የደመና ኩታ በሚያጣፋው ስፍራ ያረፈው-ታሪካዊው የቁልቢ ገብርኤል፤
———————-
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ዛሬ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረውን የቁልቢ ገብርኤል በዓል በመንፈሳዊ ቱሪዝም ረገድ ወደር ከሌላቸው ከአምስቱ የንግሥ ጉዞዎች አንዱ ነው ይለናል፡፡ ወደ ምሥራቁ የሀገራችን ክፍል በምናብ ይወስደንና እንዲህ ያስጎበኘናል፡፡) (ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)
————————
ዛሬ ወደ ጸሐይ መውጫ ተአምር ነው፡፡ ወደ ምሥራቅ ተጉዘናል፡፡ ከፈንታሌ እስከ አሰቦት ሙቀት ያስጨነቃችሁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ናችሁና አትጨነቁ፡፡ ወደ ደጋማዋ ምድር እየተጓዝን ነው፡፡ ምሥራቃዊቷ ሐረርጌ ምድር የተለየ አየር ከሚሳብባት ስፍራ ነው መድረሻችን፡፡
ከአዲስ አበባ 461 ኪሎ ሜትር ተጉዘን መጥተናል፡፡ ምሥራቅ ሐረርጌ እንደ እርጎ የሚሳብ አየር ባለበት ምድር ላይ ባረፈችው ታሪካዊቷ ቁልቢ ነን፡፡ ቁልቢን ከታሪክ አንጻር ካየናት የበርካታ ኩነቶች ምድር ናት፡፡ ደመና እንደ ጋቢ መከናነብ ብርቋ አይደለም፡፡ እንደ ራስ መኮንን ገለጻ ዘወትር አየሩ ንጹሕ ሣሩ ለምለም የሚባልላት ቁልቢ፡፡
በአራቱ መዓዘን ያለው የክርስትና አማኝ ወይ ተሳልሞታል፤ ወይ በስሙ ይምላል፤ ወይ የቤተሰብ አባሉን ያክል ስሙ እየተነሳ ሲጠራ አድጓል፡፡ በመንፈሳዊ ቱሪዝም በኩልም ብዙዎች ከሀገር ሀገር ለመሳለም የሚንቀሳቀሱበት በዓል በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከብራል፡፡ ወደ ደራ ወንቅሸት ገብርኤል፣ ወደ መንዝ ዘብር ገብርኤል፣ ወደ ሐዋሳ ገብርኤል፣ ወደ ጅማ ብቻ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የሚጓዘው ተጓዥ ቁጥር የለውም፡፡ ቁልቢ ከእነዚህ አንዱና ቀደምቱ ነው፡፡
ስለ ቁልቢ ታሪክ ከጀመርን ሩቅ ይወስደናል፤ እኛ እዛ አንደርስም፡፡ የቁልቢ ታቦት መነሻው ርዕሰ አድባራት ወ ገዳማት አክሱም ጽዮን ናት፡፡ በዮዲት አብዮት ጊዜ ታቦቱ ከአክሱም ጽዮን ታቦት ጋር አብሮ ወደ ዝዋይ ሐይቅ ወደ ታላቋ ደብረ ጽዮን ደሴት መጣ፡፡ ከዮዲት መውደቅ በኋላ ሌሎቹ ታቦታት ሲመለሱ ቁልቢ በዚያው በደብረ ጽዮን ቀረ፡፡
ወደ ዛሬው ቦታ እንዲመጣ ካደረጉት ሰዎች ዋናው የኤርትራ ደብረ ሲና ማርያም ገዳም አገልጋዩ አባ አፀቀ ሌዊ የተባሉ መነኩሴ መሆናቸውን የገዳሙ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በእሳቸው አማካይነት ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በዛሬው ቁልቢ አካባቢ በሚገኙ በጥድና ዝግባ ችምችም ባሉ ሁለት ተራሮች አቅራቢያ ወደ ምትገኝ አንዲት ዋሻ መጥቶ አረፈ፡፡ ይህ ቦታ ቀድሞ ጠፍ ነበር፤ እንደውም በውበቱና በአየሩ መልካምነት ተማርከው አሁን እኔ በቆምኩበት ቦታ ላይ ራስ መኮንን ቤት ሰርተውበት ነበር፡፡ ራስ ማረፊያ ይሉት ነበር ሀረርጌዎች፡፡
የአየሩ ማማር፣ የስፍራው ለምነትና፣ የመልከኣ ምድሩ አቀማመጥ ይለያል፡፡ ቁልቢ የእኛ ዘመን ኪነ ህንጻ ቢሆንም ልቅም ተደርጎ ነው የተሰራው፡፡ አሁን የቆምኩበት ቦታ ለመቆም ምናልባትም ከታህሳስ 18 እስከ 20 አልያም ከሐምሌ 18 እስከ 20 ባሉት ቀናት ለመጣ አይሳካለትም፡፡ ስዕለት ሰሚ ነው የሚባለው ታቦት ቀድሞ ቡልጋ ይኖር ነበር፤ ጠባቂው አባ ዱባለ ይባሉ ነበር፡፡
ራስ መኮንን ቡልጋ የነበረውን ታቦት አስመጡት፤ ሸንኮራ ድረስ ወርደው ነበር የተቀበሉት፤ ታቦቱ በወርሃ የካቲት 1884 ዓ.ም. ቁልቢ ገባ፤ ውብና ዋናው ህንጻ ታህሳስ 1888 ዓ.ም. ተመረቀ፤ በኢጣሊያ ወረራ በቦንብ ተደበደበ፤ አሁን የቆመው ድንቅ ቤተ ክርስቲያን በአጼ ሐይለ ስላሴ በ1933 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የተሰራ ነው፡፡
ከዚያም ቁልቢ ከዳር ዳር ዝናው ናኘ፤ ቁልቢ የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር እሴት ማሳያም ነው፡፡ ቁልቢን የጠበቀው ክርስቲያኑ ብቻ አይደለም፡፡ ቁልቢን ያላስደፈረው በዙሪያው የከበበው ሙስሊሙ ህዝብ ነው፡፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በየአውቶቢሱ ተጭኖ ሀረርጌ ሲከትም ከጭሮ እስከ ድሬደዋ፤ ከላንጌ እስከ ሐረር ምዕመኑን የሚያስተናግደውና ከዓመት ዓመት ወገኑን በስስት የሚጠብቀው ሙስሊሙ ነው፡፡ ቁልቢ እንዲህ ነው፡፡ ሐይማኖት ለምኔ ያለው ኮሚኒስቱ መንግስት እንኳን ጭምር የቁልቢ የስዕለት ኮሚቴ አባል ሆኖ ሰርቷል፡፡
ከድሬደዋ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቁልቢ ኢትዮጵያውያን ተግባቢና ፍቅር ናቸው ያሏቸውን የድሬደዋና ሐረር ነዋሪዎች እንዲተዋወቁ እድል የፈጠረ ነው፡፡ ዛሬ ስለ ምሥራቅ ሀገር ሰዎች የዋህነት የሚያወራው የዳር ሀገር ሰው ሁሉ የት አየህ ብትሉት ለቁልቢ ስሄድ ይላችኋል፡፡