የኢትዮጵያ መንግስት እውነቱን መናገሩ ፖለቲካዊ ስም ያሰጥብኛል ብሎ ተሽኮርምሟል | ከስናፍቅሽ አዲስ
ከሰው ህይወት ከወንድምና እህት ሞት በላይ ስሙ ያጣላናል ብዬ አላምንም ነበር፤ እርግጥ ነው ግጭት ብለው ቅጽል ስም ያወጡለት ሹማምንት ከተግባሩ ጀርባ ላለመኖራቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡ ግጭት በሁለት ወገን የሚኖር ጠብ እንጂ ሰው እየሸሸ የሚገደልበት፣ በተኛበት የሚታረድበት፣ በማንነቱ የሚጨፈጨፍበት አይደለም፡፡
የሆነውን ለይተን ካላወቅነውና የለየንውን ካላረምነው ዳግም ላለመሆኑ ምን ዋስትና አለ? ክርስቲያን ሆነው ኦሮሞ መሆን እኮ ምስራቁ ኢትዮጵያ ላይ አበሳ ሆኗል፡፡ ብዙ አካባቢዎች የሰላሌ አካባቢ ሰዎች ላይ ጭምር ጥቃቱ ተፈጽሟል፡፡ ክፉ አድራጊዎቹ ፍላጎታቸው የተለየ እንደሆነ የሚታወቀው ለፍላጎታቸው የተቀራረበ ወገናቸውን ሁሉ አጥቅተዋል፡፡
የተፈጠረው ቀውስ አንድና ወጥ ቀለም አለው ማለት አይቻልም፡፡ ለሌብነት ብሎ እምነትና ብሔር ያልለየ ቡድን ጎን ለጎን ስራውን ሰርቷል፡፡ ይሄ ግን ዋናውን ምስል አያደበዝዘውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈንቅሎ መጣልና አማራ ክርስቲያኑን አርዶ ማሳደድን ያቀናጀ ሴራ ነበር፡፡
ዛሬም ዘር ማጥፋት አይደለም የሚሉ ሰዎች እምነት ተኮር አይባል ብለው የሚሟገቱ እንሰማለን፡፡ እምነት ተኮርና ብሔር የለየ ማለት የገዳዩ ወገን ብሔር እና እምነት ገዳይነትን ይፈቅዳል መርሁ ነው ማለት አይደለም፡፡ የድርጊት ፈጻሚዎቹ ዓላማ ግን በብሔርና በእምነት የማይመስላቸውን መግደል ነው፤ ሊያውም በአሰቃቂ ሁኔታ፡፡
እንዲህ ያለው ተግባር ስሙ ሌላ ነው ብሎ መሟገት በራሱ ያስተዛዝባል፤ በጀርመን ዘር ማጥፋት አይሁድ ላይ ሲፈጸም በወቅቱ እንደ አይሁድ ሁሉ ሰውነት የበለጠባቸው ጀርመናውያን በአስተሳሰባቸው አብረው አልቀዋል፡፡ በሩዋንዳ ለዘብተኛ የተባሉ የጨፍጫፊው ጎሳ አባላት ከተጨፍጫፊው ወገን ተፈርጀው አልቀዋል፡፡ ይሄ የድርጊቱ ስም አላስቀየረውም፡፡
የተፈጸመው ነገር ልብ ይሰብራል፡፡ አንገት የሚያስደፋና የሚያሸማቅቅ ነው ወንድማማችነታችን ላይ እሳት የለኮሱ ጨካኞች በጥፋታችን ሀሳባቸውን አላሳኩም፡፡ የታሰበው ሁሉ ከሽፎም ዛሬ ዳግም ተግባሩን ስም አትስጡት ብለው ይሟገታሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እንደ አጠቃላይ ተግባሩ ያሳፈረውና ስም ያጣለት ሆኖበታል፡፡ እውነቱን መናገሩ ደግሞ ፖለቲካዊ ስም ያሰጠኛል ብሎ ተሽኮርምሟል፡፡ በዚህ ደረጃ አጠራጣሪ ጉዳይ ካለ መፍትሔው የአፍሪካ ህብረትና የተመድ ገብተው ይፈትሹት፣ ስም ይስጡት ዓለምን ያስተምሩበት፡፡ ሞቶም ሟች እንዴት እንደሞተ መናገሩ ወንጀል ከሆነ ዓለም አሟሟቱን ይመስክርና ይናገር፡፡ ያኔ ምናልባት ባህር ማዶ ሆነው የሚያጨራርሱ የድርጊቱ አንጋፋዎችም ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይገተራሉ፡፡ ያኔ እውነቱ ይወጣል፡፡
( ማስታወሻ ከአዘጋጁ:- ይኸ አስተያየት የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም።)