Connect with us

ግብጻውያንን ነስር በነስር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን

ግብጻውያንን ነስር በነስር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን

ባህልና ታሪክ

ግብጻውያንን ነስር በነስር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን

ግብጻውያንን ነስር በነስር ያደረጉ ኢትዮጵያውያን!

(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

አዎ!.. ግብጻውያን ነስር በነስር ሆነዋል፡፡ እንደዋዛ በጀመሩት የሚዲያ ጦርነት በገዛ ሜዳቸው ሽንፈትን ማስተናገድ ተገደዋል። ከወራቶች በፊት ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ስንሻኮት ግብጻውያኑ ስራ ላይ ነበሩ፡፡ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በአንድ መቆም በመቻላቸው በፕሮፖጋንዳ ጣራ ነክተው የውሸት ዳቦ ሲጋግሩ ታዝበናል፡፡ በሀገር፣ በውጭ ያለው ግብጻዊ ሁሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ ማሰማቱ ብቻ ሳይሆን የእኛም ረጅም ዝምታ ተከልሎ የተደጋገመውን ውሸት እውነት አስመስሎ ኖሯል፡፡ ከረጅም እንቅልፋችን ስንነቃ ግን ግብጻውያኑን በአንድ ጊዜ ሰፍረንባቸው ቀልባቸውን እንደክረምት ጉም ብን አድርገናቸዋል፡፡

በኢትዮጵያውያን በሁሉም የሚድያ ግንባር የተከፈተው ጦርነት መከራከሪያቸውን ሁሉ ፉርሽ አድርጎ እርቃናቸውን አስቀርቷቸዋል፡፡ ከወራቶች በፊት በዚሁ ገጽ ላይ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶቻችንን ትተን በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በአንድ እንድንቆም ያቀረብኩት ተማጽኖ ፍሬ አፍርቶ በማየቴ በግሌ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡

እንደአህራም ያሉ ዕውቅ የግብጽ ሚዲያዎች ጨምሮ አክቲቪስቶችቻቸው የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን በውሸት ትረካ በማጨናነቅ ኢትዮጵያ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የግብጽን ሕጋዊ መብት ረጋጭ ሆና እንድትሳል ብዙ ጥረዋል፡፡ በጠራራ ጸሐይ ዘራፊ አስመስለዋት ኖረዋል፡፡ በተለይ ባለፉት ሶሰትና አራት ወራት ወዲህ ግን ውርጅብኝ መጥቶባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን እውነታ ደጋግመው ማስረዳት ችለዋል፡፡ በትላልቆቹ አለም አቀፍ ሚዲያዎች አንቱታን ካተረፉ የግብጽ ምሁራን ጋር ጭምር እየቀረቡ በውሸት ትርክታቸው የገዛ ሕዝባቸውን የቱን ያህል እየዋሹ እንደኖሩ ፊት ለፊት ቀርበው በተጨባጭ ነግረዋቸዋል፤ ውሸታቸውን አጋልጠዋል፡፡

ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ የግብጽ ሚዲያዎች በማህበራዊ ድረገጾች የሚለቋቸው ዘገባዎችና የውሸት ትርክቶች በዚያው ገጽ ላይ እየገቡ የበሰሉ የተቃውሞ አስተያየቶችን በመስጠት በውሸታቸው አሸማቀዋቸዋል፡፡ በተለይ በአንድ ዘገባ ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች በግምት ከ80 በመቶ በላይ በኢትዮጵያውያን ወገኖች አስተያየት መሞላት የግብጽ ሚዲያዎችን ብቻ ሳይሆን ግብጻውያንን አስደንግጧል፤ ግራም አጋብቶ ከርሟል፡፡

በአረብኛ በትልልቅ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ እየቀረቡ አጥብቀው የሞገቱ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል መሐመድ አልሩሲ አንዱ ነው፡፡ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ በግል እየቀረቡ ምሁራዊ እይታቸውን እያቀረቡ ከሞገቱት መካከል ኢንጅነር መቅደላዊት መሳይ፣ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ይጠቀሳሉ፡፡

እንደእነፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም አይነቱ ደግሞ አሜሪካ በአደራዳሪነት ስም ለግብፅ ያሳየችው ውግንና በመቃወም ለሚመለከታቸው የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ደብዳቤ ጽፈው ሁኔታውን በማስረዳት ገድል ሰርተዋል፡፡

ከጋዜጠኞች መካከል ዩስራ ሲራጅ፣ ኦማር ረዲ፣ ግሩም ጫላ፣ መሐመድ ጠሃ ተወከል፣ ኡስታዝ ጀማል በሽርና የመሳሰሉትን ያደረጉት አስተዋጽኦ ለትውልድ ተሰንዶ የሚቀመጥ ነው፡፡

ከስመጥር ኢትዮጵያዊያን መካከል በእንግሊዝ ሀገር የሚኖረው ባለቅኔ ለምን ሲሳይ፣ አለምቀፍ የፋሽን ባለሙያ ሊያ ከበደ፣ አለምቀአቀፍ የምግብ ባለሙያ ማርከስ ሳሙኤል እና ሌሎችም ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

ወገኖቼ በስም ያልጠቀስኳቸው እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁን ድረስ ስለህዳሴ ግድብ እውነታ ለዓለም መናገራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ግብጻውያኑ የሚዲያ ጦርነቱ መሸነፋቸውን ከወዲሁ ያመኑ ይመስላል፡፡ ያመኑት ግን እውነታውን በመካድ ጭምር ነው፡፡ አረብኛ ተናጋሪ ሞጋቾችን ኢትዮጵያውያን አይደሉም በማለት የተገዙ አረቦች ለማስመሰል ይጥራሉ፡፡ በእንግሊዝኛ የሚሞግቱትን “የመንግስት ተከፋዮች ናቸው” በማለት አጀንዳው የህዝብ ሳይሆን የመንግስት ብቻ ለማስመሰል ክፉኛ እየደከሙ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን በጦርነቱ ተሸንፈዋል፤ ገና ከጅምሩ እጅም ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ!.. በስራችሁ፣ በጥረታችሁ ግብጻውያን ነስር በነስር አድርጋችሁ ውሸታቸውን በአደባባይ ማስጣት በመቻላችሁ ኮርተንባችሃል፡፡ በዚሁ ቀጥሉልን፣ እኛም በእናንተ መመካቱን፣ መኩራቱን እንቀጥላለን፡፡

በያላችሁበት ሰላማችሁ ይብዛ!!

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top