Connect with us

ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው!

ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው!
Photo: Social Media

ትንታኔ

ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው!

ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው !
(ዮሐንስ መኮንን)

በሀገራችን የታየውን ማሻሻያ (Reform) ተከትሎ የዜጎችን ትእግስት የሚፈታተን እና “ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ነው?” የሚያስብሉ ክስተቶች በየወቅቱ መከሰታቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው። በአንድ ወገን ማሻሻያውን (Reform) በሚመሩት እና “አብዮቱን ያመጣነው እኛ ብቻ ነን” ባዮች ለከት የለሽ የሕግ ጥሰት የአማካይ ፖለቲካ (Center Politics) ደጋፊ ዜጎች ስንበሽቅ በሌላ ወገን ደግሞ “ይህንን ሁሉ የሕግ ጥሰት እንዳላየ እንዳልሰማ ለምን ዝም ትላላችሁ?” በሚሉ ከሳሾች እንደ ወዶ ገብ መብጠልጠላችን አልቀረም።

ከለውጡ ተሥፋ በተቃራኒ በዝግ ስብሰባዎች የተነገሩትን አወዛጋቢ ንግግሮች እና የሸፍጥ ፖለቲካ አካሄዶች ትተን በአደባባይ የተነገሩትን ጥቂቶቹን አስተዛዛቢ ትርክቶች ብቻ ወደኋላ ተመልሰን እናስታውስ!
______

#1
ከኦሮሞ አርቲስቶችና አትሌቶች ጋራ በተካሄደ ስብሰባ ላይ አቶ አዲሱ አረጋ …

‹‹…እነ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጠዋትም ማታም ሻይ አብረን ስንጠጣ፣ የኦሮሞን ጥቅም አዲስ አበባ ውስጥ ለማስጠበቅ፣ በተለይም ካሁን ቀደም ተገፍቶ ከአዲስ አበባ ሲወጣ የነበረውን አርሶ አደርና፣ ኦሮሞነት ከከተማ ውጭ እንዳይሆን ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው” ማለታቸውን አንዘነጋውም።

#2
በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በተደረገ የጨፌ ኦሮሚያ የእርቅ ህዝባዊ ሸንጎ ላይ አቶ ለማ መገርሳ

“ከሶማሌ የተፈናቀሉትን ከ 500, 000 (አምስት መቶ ሺህ) በላይ ሰዎችን፣ እንዲያውም አዲስ አበባ ዙሪያና አዲስ_አበባ ውስጥ አስፍረናል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 6000 (ስድስት ሺህ) አስገብተናል፤ … ማለታቸውን አንረሳውም።

#3
ከአራት ወራት በፊት “በተለያዩ ጊዜያት ካሳ ተከፍሏቸው (ካሳው በቂ ላይሆን ይችላል) ከመሬታቸው ተፈናቅለው ነበር” ለተባሉ አርሶ አደሮች 460 ሺህ ካሬ አዲስ አበባ ላይ ሲያስረክቡ የወቅቱ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ “የኦሮሞ ትግል ማዕከል አዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ብቻ ናት” ማለታቸው መች ተዘነጋን?

#4
መስቀል አደባባይ ላይ ኢሬቻ በተከበረበት እለትም ሆነ ሰሞኑን ዋንኛ አጀንዳ ሆኖ በከረመው የአዳራሽ ውስጥ ንግግራቸው አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለውጡ ዋንኛ (ምናልባትም ብቸኛው) ማጠንጠኛ ኦሮሞን ብቻ ለይቶ “ተጠቃሚ” ማድረግ ማስመሰሉ በለውጡ አቅጣጫ ላይ ተሥፋ የሚያስቆርጥ ንግግር ሆኖ ተመዝግቧል።

#5
ኢዜማ በአዲስ አበባ ውስጥ ታይተዋል ያላቸውን የህግ እና የመርኅ ጥሰቶች መርምሮ የከተማ መስተዳደሩ ሃሳብ እንዲሰጥበት በጨዋ ደምብ ሠነዱን ለከተማ አስተዳደሩ ቢያስረክብም አስተዳደሩ መልስ ሳይሰጥ ቆይቷል። ይባስ ብሎም ሁለት ጊዜ የፓርቲው ጋዜጣዊ መግለጫ መታገዱ ይታወሳል።

የኢዜማን መግለጫ ከሚዲያዎች እንደሰማነው በአዲስ አበባ የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ

• ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ፤

• በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታ እና ፕላን ተሠርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ መተላለፍ፤ በማኅበር እና በግል፣ ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉም መደረግ፤

• የመሬት ወረራው ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ‹ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸው› እና ‹በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል› የሚሉ ግለሰቦች እና ወረራ በተፈፀመባቸው ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች መሆን፤ ሕገ-ወጥ ደላላዎችም ተሳታፊዎች መሆናቸው፤

• በጠራራ ፀሐይ፣ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ባሉ አመራሮች እና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን የነበሩበት መሆኑ፤

• በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች በተለያየ መልኩ ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወርረው እንዲይዙ ማመቻቸታቸው፤

• ሕገ-ወጥ የሆኑ የግንባታ ፈቃዶች፣ ካርታ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማዘጋጀት ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሕጋዊ መስለው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተነግሮናል፤
—————————-

ጥናቶች እንደሚያረጋገጡት 83% የሚሆኑት የአውሮፕላን በረራ አደጋዎች የሚከሰቱት አውሮፕላኖች ለመነሳት ሲያኮበኩቡ ወይንም ሊያርፉ ሲያንዣብቡ ነው (Aviation Knowledge Forum) ከዚህም የተነሳ በበረራ ሥርዓት የአውሮፕላን መነሻ እና ማረፊያ ወቅቶች Critical Phase ይባላሉ።

በዚህ ወቅት የበረራ አስተናጋጆች በተሳፋሪዎች ወይንም በሌሎች ሠራተኞች የሚታዩ ችግሮች፣ ጭቅጭቆች ወዘተ ለአብራሪው ሪፖርት አይደረጉም። ምክንያቱም ፓይለቶቹ የብዙዎችን ሕይወት ደኅንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሥራ ላይ ስለሚጠመዱ።

ሀገራችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ስታካሂድ የቆየችው የሥርዓት ማሻሻያ (Reform) እኔን ጨምሮ ለበርካታ ዜጎች Critical Phase ዓይነት ስሜት ነበረው። እዚህም እዚያም በለውጡ አመራሮችም ሆነ በጽንፈኛ ዘውጌ አክቲቪስቶች የሚታዩ ዳኀጸ ልሳንም ሆነ የእብሪት ተግባሮች አንስቶ ማራገብም ሆነ ማጋጋል ሀገርን አደጋ ላይ እንዳይጥል አርቆ በማሰብ ዐይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ ሆኖ በሆደ ሰፊነት እና በትዕግስት ማለፍ ምርጫቸው ያደረጉ በርካታ ቅን አሳቢ ዜጎች መኖራቸውን እገነዘባለሁ። አውሮፕላኗ አስጨናቂውን Critical Phase አልፋ በሰላም ምድር ላይ እንድታርፍ እንደመጠንቀቅ ዓይነት!

ለሀገራችን እና ለኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ካለን ተቆርቋሪነት እና በጎ ምኞት የተነሳ በቀና ሱታፌ (Constructive Engagements) የለውጡን አመራር በየደረጃው እንደየ አቅማችን ለማገዝ የምንደክም ዜጎች አንዳንዴ መንግሥት ራሱን በልቶ እንዳይጨርስ “ኧረ ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው” ማለትም ያስፈልጋል እላለሁ።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ትንታኔ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top