Connect with us

ዛሬን ለማመስገንማ ትላንትን አንወቅስም

ዛሬን ለማመስገንማ ትላንትን አንወቅስም
Photo: Social Media

ባህልና ታሪክ

ዛሬን ለማመስገንማ ትላንትን አንወቅስም

ዛሬን ለማመስገንማ ትላንትን አንወቅስም፤ ትናንትም ቢሆን ሊታሰቡ የማይችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋልና፤
****
ከስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ

ዶክተር አብይ አስበው ጀምረው የጨረሷቸውን ፕሮጀክቶች ትናንት በኢትዮጵያ ቴሌቨዥኖች ለመላ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው አስጎብኝተዋል፡፡ አንዳንዶች ፕሮጀክቶቹ ቀድሞውኑም የታሰቡ ናቸው ብለው ይሞግታሉ፡፡ ለምሳሌ እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ በ1988 አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጌታቸው ሰናይ የጻፉትን በእንጦጦ ኮረብታ ለአዲስ አበባ ልዩ ጌጥ የሚሆን መናፈሻ ሊሰራ መታቀዱንና ከክልል 14 የቅርስ ባለ አደራ ማህበር መሬቱን መረከቡን የሚገልጽ ዜና ለትውስታ ተለጥፎ አይተናል፡፡

አላሳኩትም እንጂ ኢህአዲጎችም ቢሆን አዲስ አበባ ወንዞች ይልሙባት ብለው የወንዞችና አረንጓዴ ልማት ኤጀንሲ አቋቁመው ነበር፤ ቤተ መንግስቱን ሙዚየም ለማድረግ የነ ዶክተር ሀሰን ድካምም እንዲሁ የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን የቀደመ ምኞት ነበር፡፡ ያ ሁሉ ሆኖ የለውጥ ሃይሉ መሪ እውን አድርገውታል፡፡

ችግሩ ዛሬን ለማመስገን ትናንትን ካጣጣልን ነው፡፡ ትናንትናም ቢሆን ግዙፍና ሊታሰቡ የማይችሉ ፕሮጀክቶች እውን የሆኑባት ኢትዮጵያ ናት፡፡ አባይን መገደብ መገንባትና መሙላት አይደለም ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ግልግል ግቤ፣ ግቤ ሁለትና ሦስት ተከዜ ጣና በለስ እያልን ሃይል ማመንጫውን ከቆጠርን ትናንት ኩነኔ ብቻ ያለበት ምዕራፍ ነው ብለን ደፍረን አንናገርም፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ተአምር ናቸው፡፡ አርባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ያመጣውን የልማት አብዮት ከየከተሞቹ ህዝብ ልብ ማፈስ ይቻላል፡፡ የኤርፖርቶች መስፋፋት፣ የግዙፍ ድልድዮች ግንባታ፣ የረዣዥም አይታሰቤ መንገዶች እውን መሆን የትናንት ቱሩፋት ናቸው፡፡

የትናንትን በደል ብቻ ማጥናት 100 አመት ወደ ኋላ ሄደን ስንተርከው ከኖርነው ቆሻሻ ትርክት ጋር ተነጥሎ አይታይም፡፡ እንደ ሀዋሳ ባህር ዳርና መቀሌ እኮ የትናንት ልማት ውጤቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ጥሩ ነገር ሲሰራ ትናንት ላይ እንሳለቅ ካልንማ አይሆንም ትናንት ከዛሬ ቢገዝፍ እንጂ አያንስም፡፡

ኮለኔል መንግስቱ እንኳን በዚያ አበሳ ጦርነት ላይ ሆነው በደንብ የሚቆጠር ስራ ሰርተዋል፡፡ ኢህአዴግ የሚታማበት ቢኖርም የሚወደስበት ልማት ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ ዛሬ እንደ ማተባችን የምንመለከተው የአባይን ግድብ ከኢህአዴግ ለመለየት መሞከር ነውር እንጂ ክብር አይደለም፡፡

ኮንዶሚኒየሞቻችንን ካሰብን ትናንት የባከነ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ እኮ እጣ አልወጣልኝም ብለን የምንሻኮትበት በአመት አስር ሺህ ቤት ብርቅ ሆኖ ነው፡፡ በአስራ ሁለት አመታት ወስጥ በመቶ ሺህ የሚቆጠር የጋራ መኖሪያ ቤት መስራት ትናንትን ጨለማ ብቻ ነው ካስባለው ሚዛኑ ጠማማ ነው፡፡

ዶክተር አብይን በመደገፉ የበለጠ እንዲሰሩ ማድረጉ እንጂ ከትናንት አወዳድሮ ትናንትን መርገሙ ለሀገር አይበጅም፤ ለዶክተር አብይም ቢሆን ነገ ተረኛ ተረጋሚ መሆናቸውን ይነግራቸው እንደሁ እንጂ ዛሬ መወደዳቸውን አያበስርም፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top