“‘ትህነግ የአማራ ክልል ሕዝብንና መሪዎች አንገት ለማስደፋት እየሠራ ይገኛል’’ – ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ
በአማራ ክልል የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የወቅታዊ ጉዳይ ግምገማና የክረምት ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ ተጀምሯል፡፡
በአማራ ክልል የክልልና የዞን ከፍተኛ መሪዎች የወቅታዊ ጉዳይ ግምገማና የክረምት ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ ተጀምሯል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ‘‘ከአንድ ዓመት በፊት ሀገር፣ ሕዝብና ክልል በሠላም እጦት ምክንያት ወዴት ይሄዳሉ በሚል ማጥ ውስጥ ነበርን፡፡ አሁን የተገናኘነው ግን ክልሉ በሁለት እግሩ ቆሞ አስተዋይ ሕዝብና በሳል አመራር መኖሩን አስመስክረን ነው’’ ብለዋል፡፡
ዛሬ የተቆመበት የክልሉ ሰላም ለሀገር ሰላም የተረፈ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም በየትኛውም ጊዜም ይሁን ሰዓት ጠንካራ ወረዳና ቀበሌ ተፈጥሯል ብሎ መኩራራት እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ኢንቨስትመንት በመሳብ በኩል ብዙ ሥራ ማከናወን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡ በሚፈለገው መልኩ ገቢ እየተሰበሰበ እንዳልሆነና ገቢ መሰብሰብ ካልተቻለ ደግሞ ልማት እንደማይመጣም ጠቅሰዋል፡፡ ሕዝቡን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በማድረግ ማሻገር እንደማይቻልም አስታውቀዋል፡፡
ሁሉም ሰው እስከ ሠራ ድረስ ወንበሩ ላይ የሚቀመጥበት፣ ሲደክም ደግሞ አስረክቦ የሚለቅበትን ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያሻም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል፡፡ የማይሠራ አመራር ከቦታ ቦታ እያሸጋገርን ሕዝቡን ማሻገር አይቻልም ነው ያሉት፡፡
የሥራ ኃላፊዎች ስምሪት አንዱ የመድረኩ መነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ይሆናልም ብለዋል፡፡ እያንዳንዱ ዞንም ሆነ ወረዳ በራስ ገቢ የራስን ወጪ መሸፈን ላይ ትኩረት ሰጥቶና ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አገኘሁ ተሻገር ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የወደፊት ፓርቲ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመከላከል፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ በከተማና በገጠር ወቅታዊና መደበኛ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ፓርቲው የሠራው ሥራ አበረታች ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ለክስተቶች የማይበገር የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎችን መፍጠር ስለመቻሉም አመላክተዋል፡፡ ባለፈው አንድ ወር የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማስመረቅ በተደረገው እንቅስቃሴ የኅብረተሰቡን ተስፋ ማለምለም መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በፈጠረው መዋቅርና ቅንጅት የክልሉን ሠላም ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የሥራ ኃላፊዎቹ ከመድረክ ባለፈ መሬት መርገጥና ተግባር ላይ መገኘት መጀመራቸውንም አመልክተዋል፡፡ ተልዕኮን የሚፈፅም የሥራ ኃላፊ ከወረዳ እስከ ክልል ለመፍጠር ተሞክሮ መሻሻሎች መታየታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የክረምት የግብርና ሥራ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታ እየተመራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም አሁንም በርካታ ፈተናዎች መጋረጣቸውን ኃላፊው አስምረውበታል፡፡ የክልሉን ሰላም የአማራ ሕዝብ ጠላቶች ለማበላሸትና ወደኋላ ለመመለስ በርካታ ሙከራዎች እያደረጉ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡ ሁኔታዎች ተቋቁሞ የሚዘልቅ የድርጅትና የመንግሥት መዋቅር አለመፈጠሩንም አስገንዝበዋል፡፡
የፀረ ለውጥ ኃይሉና የትህነግ ሀገር አፍራሽ እንቅስቃሴ በዋነኝነት ለአማራ ክልል ሕዝቦች ሰላም ትኩረት የሚሻ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡ ‘‘ትህነግ የአማራ ክልል ሕዝብንና መሪዎች አንገት ለማስደፋት እየሠራ ይገኛል’’ ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከ85 በላይ የትህነግ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸውም በአብነት ጠቅሰዋል፡፡
የተጀመረው ሠላም የማስከበር ሥራ ወደኋላ እንዳይመለስ ጠንክሮ መሥራት ካልተቻለ ችግር ላለመከሰቱ ዋስትና እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ‘‘ያለንበት ጊዜ አንድነትን በማጠናከር የአማራ ሕዝብን ህልውና የምናረጋግጥበት፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሠላም የበኩላችንን ድርሻ የምንወጣበት ነው’’ ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ሰላም ሲሆን ኢትዮጵያ ሰላም እንደምትሆን ያረጋገጥንበት ጊዜ በመሆኑ ትልቅ አደራና ኃላፊነት መጣሉንም አስገንዝበዋል፡፡
በውስጥ የጠላትን አጀንዳ ይዘው የሚሠሩ ተልዕኮ ፈፃሚ ኃይሎች በመኖራቸውም በተጠናከረ ሁኔታ ቡድኖቹን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አቶ አገኘሁ አሳስበዋል፡፡
ውጤት የማያመጣ የሥራ ኃላፊን የምንታገልበት፣ ክልሉን በጎጠኝነት ከፋፍለው የጠላቶችን አጀንዳ ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎችን በግልጽ የምንፋለምበት ጊዜ ላይ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ ያለፉት ወራት ሥራ አፈፃፀም በመገምገም ተሞክሮዎችን መቅሰምና ቀጣይ የመልካም አስተዳደር አቅጣጫ ማስቀመጥ ነውም ተብሏል፡፡
(ምንጭ፡-አብመድ)