የአስተዳደሩን ሥልጣን በኃይል ለመያዝና ለሽብር ወንጀል መሰናዳት ወንጀሎች የተከሰሰው እስክንድር ነጋ
ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለው የቆዩት እነ አቶ እስክንድር ነጋ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀና ለ)፣ 35፣ 38፣ 240(1ለ) እና የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌዎችን በመተላለፍ መንግሥትን ሰላም በመንሳትና እንዳይረጋጋ በማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥልጣንን ኃይልና አመፅ ተጠቅመው ለመያዝ በመንቀሳቀስና ለሽብር ወንጀል በመሰናዳት ወንጀሎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥትና የሽብር ወንጀሎች አንደኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ የፓርቲው አመራር ወ/ሮ ቀለብ ሥዩም፣ አስካለ ደምሌ ደሳለኝ፣ ጌትነት በቀለ፣ አሸናፊ አወቀና ፍታዊ ገብረ መድኅን ላይ ክሱን አቅርቧል፡፡
በተለይ አቶ እስክንድር፣ አቶ ስንታየሁ፣ ወ/ሮ ቀለብ፣ አስካለና ጌትነት የተባሉት ለተከሳሾች ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ለማነሳሳት፣ መንግሥት በማዳከም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ሥልጣንን ለመያዝ መሥራት የጀመሩት በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በወቅቱ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ‹‹የአዲስ አበባ ባላደራ›› በሚል ስያሜ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች የሚኖሩበትን አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪን እንወክላለን በማለት ሲንቀሳቀሱ ቆይተው፣ ሕገወጥ የነበረውን ድርጅት ‹‹ባልደራስ›› በሚል የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘታቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡
ፓርቲው ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስና ዓላማውን ማራመድ ሲገባው፣ በተቃራኒው በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ‹‹የኦሮሞና ትግራይ ተወላጆች እንዳይካተቱ፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች በተቻለ መጠን እንዳይኖሩ ወይም የእስልምና እምነት ተከታዮች ከተካተቱም ተፅዕኖ መፍጠር የማይችሉ መሆን እንዳለባቸው በመወሰን፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ያገለለ እንዳይመስል ፓርቲው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የሚሳተፉ ሙስሊሞችን ፎቶ ጎላ አድርገው በማንሳት በማኅበራዊ ሚዲያ ያሠራጩ እንደነበር ገልጿል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲ ሽፋን ሕገወጥ በሆነ ድርጊት በመሰማራት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የነበሩት ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ወደ ሥልጣን የመጡት በሕገወጥ መንገድ መሆኑን በመግለጽ፣ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስና የአዲስ አበባ ነዋሪን በማሳመፅ ከሥልጣን ለማስወገድ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡
ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ብሔርና እምነት ተኮርት ጉዳዮችን በመምረጥ ግጭት በመቀስቀስ መንግሥትን ሰላም በመንሳትና እንዳይረጋጋ በማድረግ፣ የጥላቻ ዘመቻ በመክፈትና የጥላቻ ዘመቻ የሚካሄድባቸውን የተለያዩ ዘዴዎችን በመንደፍ የፓርቲውን ደጋፊዎችና አባሎቻቸውን ሲያንቀሳቅሱ እንደነበርም ገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የምክትል ከንቲባውን ስም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ በትራንስፖርትና በተለያዩ አጋጣሚዎች በአካል ለሚያገኟቸው ሰዎች ጥላቻቸውን በመግለጽና ሐሰተኛ የፌስቡክ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ማናቸውን ዓይነት የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቅመው ስም በማጥፋት ጥላቻን ያሰርፁ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
ሕገወጥ ግንባታዎች በአስተዳደሩ እንዲፈርሱ ሲደረጉ ‹‹አስተዳደሩ ቅርስ አፈረሰ፣ ዜጎችን አፈናቀለ›› በማለት ፎቶ በማንሳትና ቪዲዮ በመቅረፅ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያሠራጩ እንደነበርና የኦሮሞና የአማራ ብሔር ተቆርቋሪ መስለው አንዱ ብሔር የሌላውን ብሔር እንዲዘልፍ፣ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች እንዲሠራጩ ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ መንግሥትን ለመጣል የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ እንደሚጠቀሙ በመግለጽ፣ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉና ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከመስከረም 30 ቀን በኋላ በከተማ አስተዳደሩ የሚቆየው ‹‹በእኛ እሬሳ ላይ ተረማምዶ ነው›› በማለት፣ ማንኛውንም መስዕዋትነት ለመክፈል ደጋፊዎቻቸውና የፓርቲው አባላት እንዲዘጋጁ ሲቀሰቅሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡
ተከሳሾቹ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ በቦሌ፣ በአራዳ፣ በጉለሌና በየካ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የእርስ በርስ ግጭት ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፣ ‹‹መንግሥት ከሃይማኖት ላይ እጁን ያንሳ›› የሚልና ሌሎች አንዱን ብሔር ከሌላኛው ብሔር ጋር የሚያጋጩ አፀያፊ ስድቦችን የያዙ መፈክሮችን በማራገብ፣ ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ በማድረግ የጥላቻ ንግግር ሲዘሩ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በተለያዩ ክፍላተ ከተማ ለሚገኙ አባሎቻቸው ‹‹ቄሮዎች ለሐዘን ወደ አዲስ አበባ ስለሚመጡ፣ የተደራጀውን ኃይል በመጠቀምና ለሁለት በመክፈል ቀጥቅጣችሁ እንዲመለሱ አድርጉ›› የሚል ተልዕኮ መስጠታቸውንም ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ጠቁሟል፡፡ ተከሳሾቹ የኦሮሞና የትግራይ ተወላጆች መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ መደብሮችና ሕንፃዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ መንቀሳቀሳቸውንም አክሏል፡፡ ተልዕኮ ለተሰጣቸው 1,500 ብር አበል በመክፈል ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተከስቶ የነበረውን የእርስ በርስ ግጭት መምራታቸውንም በክሱ ዘርዝሯል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ማናቸውንም አጋጣሚ በመጠቀም ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት ያደረገ ግጭት በማስነሳት የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያን እንደ አጋጣሚ በመጠቀምና ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት፣ በተለይ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲፈጠር ባደረጉት የእርስ በርስ ግጭት የ14 ሰዎች ሕይወት እንደጠፋና 187,258,459 ብር ንብረት እንዲወድም በማድረጋቸው፣ አንዱ ወገን በሌላኛው ወገን ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳና በመንግሥት ላይ የማሳነሳሳት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርቲውን እንደ ሽፋን በመጠቀም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ መስጊዶችንና አቢያተ ክርስቲያናትን የሚያቃጥል፣ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና ሌሎች የመንግሥሥት ባለሥልጣናትንና የፖለቲካ አመራሮችን በግድያ የሚያስወግድ ገዳይ የሽብር ቡድን መመልመላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ቡድኑ የተመለመለው ከአዲስ አበባና ከአማራ ክልል መሆኑንና ባልደራስ ሥልጣን ሲይዝ ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት ወደ ክልል ተልከው ምልመላ እንዲፈጽሙ ተሰማርተው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አስረድቷል፡፡ ተከሳሾቹ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ የሽብር ቡድን በመምራት በማሠልጠንና ለመሠልጠን ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በመግለጽ፣ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የመሰናዳት ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ የክስ ቻርጁ ደርሷቸው መቃወሚያና የመብት ጥያቄ ማንሳት የሚፈልጉ ስለመሆናቸው ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው የተጠቀሱባቸው ክሶች እነሱን እንደማይመለከቱ፣ የታሰሩበትና የተከሰሱት የፖለቲካ ልዩነት ስላላቸው መሆኑን ተናግረው በሌሉባቸው የወንጀል ተሳትፎ ከመከሰሳቸው አንፃር ዳኞች በሕጉና በህሊናቸው ብቻ ገለልተኛ ሆነው እንዲዳኟቸው ጠይቀዋል፡፡ ከጠበቆቻቸው ጋር በመመካር በክሱ ላይ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረው ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ምላሻቸውንና የሚያቀርቡትን የመብት ጥያቄ ለመስማት ለመስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡(ታምሩ ፅጌ~ ሪፖርተር)