Connect with us

የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት አወገዙ

የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት አወገዙ
Photo: EPA

ባህልና ታሪክ

የእስልምና ሃይማኖት አባቶች በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት አወገዙ

የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌ የሠላም ኮሚቴ አባላት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት አወገዙ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር በበርካታ ምዕመኗ ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቃለች።

የሃይማኖት አባቶቹና የሠላም ኮሚቴው አባላት በዜጎች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር ታስቦ የተፈጸመ ነው ሲሉ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሄኖክ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሃጂ ጀይላን ከድር፣ የኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዲሁም ከሃገር ሽማግሌዎች የሠላም ኮሚቴ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ሌሎችም ተገኝተዋል።

አባቶቹ የተፈጸመው ድርጊት ማንኛውንም የሃይማኖት ተቋምና ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል እኩይ ተግባር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያወግዘው ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሄኖክ ክርስቲያንና ሙስሊሙ በዚች አገር ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ በሠላምና በፍቅር አብረው ኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በክልሉ በአጥፊዎች በደረሰው ጉዳት በሰባት ሀገረ ስብከት የ17 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ በዜጎች ላይ የስነ ልቦና ተጽዕኖ ደርሷል፤ ንብረትም ወድሟል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሃጂ ጀይላን ከድር በበኩላቸው በእስልምና ሃይማኖት የሰው ሕይወት ማጥፋት ከባድ ሃጢያት ነው ብለዋል።

በዜጎች ላይ አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙት አካላት እስልምናን የማይወክሉ በመሆናቸው እናወግዛቸዋለን ሲሉም ኮንነዋል።

የኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ሙስሊምና ክርስቲያኑ ከጥንት ጀምሮ አንዱ የሌላውን እምነት አክብሮና ተዋደው መኖራቸውንም አውስተዋል።

በስመ እስልምና በዜጎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱና አገር የሚያተራምሱ አካላት ከእኛ ወገን አይደሉም፣ የእስልምናን ሃይማኖት አስተምህሮም የማያውቁ ናቸው ሲሉ ነው የገለጹት።

የእስልምና መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው በዜጎች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ልብ የሚሰብር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ብለዋል።

ሌሎችም ድርጊቱ እስልምናና ተከታዮቹንም የማይወክል በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች የሠላም ኮሚቴ አባል አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴም በአገሪቱ ሁከትና ግርግር በማስነሣት ትርፍ ለማግኘት የሚሹ አካላትን በጋራ ልንመክት ይገባል ብሏል።

ወጣቶች ኡኩይ አጀንዳ ላላቸው አካላት መጠቀሚያ ባለመሆን ራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስቧል።

የሠላም ኮሚቴው አባል አቶ ተድላ ተሾመ በበኩላቸው ድርጊቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው፤ መንግስትም ለተጎጂዎች ሰላም ዋስትና ሊሠጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ እስልምና ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ይህን ጉዳት ያደረሱ አካላት በአፋጣኝ ለሕግ ቀርበው ለጥፋታቸው ፍርድ ማግኘት አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ወር በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግርግር በዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወቃል።(ኢዜአ)

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top