Connect with us

ደብረ ታቦር-የደብረ ታቦር ሙሽራዋ

ደብረ ታቦር-የደብረ ታቦር ሙሽራዋ

ባህልና ታሪክ

ደብረ ታቦር-የደብረ ታቦር ሙሽራዋ

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በደብረ ታቦር ከተማ ደብረ ታቦር በዓልን ለመታደም ገብቶ ቆይታውን እየተረከልን ነው፡፡ ታሪካዊቷ ከተማ ዛሬ ሙሽራ ናት ሲል የደብረ ታቦር ተራራ አናት ያለውን ድባብ እንዲህ ይተርክልናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ደብረ ታቦርን ቁልቁል አየኋት፤ ደብረ ታቦር ተራራ ላይ ቆሜ፡፡ የደብረ ታቦር ዕለት-ደብረ ታቦርን ላከብር፡፡
ከተማዋ አድጋለች፡፡ የፋርጣ አድማስ ሞገስ ለብሷል፡፡ 2700 ሜትር ከባህር ወለል በላይ ከፍታ ላይ የተዘረጋችው ከተማ አሁን እንደ ሸለቆ እግሬ ስር ተኝታለች፡፡ ከጉና በታች ከጁራ በላይ ደብረ ታቦር ተራራ አናት ቆሜያለሁ፡፡ ከጣና ሐይቅ ስሜናዊ አቅጣጫ ነኝ፤ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ገደማ፡፡ አዲስ አበባ ከዚህ 667 ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ ለገናና ታሪካችን ከምትቀርበው መዲና ነኝ፡፡

ጁራ የቀድሞ ስሟ ነው፡፡ የቆምኩበት ለከተማዋ መጠሪያ ምክንያት የሆነ የተፈጥሮ ማማ ነው፡፡ ዐፄ ሰይፈ አርእድ ኢየሱስን ተከሉ፤ ከተማዋን ከተሙ፡፡ 1350 ገደማ የፋርጣ ምድር እምብርት ይኽቺ ከተማ ጎጆ ወጣች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የነገሥታቱን ቀልብ እንደገዛች የኖረች ባለ ታሪክ ናት፡፡

የጅራፍ ድምጽ ይጮሃል፡፡ ሆ የሚሉ ልጆች ቡሄን ያወድሳሉ፡፡ ሰንበት ተማሪዎች በደብረ ታቦር የተገጠውን የመለኮት ብርሃን በዝማሬ ያነሳሉ፡፡ ሊቃውንት በተክሌ ዝማሜ ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ የተክሌ ዝማሜ የተዘራበት፣ የበቀለባት፣ እልፍ ሊቃውንት ያፈራባት መዲና መጥቻለሁ፡፡

ዘመነ መሳፍንት የዓይኑ ብሌን ይህቺ ከተማ ነበረች፡፡ በትዝታ ሄድሁ፤ የልብነ ድንግል ዘመን ወደ ነበረችው ደብረ ታቦር፤ የራስ ጉግሳ ቆንጆ ወደነበረችው መዲና፤ የአሊ ጓንጉልን ልብ ወደ አጠፋችው ቅርስ፤ የሴት አቦ ሸማኔ ንግርት የጦረኞች መዲና ወደ አደረጋት የራስ ጉግስ ከተማ፤

እልልታው አስተጋባ፤ ከጣና እንደሚመጣው አየር ከአምባው ወደ አጅባር ሜዳ ፈሰስ፤ ከእናቲቱ ማርያም እስከ ታላቁ መዳሃኒዓለም፤ በያሬዳዊ ዜማ፣ በተክሌ ዝማሜ ውበት ዳግም በደብረ ታቦር ብርሃን ሆነ፤

የእቴጌ ጣይቱ ትውልድ ቀዬ፤ የዮሐንስ አራተኛ የክረምት ሙቀት፤ የቴክኖሎጂ ጥማት የኢንዱስትሪ ናፍቆት ዘሯ፤ ደብረ ታቦር፡፡ እውነትም የደብረ ታቦር ሙሽራ፡፡ ፎቶውን ላነሳው በሪሁን ታደለ እጅህ ይባረክ ብያለሁ፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top