የተበዳሪው ማመልከቻ:-
ይድረስ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ!
እኔ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከባንኩ የኮንደምኒየም ብድር ከወሰዱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነኝ። ባንኩ የኮሮና ወረርሽኝ በተበዳሪ ደንበኞች ላይ እያሳደረ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመካፈል ሲል በሰጠን ለሶስት ወራት የሚቆይ የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። የተሰጠው የእፎይታ ጊዜ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቋል። በዚህም ቅንነት የታከለበት እርምጃ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ የባንኩን ከፍተኛ ማኔጅመንትና ሰራተኞች ከልብ አመሰግናለሁ።
እንደእድል ሆኖ በአለምም ሆነ በአገራችን በአሁን ሰአት የኮሮና ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው ጫና ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መጥቷል። በኢትዮጵያ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አልተነሳም። “የገበታ መካፈል” የመንግስት አቅጣጫም አልተቀየረም።
ባንኩ ግን የኮሮና ችግር ጨርሶ የጠፋ ይመስል ትላንት ችግራቸውን ለመካፈል ዋጋ የከፈለላቸው ደንበኞቹን በአሁን ሰአት “እዳችሁን ክፈሉ” በሚል ማስጨነቁን ቀጥሏል። ይህ የባንኩ እርምጃ ቀድሞውኑም ለታይታ የተወሰደ እንዳያስመስልበት እና ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳያሳንስበት በግሌ እሰጋለሁ። ለምን ቢባል ባንኩ ብድር ለማራዘም የተገደደበት ዋንኛ ምክንያት ከመወገድ ወይንም ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መጥቷልና ነው።
በዚህ ክፉ ወቅት እኔን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የባንኩ ተበዳሪ ደንበኞች የገቢ መቀዛቀዝ ገጥሞናል። እናም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልክ እንደመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ወቅታዊ ችግሩ አለመቀረፉን እንደገና ገምግሞ ቢያንስ መንግስት የችግሩን መቀነስ እስከሚያውጅበት ቀጣይ ጊዜ ድረስ የደንበኞቹን ችግር መካፈሉን እንዲቀጥል በሌላ አነጋገር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የብድር መክፈያ ጊዜውን በድጋሚ እንዲያራዝም እጠይቃለሁ።
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
እሱባለው ካሳ ነኝ
*********************
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ የ3 ወራት የብድር መክፈያ እፎይታ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ ለጋራ መኖሪያ ቤት ደንበኞቹ የሶሰት ወራት የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜ መስጠቱን አስታወቀ።
በዚህም ባንኩ ከደንበኞቹ መሰብሰብ የሚችለውን ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ብድር ወደቀጣይ ጊዜ ማስተላለፉን ነው የገለጸው።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባንኩ መንግስት ነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመፍታት ያወጣውን ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ላለፉት ዓመታት ከ74 ቢሊየን ብር በላይ በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች ለፕሮግራም ማስፈጸሚያ ብድር መስጠቱን ገልጸዋል።
በተጫማሪም ነዋሪዎች ከባንኮች ጋር በመቆጠብ የቤት እድለኛ በሚሆኑበት ጊዜ የሚሰጠውን በረጅም ጊዜ የሚከፈል ውል ከ107 ሺህ በላይ ለሆኑ ደንበኞች ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ማቅረቡንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በ40/60፣ በ20/80 እና በ10/90 የመኖሪያ ቤት ልማት መርሐ ግብር ከ31 ቢሊየን ብር በላይ በመቆጠብ የቤት ባለቤት ለመሆን በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በመላው ዓለም የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸው፤ ደንበኞች በወረርሽኙ ሳቢያ ብድራቸውን በተቀመጠላቸው ጊዜ መክፈል ይቸገራሉ በሚል የብድር መክፈያ ጊዜ እፎይታ ለመስጠት መወሰኑን አብስረዋል።
በዚህም ከሚያዝያ ወር እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ መክፈል የሚጠበቅባቸው የሶስት ወራት ክፍያ እንደተራዘመላቸው ይፋ አድርገዋል።
ለዚህም ደንበኞች ባንኩ ቀርበው ምንም አይነት ውል መፈጸም አይጠበቅባቸውም።
ነገር ግን የብድር መክፈያ ጣሪያው እንደማይራዘም ገልጸው፤ ”ክፍያውን መክፈል አቅም ያላቸው ደንበኞች የወርሃዊ ብድር ክፍያቸውን እንዲከፍሉ ይበረታታሉ” ብለዋል።
ባንኩ የብድር መክፈያ ጊዜ እፎይታ በማድረጉ 542 ሚሊየን ብር ገንዘብ መሰብሰብ ይችል እንደነበር ገልጸው፤ ”በወረርሽኙ ምክንያትም ወደቀጣይ ጊዜ አራዝሟል” ነው ያሉት።
ይህ በእንዲህ እንዳለው ባንኩ ብድር ወስደው መክፈል ባለመቻላቸው ንብረታቸው በጨረታ ሂደት ላይ ያሉ ደንበኞች ወረርሽኙ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ለጊዜው የጨረታ ሂደቱ እንዲቆም መወሰኑን አብራረተዋል።
የብድር ማራዘሚያ የሚከፈለው የአገልግሎት ክፍያ በእነዚህ ብድሮች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።