‹እኛና ሱዳን አንድ ሕዝብና አንድ ቤተሰብ ነን፤ ልዩነቶቻችንን ተግባብተን እንፈታለን›› – ጠ/ሚ ዓብይ አህመድ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶክተር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሰሞኑን የተለያዩ አገሮችን ትኩረት በሳበችው ሱዳን የሥራ ጉብኝት አደረገ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተመራውና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተካተቱበት የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሱዳን ያቀናው ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ልዑክ ውስጥ ከተካተቱት መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ልዑክ በሱዳን ከተማ በደረሰበት በዛው ዕለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማይክ ፖምፒዮ በካርቱም ተገኝተው ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሐምዶክና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና ልዑካቸው እንዲሁም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ፖምፒዮ ሱዳንን በተናጥል ከመጎብኘታቸው ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ በግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማዶቦሌ የተመራ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በካርቱም ተመሳሳይ የሥራ ጉብኝት አድርጎ ነበር።
በካርቱም የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሱዳኑ አቻቸው አብዳላ ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ‹‹እኛና ሱዳን አንድ ሕዝብ ነን፣ አንድ ቤተሰብ ነን›› በማለት ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ በሱዳን በኩል የሚነሳው ቅሬታም ሆነ በድንበር ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶች በዚሁ ቤተሰባዊ መንፈስ እንደሚፈታ ለሱዳኑ አቻቸው ማረጋገጣቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሰክሬታሪ (ቃል አቀባይ ቢሮ) አስታውቋል።
የጉብኝቱ አንዱ ዓላማ በሆነው የኢትዮጵያና የሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የሚመክር የጋራ ጉባዔም በካርቱም መካሄዱን የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል አስታውቋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፖምፒዮን አግኝተው መወያየታቸው ታውቋል።
ፖምፒዮ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያለውን የአሜሪካ ፍላጎት ለማስፈጸም በጀመሩት የሥራ ጉብኝት ውስጥ መዳረሻ ካደረጓቸው አገሮች መካከል አንዷ ሱዳን መሆኗን የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ፖምፒዮ በጀመሩት በዚህ ጉብኝት የመጀመርያ መዳረሻ የነበረችው አገር እስራኤል ስትሆን፣ በእስራኤል የነበራቸውን የአንድ ቀን ቆይታ አጠናቀው እስራኤልና ሱዳንን ከረጅም ዓመታት በኋላ ባገናኘ የቀጥታ በረራ ወደ ሱዳን ከተማ አምርተዋል።
ይህንንም ጉዞ አስመልክቶ ፖምፒዮ በቲውተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ጉዞው ከእስራኤል ወደ ሱዳን የሚደረግ ታሪካዊ የቀጥታ በረራ እንደሆነ አመልክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኋላፊው በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ በእስራኤልና በሱዳን መካከል የተቋረጠውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም ማስጀመርና በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሆነ ጉዟቸውን አስመልክቶ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ማይክ ፖምፒዮ በሱዳን የነበራቸውን ጉብኝት አስመልክቶ የሱዳን መንግሥት ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች ውይይት ትኩረት ሰጥተው ከተወያዩባቸው አንኳር ነጥቦች መካከል አሜሪካ ሱዳንን ሽብርን ከሚደግፉ አገሮች ዝርዝሯ ውስጥ እንድታስወጣና በሱዳንና በእስራኤል መካከል ሰላማዊና መደበኛ ግንኙነት በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ እንደነበር አስታውቋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካ በፍጥነት ሱዳንን አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገሮች ዝርዝር ውስጥ በመሰረዝ የሱዳንን የሽግግር መንግሥት እንደትደግፍ መጠየቃቸውን መግለጫው አስታውቋል።
በሱዳንና በእስራኤል መካከል ያለውን የሻከረ ግንኙነት አስታርቆ ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስን በተመለከተ፣ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ሥልጣን እንደሌለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ መግለጻቸውን የአገሪቱ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ይጠቅሳል፡፡
ይህ ሥልጣን ከሕዝብ የሚመነጭ በመሆኑ የሽግግር መንግሥቱ በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት ሥልጣኑን ካስረከበ በኋላ ሊታይ የሚችል እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሱዳንን ከሽብር ዝርዝር ውስጥ የመሰረዝ ጉዳይ ከእስራኤል ግንኙነት ጋር መቆራኘት እንደሌለበት ማሳሰባቸውንም መግለጫው አመልክቷል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ሱዳንን የጎበኘው የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በግብፅና በሱዳን መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ያተኮረ እንደነበር የሱዳን መንግሥት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተመራው የግብፅ ልዑክ በሱዳን ከቀናት በፊት ባካሄደው ጉብኝ ወቅት፣ ሁለቱ አገሮችን የሚያገናኝ የባቡር መሠረተ ልማት ለመገንባት፣ ተጨማሪ ኤሌክትሪክ መስመር ትስስር ለመፍጠር፣ በግብርና ቴክኖሎጂ ሱዳንን ለመደገፍ፣ በቀይ ባህር አካባቢ ደኅንነት ላይ ለመተባበርና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ ስምምነት ማድረጋቸው ታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ የሚመራው የሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣበት አንደኛ ዓመት በዚሁ ሳምንት ተዘክሮ ነበር።
የሽግግር መንግሥቱን የአንድ ዓመት ጉዞ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ አድረግው የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ቃለመጠይቅ ላይ ከቀረቡላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ መንግሥታቸው የሚያራምደውን አቋም እንዲያስረዱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
‹‹ከጥንስሱ ጀምሮ ሱዳን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም የምታገኝ በመሆኑ ስትደግፈው ነበር። አሁንም ይህ አቋማችን አልተቀየረም። ነገር ግን ግድቡ በሱዳን ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ጉዳት ስለሚኖር ይህንኑ ሥጋትም ከጅምሩ አንስቶ ሱዳን ስታንፀባርቅ ነበር፤›› ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ በሱዳን ከሚገኙት ግድቦች በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝና ግዝፈቱ ከሱዳን ግድቦች አሥር እጥፍ የሚበልጥ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የደኅንነት ሥጋት ለመፍታት ድርድር ላይ መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለው ልዩነት ወደ ግጭት ያመራ እንደሆነ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሦስቱ አገሮች ልዩነት በውይይት እንደሚፈታ እንደሚያምኑና ይህንንም ለማሳካትና በተለይም ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርህ መሠረት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ሥር በኅብረቱ ሊቀመንበር መሪነት መካሄድ መጀመሩ እምነታቸውን እንዳጠነከረው ገልጸዋል።(ሪፖርተር ~ ዮሐንስ አንበርብር)