጨምሮ በገሀድ በመሔስ የሚሰማቸውን በመጣጥፍና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በመግለጽ ከቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ሲጨብጥ በሽግግሩ ዘመን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ክርክር የገጠሙበት መንገድም (ሌሎች ምሁራን ጨምሮ) በብዙዎች ዘንድ ይታወሳል፡፡
በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰውን ድርቅና ረሃብ ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ ይፋ በማድረግ የሚጠቀሱት በስሚ ስሚ ያገኙትን ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት ያዩትን የተመለከቱትን በፎቶግራፍ ጭምር በማስደገፍ ከባልደረቦቻቸው ጋር መጣራቸው ይወሳላቸዋል፡፡ በርሳቸው አገላለጽ ‹‹ጠኔ›› የሚባለውን ረሃብ አስመልክቶ መፍትሔ ማሳያ መጽሐፍም እስከ ማዘጋጀት መድረሳቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
ከባህር ማዶ የቅድመና ድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሥራውን ገበታ የተቀላቀሉት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን ነው፡፡ በዘመኑ ጥቂት ምሁራን ብቻ የሚያደርጉትን ለሚያስተምሩት ትምህርት የመማርያ መጽሐፍ በማዘጋጀት ረገድም ዓይነተኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአካዴሚያ ሕይወታቸው ለፕሮፌሰርነት የበቁበት የጂኦግራፊያ መምህርነታቸው የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር በጥልቀት የሚያሳይ መጽሐፍን አበርክተዋል፡፡ የትምህርት ክፍሉንም እስከ መምራት ደርሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በነበሩበትና ጡረታ ከወጡም በኋላ ጥናታዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን አሳትመዋል። የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ የአደባባይ ምሁር ካሰኛቸው አንዱ የተለያዩ ጽሑፎችን በማዘጋጀት በጋዜጦች፣ በመጽሔቶችና በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ያለመታከት ሲያካፍሉ መቆየታቸው ነበር፡፡
በገጣሚነትም የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን በመስከረም 1967 ዓ.ም. ያሳተሟት ‹‹እንጉርጉሮ›› የግጥም መድበል የኅብረተሰቡን እንጉርጉሮ ያንፀባረቀች ናት፡፡ ከ38 ዓመት በኋላም የአገሬው እንጉርጉሮ ፈውስ ባለማግኘቱም የ2005 ዓ.ም. “ዛሬም እንጉርጉሮ” በማለት አሳትመዋል፡፡
ካዘጋጇቸውና የኅትመት ብርሃን ካገኙት መካከል ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት፣ አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ፣ ሥልጣን ባሕልና አገዛዝ፣ ፖሊቲካና ምርጫ፣ የክህደት ቁልቁለት፣ አገቱኒ፣ መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ አድማጭ ያጣ ጩኸት፣ እንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ፣ አዳፍኔ፣ ፍርሃትና መክሸፍ፣ ዛሬም እንደ ትናንትና ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዘውዳዊ ሥርዓት የተጀመረው ፖለቲካዊ ትግላቸው ወደ ፓርቲ ሕይወት የተሸጋገረው በ1997 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ ዋዜማ ከትግል አጋሮቻቸው ጋር ባቋቋሙት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አማካይነት ነው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስም ‹‹የሕገ መንግሥቱን ሥርዓት አደጋ ላይ በመጣል›› በሚል ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸው በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ከአባታቸው አቶ ወልደ ማርያም እንዳለና ከእናታቸው ወ/ሮ ይመኙሻል ዘውዴ ሚያዝያ 15 ቀን 1922 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በልጅነታቸው ዘመን በ1937 ዓ.ም. ለድቁና ያበቃቸውን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መሠረታዊ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ህንድ አገር በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማገልገላቸው ከመጀመራቸው በፊት በካርታና ጂኦግራፊ ኢንስቲትዩት ውስጥ ሠርተዋል፡፡
ባደረባቸው ሕመም ሳቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ፕሮፌሰር መስፍን ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ለረቡዕ አጥቢያ በ90 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ከሰኞ በኋላ እንደሚፈጸም የቀብሩ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው ታውቋል፡፡
ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሐዘን መግለጫቸው፣ “የሐሳብ ልዕልና ምልክት፣ የሰላማዊ ትግል አርአያ፣ ላመኑበት ነገር እስከ መጨረሻቸው ሞጋች፣ ላመኑበት እውነት ብቻ የሚቆሙት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በማረፋቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል፤” ብለዋል።
ከአርባ ስድስት ዓመታት በፊት በወርኃ መስከረም ካሳተሟት “እንጉርጉሮ” የግጥም መድበል ውስጥ የሞትን ምንነት ከገለጹበት ውስጥ የሚከተለው አንጓ ይገኝበታል።
ሞት ማለት:-
ሞት አለመስጋት ነው የግዴለሽ ዓለም፣
ድንጋይ ተሸክሞ በውኃ ላይ መቆም፣
ጤንነት የለበት፣ አያጠቃው ሕመም፣
ትዝታ የለበት፣ አይታይበት ሕልም፣
ቡቃያው አያሸት፣ ፍሬው አይለመልም።
ዝናብ አይዘንብበት ድርቀት ነው ዘላለም።
ማንም አይጎዳ ማንም አይጠቀም።
የሦስት ልጆች አባት የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ በኅልፈታቸው ዋዜማ በ13ኛዋ ወር ጳጉሜን ‹‹መልካም ምኞት ለአዲስ ዓመት በሚል ርዕስ በፌስቡክ ገጻቸው እንዲህ ተመኝተው ነበር፡፡
“2012 ዓ.ም. ቆሻሻውን አራግፎብናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ክረምቱን ከባድ አድርጎታል፣ እግዚአብሔር ክረምቱን ያከበደው በውስጣችንም ሆነ በላያችን የተሸከምነውን ቆሻሻ ለማጠብ እንድንችል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን በፍቅር፣ አዕምሮአችንን በዕውቀት ይሙላልን፡፡