Connect with us

አረንጓዴ አሻራ ከዐጤ ምኒልክ እስከ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አረንጓዴ አሻራ ከዐጤ ምኒልክ እስከ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
Photo: Social Media

ባህልና ታሪክ

አረንጓዴ አሻራ ከዐጤ ምኒልክ እስከ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አረንጓዴ አሻራ ከዐጤ ምኒልክ እስከ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

እንደ መንደርደሪያ
አንድ ዛፍ ቆርጣችሁ፣
ሁለት ካልተካችሁ፣
የተፈጥሮ ጠላት፣
የደን አሸባሪ፣
የሰው ልጅ አዋኪ፣
የተፈጥሮ ፀሯ- ነፍሰ ገዳይ ናችሁ፡፡
(ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ -1994 ዓ.ም. ጀርመን/ሀምቡርግ)

በቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር፣ ነፍሰ ኄር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ይፋ በተደረገው ‘‘ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ’’ ስትራቴጂን ቀርፃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ አገሮችን ቀልብ ከሳበች ሰነባብታለች፡፡

በተለይ ከበለፀጉ አገሮች መካከል ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይና አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች ኢትዮጵያ እየተገበረችው ላለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ድጋፋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ አገራችን የነደፈችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተከትላ በአገር ውስጥ የምታከናውናቸው ሥራዎች የራሷን ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ፣ ለዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና አደጋዎቹን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም በእጅጉ ታምኖበታል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ትልቅ ሚና የነበራቸው አገሮች ሳይቀሩ እንኳን ሀገራችን ለምታከናውነው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ድጋፋቸውን ለመስጠት የወሰኑት ችግሩ ያስተሳሰራቸውና የጋራ ጥቅም ወደሚያስገኝ መፍትሔ የሚወስዳቸው ሆኖ በማግኘታቸው መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡

ኢትዮጵያ የያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት ነው፡፡ ስትራቴጂው በአንድ ጎን ልማትና ዕድገቷን የሚያፋጥንና ዘላቂነቱን አስተማማኝ የሚያደርግ አካባቢ እንደሚፈጥር ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየት ሁነኛ መፍትሔ ያዘለ ሆኗል፡፡

በ2017 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2025) መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራእይ ሰንቃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ በተለይ አረንጓዴ ልማት ለሕዝቧ የሕልውና እና የኑሮ መሠረት በመሆኑ፣ እየተሠራ ያለው ሥራ ዓለም ጭምር በሞዴልነት እየወሰደና እየሠራበት እንደሚገኝም ነው የዘርፉ ምሁራንና ጥናቶች እያረጋገጡ ያሉት፡፡

አረንጓዴ አሻራ እና እምዬ ምኒልክ

የአገራችን የደን ሀብት ታሪክ በጣም ወደኋላ ብንሔድ የምድሪቱ 120 ሚሊዮን ሄክታር 60 በመቶ በሚሆን ደን ተሸፍኖ እንደነበር ነው የታሪክ ድርሳናት የሚጠቁሙት፡፡ ቀደም ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ1375-1404 አገሪቱን ያስተዳደሩት አፄ ዳዊት የደን እንሳትንና ገደብ የለሽ የአደን ጨዋታን ለመከላከል አገሪቱን ለሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች ጠባቂ ሰው በመመደብ ከፋፍለውት እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይነግረናል፡፡ በተመሳሳይም ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብም የጅባትን ደንና የወፍ ዋሻን ውኃ-በል (watershed) የደን ክምችት እንዲጀመር አድርገው ነበር፡፡ የወጨጫንና የየረር ጋራዎችን በደን በማልማት እንዲሁም ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› በማድረግ አገሪቱን በደን የማልበስ ተግባር በስፋት እንደፈጸሙ ታሪካቸው በስፋት ያወሳል፡፡

የደን ሀብትን ጠቃሚነትን በእጅጉ የተገነዘቡት ዐፄ ምኒልክም፤ ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› የሚለውን እሳቤ አጽንዖት በመስጠትም በዘመናቸው የመጀመሪያውን የደን ሥርዓት መሥርተው ነበር፡፡ ዐጤ ምኒልክ የመጀመሪያውን የደን ሕግ ለማርቀቅም የውጭ አገር ባለሙያዎችን ቀጥረው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ይህም ሕግ ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆን ይደነግጋል፡፡ አገሪቱን በደን ለማልማት ካላቸው ቅንአት የተነሣም በፍጥነት ሚያድጉ ዛፎችን ከሌሎች አገር ያስመጡ ነበር፡፡ ንጉሡ የደን አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለማቋቋም ካላቸው ፍላጎት የተነሣ የውጭ አገር ዜጋም ቀጥረው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሕዝብ የተፈጥሮ የደን ሀብትን እንዲንከባከብ ያበረታቱ ነበር፡፡ ንጉሡ የደን አጠባበቅን በተመለከተ ያወጡት ሕግ ደንን አላግባብ የሚጨፈጭፉ ሰዎችን ንብረታቸውን በመውረስና እስከ ሞትም በሚያደርስ የቅጣት ርምጃ የጠነከረም ነበር፡፡

አረንጓዴ አሻራ እና ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ከደን መመናመንና ከተፈጥሮ ሀብት መራቆት ጋር ተያይዞ አፍሪካና ኢትዮጵያ ያጋጠማቸውን ቀውሶችና ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለአሜሪካና ለምዕራቡ ዓለም በማስረዳትና ባገኙት መድረክ ሁሉ በመሞገት ትልቅ ሚና እንደነበራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አቶ መለስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እስከማለት ድረስ የዘለቁበትና ለምዕራቡ ዓለም ያስተዋወቁት ፓኬጅም የሚጠቀስ ነው፡፡

ይህንኑ ‘የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ’ በማስቀጠል ረገድም ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እንደ አብነትም ዶ/ር ዐቢይ በመዲናችን በአዲስ አበባ ያስጀመሯቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የተፈጥሮ ሀብምት ሆነ የዕፅዋቶችና የደኖች መመናመን ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ ያስገቡት ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ መላው የሀገራቸውን ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ የአረንጓዴ ልማት ዐርበኛ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስኬትን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ባለፈው ዓመት ‘በአረንጓዴ አሻራ’ ዘመቻ በሀገሪቱ ሁሉም ክልሎች በተደረገው የችግኝ ተከላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ትኩረትን የሳበ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁር እስከ አፈ ነቢብ… ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈው የችግኝ ተከላ ዘንድሮም በስፋት ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ/ልማት ሞዴል የማድረግ እንቅስቃሴው የበርካታዎችን ይሁንታንና ድጋፍን እያገኘ መሆኑንንም በስፋት እያስተዋልን ነው፡፡

የደን ሀብቶቻችን ሊያበረክቱ የሚችሉትን እምቅ ጠቀሜታዎችም ግምት ዉስጥ በማስገባት- ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለልጆቹና ለመጪው ትውልድ ሲል በዚህ የአረንጓዴ ዘመቻ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ በተደጋጋሚ ላስተላለፉት ሀገራዊ ጥሪ ከሁለም የማኅበረሰሰብ ዘንድ ተግባራዊ የሆነ ምላሽን እየተቸረው ነው፡፡

በዚህ ረገድም ሀገራችን ኢትዮጵያ በስፋት እያከናወነችው ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ዓምና ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ውሎ በ12 ሰዓታት ውስጥ ከ353.6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመተከላቸው በዓለም በክብረ ወሰንነት መመዝገቡን እናስታውሳለን፡፡ የአገሪቱንና ደንና የአየር ንብረት ይዞታ እንዲያገግም ለማድረግ የታለመው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዘንድሮም ቀጥሏል፡፡ በዚህ ዓመትም የ4 ቢሊየን ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ወሰን የገጠርና የከተማ የመሬት ገፅታን አረንጓዴ ማድርግ ሲሆን፣ ለመርሐ ግብሩም ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ተመድቦለታል፡፡ ከዚህ ውስጥም 45 በመቶው የሕዝብ ተሳትፎ በጉልበት አስተዋፅኦ ማድረግ መሆኑም በመገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡

እንደ ማጠቃለያ

ሀገራችን ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልሚያ ዕድሎች አንዱ የደን ሀብት ሲሆን የደን ሀብቶችንን መጠበቅ፣ ማልማት እና በዕቅድ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚያዊ፣ ሥርዓተ-ምሕዳራዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ጃሬድ ዳይመንድ (Collapse – ዉድቀት በተሰኘ መጽሐፉ) ‘‘የተፈጥሮ ሀብቶቻቸዉን በተገቢዉ መንገድ የማይዙ እና ጥቅም ላይ የማያዉሉ ማኅበረሰቦች ላልታሰበ ሥርዐተ-ምሕዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ፤’’ ይላል፡፡ የደኖች መመናመን፣ የዕፅዋት ዓይነት እና ብዛት መቀነስ፣ የደን ለበስ መሬቶች መራቆት፣ ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለተጠቀሰዉ አደጋ ምክያት መሆናቸዉን ከምድረ ገጽ የጠፉ ማኅበረሰቦች ታሪክ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ከዚህ አደጋ ለመትረፍ ዛፍ መትከል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡

የብዝሀ ሕይወት ሀብትና ሥርዓተ ምሕዳር በፕላኔታችን የሰው ልጅን ጨምሮ ለሌሎች ሕይወት ላላቸው ነገሮች አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ የደን ሀብት/የተፈጥሮ ዕፅዋት የምግብና ሥርዓተ ምግብ፤ የመድኃኒትና የመድኃኒት መቀመሚያ ንጥረ ነገሮች፤ የኃይል ምንጭ፤ ለሰው ልጅ ኑሮ እንዲሁም መንፈሳዊና ቁሳዊ እርካታዎች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ ንጹሕ ውኃና አየር በማስገኘት ረገድም ያላቸው ሚና የማይተካ ሲሆን የተለያዩ አስቸጋሪ የበሽታ ወርሽኞችን ከመከላከልና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ አረንጓዴ ውበትና አረንጓዴ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ ችግኝ መትከል፣ ዕፅዋቶችን መንከባከብ፣ ደኖቻችንን ከጭፍጨፋ መከላከል የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ክረምት ሁሉም ሰው ችግኝ በመመትከልና የተተከሉትንም በመንከባበከብ ለኢትዮጵያና ለመዲናዋ አዲስ አበባ አረንጓዴ ሕይወትና ውበት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል፡፡

የሥነ ሕይወት ባለሙያው ለገሠ ነጋሽ (ፕሮፌሰር) ካጠናቀሩትና በተለያዩ የዓለም ክፍል ኅብረተሰቦች ዘንድ ለዛፎች ልዩ ክብር እንደሚሰጡ በየአገሮቻቸው ምሁራንና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ስለዛፍ፣ ስለ ተፈጥሮ ሀብትና ዕፅዋት ከተነገሩ ቁምነገሮች ጥቂት በመጥቀስ ጽሑፌን ላጠቃል፡፡

“የዛፍ ምስጢሩ ውበቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን ማጫሩ ሕይወትን ማደሱ ነው፡፡’’
“የሠርግ ድግስ ደስታህ ያንድ ቀን ነው፣ ተሾም ተሸለም፣ ደስታህ ያንድ ወር ነው፣ ዛፍ ትከል፣ ደስታህ የዕድሜ ልክ ነው፡፡’’
በዚህ ክረምት ለ“አረንጓዴ አሻራ ቀን’’ ስኬት ዛፍን በተለይም አገር በቀሉን በመትከል ታሪካዊ አረንጓዴ አሻራችንን ለራሳችን፣ ለሀገራችን፣ ለትውልድ ማሳረፍ የምንችልበትን መልካም ዕድል እንጠቀምበት፡፡

ሰላም!!

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top