Connect with us

“ድረሱልን፣ አትርፉን” ለሚል ጥሪ፤ “ስብሰባ ላይ ነን” የሚል ምላሽ

“ድረሱልን፣ አትርፉን” ለሚል ጥሪ፤ “ስብሰባ ላይ ነን” የሚል ምላሽ
Photo: EPA

ህግና ስርዓት

“ድረሱልን፣ አትርፉን” ለሚል ጥሪ፤ “ስብሰባ ላይ ነን” የሚል ምላሽ

“በስንቱ እንቃጠል እናንተ?! የሕይወታችንንና የንብረታችንን ደህንነት ለምን አይነት ሰዎች ውሳኔና አመራር እንደሰጠን ማሰቡ እንዴት ያስፈራል? እንዴት ተስፋ ያስቆርጣል? ከሞትን፣ ከተቃጠልንና ንብረታችን እንዳይሆን ከሆነ በኋላ ሟች ሊቆጥሩ፣ አመድና ፍርስራሽ ሊመለከቱ የሚተጉ ሃላፊዎች ምን ያደርጉልናል?;

ነዳጅና ማቀጣጠያ ጎማ ተሸክሞ ቤትና ንብረትህ ላይ እሳት ሊለቅ በመንጋ የመጣን አካል እንዲከላከሉልህ፣ ከጥቃትና ከጥፋት እንዲጠብቁህ ለሚመለከታቸው የመንግስት ሰዎች “ድረሱልን፣ አትርፉን” ስትል “ስብሰባ ላይ ነን” ተብሎ ስልክ ሲዘጋብህ…..እና ቤት ንብረትህ ያለ ሃይ ባይ እየተዘረፈና በእሳት እየጋየ፣ መንግስት ባለበት ሀገር፣ የሚደርስልህ መጥፋቱን ስታውቅ እንዲህ ያለው ጥያቄ እየደጋገመ ያቃጭልብሃል፡- ስብሰባ ምንድነው? የመሰብሰብ ፋይዳውስ?

የእኛ ሃገር ሃላፊዎች ዋና ስራቸው የሚመስላቸው ስብሰባ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ሌላውም ሰው እንደሚረዳው፤ የምንሰበሰበው የሚጠበቀውን ግብ በተሻለና በተቀናጀ መንገድ ለመድረስ ወይም ለማሳካት ነው፡፡ ሃሳብ ተለዋውጦ፣ የስራ ድርሻ ተከፋፍሎና ተናብቦ የተፋጠነ ውጤት ለማስገኘት ነው:: እንጂ ልንጠብቀውና ልናድነው የሚገባ ንብረትና የሰው ሕይወት ከወደመና ከጠፋ በኋላ አመድና ፍርስራሽ ላይ ለመድረስ አይደለም፡፡

በመንጋ የመጣ የጥፋት ኃይል ‘ቆይ ስብሰባ ላይ ነን ስላሉ እስኪጨርሱ ጠብቁ’ ተብሎ እንደማይቆም ማገናዘብ የማይችሉ አመራሮች ያሉን ጉደኛ ህዝቦች እኮ ነን፤ እኛ፡፡ የማወራው በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በጂማ ከተማ የተከሰተውን ሁኔታ ተንተርሼ ነው፡፡ ሰሚ ካለ ግን የኡኡታዬ ጉዳይ ከአንድ ከተማ በላይ የሚሻገር ወሰነ ሰፊ ችግር ነው፡፡ በጂማ ከተማ ከፍተኛ የሚባለው ውድመት የደረሰበት የዶሎሎ ሆቴል ባለቤት አቶ ፀሐይ አበበ በሚዲያም እንደገለፁት፤ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ገና አራት አመት ገደማ የሆነው ይህ ሆቴል፤ ለከተማዋ አይን የሚባል ነበር፡፡ የዶላሩ ዋጋ ዛሬ ካለበት በግማሽ ያህል የወረደ በነበረበት ወቅት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ገንዘብ የፈሰሰበት ሆቴል፤ የረባ ሲኒማ ቤት እንኳን ለሌላት ከተማ አራት መቶ ወንበሮች ያሉት እጅግ ዘመናዊ ሲኒማ ቤትን ጨምሮ ከሰባ በላይ አልጋዎችንና ስፓን አካትቶ የተገነባ ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል ነበር፡፡ የዚያ ሆቴል መኖር ለባለቤቱ ካለው ጥቅም በላይ ለከተማዋ ስምና መነቃቃት ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሆነ ከተማዋን የሚያውቅ ሁሉ ይመሰክራል፡፡ በእርጅናና በመዘንጋት ውስጥ ስትዋልል ለኖረች ከተማ፤ ንቃትና መታወሻ እንደሆናትም አለመመስከር አይቻልም፡፡

ሆኖም ጂማ እንደነ አቶ ፀሐይ ያሉ ንብረታቸው እየወደመና በስጋት እየሸሹም “ጂማን እወዳታለሁ”፣ “ጂማ ከተማዬ ናት የተቃጠለችው” የሚሉ በአዚማም ፍቅሯ የናወዙ ሰዎች (ነዋሪዎች) ቢኖሯትም፤ በሚያስቡላትና በሚጨነቁላት የመንግስት ሃላፊዎች በኩል ግን የታደለች አይደለችም:: አዋራ ከለበሱ፣ ዝገት ካጠቆራቸው ቆርቆሮዎች፣ በላስቲክና በድንጋይ ክምር ከተደጋገፉና ከተወታተፉ የመንገድ ዳር ጎስቋላ ቤቶችና ሱቆች ሳትላቀቅ ለዘመናት የምናያት “የእኔ” ብሎ ከራሱ ከፍታና የኪስ ሙላት ባሻገር ከፍ ሊያደርጋት የሚተጋ መሪ በማጣቷ ነው፡፡

ዛሬም የሆነው ከዚህ የተለየ አይመስለኝም፡፡ አንድ የሚመለከተው አካል “ሆቴሌን ሊያቃጥሉት ነውና ድረሱልኝ” ሲባል “ስብሰባ ላይ ነን” የሚል ምላሽ የሚሰጠው ከምን በመነጨ ነው? የስብሰባው መዳረሻ ውድመቱ ነው ወይንስ ውድመቱን መከላከል? ማንም ባለ ጤነኛ አእምሮ የሆነ ሰው እንደሚገምተው፤ በዚያን እለት የሚደረግ ስብሰባ፤ ስለ መከላከሉ ወይንም ስለ ወቅቱ ሁኔታ ነው ሊሆን የሚገባው:: እንዲያ ከሆነ ደግሞ ከበር ለደረሰ አጥፊ ለጊዜው የመመለስ፣ የመከላከል ትዕዛዝና ስምሪት እያደረጉ ስብሰባው መካሄድ የማይችለው በምን የተነሳ ነው? የነገሮችን አዝማሚያ ተከትለን መልሱን እንገምት ካልን፣ መድረሻችን ሌላ ነውና የሚሆነው ግዴለም መልሱን እንተወው፡፡ ግን ዝም ብለን እንጠይቅ፡፡ የስብሰባው ስፍራ የትም ይሁን የት እንደው ከከተማው ምክር ቤትና ከዋናው ፖሊስ ማዘዣ (ጣቢያ) እንኳን ብንነሳ እስከ ዶሎሎ ሆቴል ያለው ርቀት ከአስራ አምስትና ሃያ ደቂቃ በላይ የሚወስድ ሆኖ ነው አመድ ላይ የደረሱት? ወይንስ ጉዳዩ በስብሰባው ላይ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ በድምፅ ብልጫ ተወስኖ ነው?

በስንቱ እንቃጠል እናንተ?! የሕይወታችንንና የንብረታችንን ደህንነት ለምን አይነት ሰዎች ውሳኔና አመራር እንደሰጠን ማሰቡ እንዴት ያስፈራል? እንዴት ተስፋ ያስቆርጣል? ከሞትን፣ ከተቃጠልንና ንብረታችን እንዳይሆን ከሆነ በኋላ ሟች ሊቆጥሩ፣ አመድና ፍርስራሽ ሊመለከቱ የሚተጉ ሃላፊዎች ምን ያደርጉልናል? መቅደም ያለበትን ማስቀደም የማይችሉ፣ ያለ ስብሰባና የበላይ አካል ቀጭን ትዕዛዝ ባላቸው የሃላፊነት ደረጃ ይበልጡንም ሰዋዊ ስሜት ሕዝብን ሊጠብቁና ሊከላከሉ የማይንቀሳቀሱ አመራሮች ለምን ያስፈልጉናል? ሰዎቹ ከዚህ የለቅሶ ደራሽነትና የሃዘን መግለጫ አውጪ ኤክስፐርትነት የሚላቀቁት መቼ ነው? ኧረ ሰው ጠማን! ሰው ራበን! አንዳንዴ እንኳን ከአዛዥና ታዛዥ ተዋረዳዊ ትብታብ ወጥቶ ስለ ሰብአዊነትና ስለ ሰው ደህንነት ሲል በራሱ ውሳኔም ቢሆን እርምጃ የሚወስድ ሰው! በገዛ ህሊናዊ መመሪያና ትዕዛዝ ጭምር የሚመራ ሰው!

እኔ የምለው ከስብሰባ በፊት የሚወሰድ ህይወትና ንብረትን ከጥፋት የመከላከል እርምጃ ወንጀል ሆኖ ያስጠይቅ ይሆን እንዴ? ግን ማን ሊመልስልኝ ነው ይህን ሁሉ የምጠይቀው? እንደው ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆን ቢችል እንኳን የሚለውን ለመጨመር እንጂ ያለ ስብሰባ የመወሰን፣ ያለ መመሪያ እርምጃ የመውሰድ አቅሙም ድፍረቱም በሌላቸው እንደተሞላንማ ግልፅ ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በየቦታው የምንሰማና የምናያቸው ጥፋቶችና ወንጀሎች ተደላድለው ባልነገሱብን ነበር፡፡ ሁሉም በየደረጃው ለህዝብ ንብረትና ህይወት ያለ አድልዎ፣ ያለ ልዩነት የመወሰን ብሎም የመጠየቅ ግዴታና ሃላፊነት ቢኖርበት ኖሮ እንዲህ ባልሆንን ነበር፡፡ በዘር፣ በፓርቲ በገለመሌ ተሰብስቦ ከመተሻሸትና ከመወሻሸቅ ይልቅ እንደ ግለሰብ ራስን ችሎ በመቆም ብቃታቸው፣ ሃላፊነት በመውሰድ ብሎም በመጠየቅ ወኔና ድፍረታቸው ወደ ስልጣን የወጡ የመንግስት አመራሮች ቢሆኑ ኖሮ ለዚህ ባልበቃን ነበር፡፡

ማንም እንደ ግለሰብ መቆም፣ ማሰብ የማይችል፣ ፈሪና አቅመ ቢስ ሁሉ ነው ሀገር ለማመስ በቡድን፣ በዘር፣ በፓርቲ የሚወሸቀው:: የእንደዚህ አይነት ፈሪዎች ሴራና ዱላ ደግሞ ለነጥሎ መጠየቅ፣ ለለይቶ መምታት ስለማይመች ጥፋቱ ሁሌም አደገኛ ነው:: ልፋትና ተስፋን፣ እምነትና ፍቅርን ሳይቀር ያሳጣል፡፡ የጂማው ባለሃብት ላይ የደረሰው ይሄው ነው፡፡ ሌላው የረሳትን፣ የሸሻትን፣ ሰርቶ ያገኘውን ገንዘብ ሰብስቦ ወደ ሌላ የሚሄድባትን ከተማ፣ ከተማዬ ብሎ የምትነሳ የምትወሳበትን ከፍ ያለ ነገር ቢያቆም፣ የማይገባ ነገር እንዳደረገ ተቆጥሮ ንብረቱን ማውደም፣ ልፋትና ተስፋውን መና ማድረግ፣ እምነትና ፍቅሩን ገደል መክተት ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ጥፋት ምንድነው የሚገኘው?

ከድርጊቱ ፈፃሚዎች መልሱ እንደማይገኝ ብዙዎቻችን እናምናለን፤ እነሱም አያውቁትምና:: በነጂዎች የሚመራው የወጣት መንጋ እንደ ሰው፣ ህሊናና ማሰብያ አእምሮ እንዳለው ፍጥረት ሳይሆን እንደ መገልገያ ቁስ (መሳሪያ) ሆኖ የተቀረፀና የተሰራ በመሆኑ እንዲያ አድርገው በሰሩት አካላት አብዝተን እናዝናለን:: የሰው ወግ ማዕረግ (ምክንያታዊ ሆኖ ማሰብና ማገናዘብ) ስለ ማጣቱ እንብሰለሰላለን፡፡ ወደ ሰብአዊነት ያልፈጠረበት አውሬነት ተራ ስላወረዱት እንቆጫለን፡፡ በሰሩ፣ በተለወጡና በበለፀጉ ሰዎች እንዲነቃቃና እንዲተጋ ከመሆን ይልቅ እንዲቀናና ለጥፋት እንዲነሳሳ በመደረጉ እንከፋለን፡፡ መሆን እንደሚገባው ሳይሆን እንዲሆን እንደሚፈልጉት አድርገው በሰሩትና እንዳሻቸው በሚነዱት ጨካኞች ገና ወደፊትም እናፍራለን፡፡

ይሄ ሆኖ ነው እንጂ ጤነኛ አእምሮና ንፁህ ልቡና የያዘ ማንም ሰው፣ ለሚኖርበት ከተማና ሃገር ጌጥና ከፍታ የሆነን ነገር ለማጥፋት አይታዘዝም ነበር፡፡ ያንን ሆቴልም ሆነ ሌላውን ማንም ይስራው ማን፣ ለምንኖርበት አካባቢ ተጨማሪ ነገር በመሆኑ ብቻ ሊጠበቅ ነበር የሚገባው:: ለባለቤቱ ኪስ ከሚገባው ጥሬ ገንዘብ በላይ ከተማዋ ተጠቃሚ እንደሆነች ማሰብ አለመቻል ድንቁርና ነው፡፡ እዚያ አካባቢ ላይ በመሰራቱ ብቻ ለአካባቢው ነዋሪ የሚኖረው ፋይዳ ነበር የሚልቀው:: አስፍቶ ለማሰብ፣ አዙሮ ለማየት እድልና አቅም እንዳይኖረን ያደረጉን የፖለቲካ ቁማርተኞቻችን ግን ለሚነዱት ወጣት ይህን አይነግሩትም፡፡ ለራሳቸው አላማ በጭፍን መንዳትን እንጂ ምን እያሳጡት እንደሆነ እንዲያገናዝብ ቀዳዳ እንኳን አይተዉለትም:: የምኞትና የህልም ግንብ እንጂ መሬት የወረደች አንዲት የመንደር ድልድይ ስለ መገንባት አስበው አያውቁምና የተገነባን እንደ ማፍረስ የሚቀላቸው ነገር የለም::

እያፈረሱና እያጠፉ ያሉትን ተቋማት እንኳንና በተግባር በሃሳብ የመገንባት አቅም የሌላቸው ስለመሆናቸው ከጭፍን ተግባራቸው በላይ ማሳያ አያስፈልገንም:: ቀላሉን (ማፍረስን) መምረጥ የቀላሎች መገለጫ ነው፡፡ ወትሮም ለመስራት የማይሞክሩትን ለማፍረስ ይሽቀዳደማሉና:: ከባዱን (መገንባትና ማልማትን) መምረጥ ግን ከፍ ያሉት መታያ ነው:: እነሱ ከ‘እኔ’ አጥር አልፈው ከ‘እኛ’፣ ከብሔርና ሃይማኖት ቆጠራ ርቀው ከሃገር (ከከተማ) ማማ ላይ የቆሙ ናቸውና የድርጅታቸውን መቃጠል ሲገልፁ እንኳን “ከተማዬ፣ ጂማዬ ተቃጠለች” ይላሉ፡፡ “ከእንግዲህ ይህን አይቶ ማን ነው ጂማ ላይ መጥቶ ኢንቨስት የሚያደርገው?” የሚለው ያሳስባቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ጉዳት ውስጥ ሆነው ስለ ጂማ ፍቅር በእንባ ጭምር ይናገራሉ:: ወይ የሰው ከፍታ! በዚህ የመንጋ ዘመን ግራ ተጋብተን ተስፋ እየቆረጥን ላለን፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ማወቁ በራሱ ተስፋ ነውና ይኑሩልን፡፡ ፈጣሪ ያቆይልን፡፡ የእንባቸውን መታበሻ ጊዜም ያቅርብልን፡፡

የዶሎሎ ሆቴልን ባለቤት ንግግርና እንባ ስመለከት “ጂማ እንደ ድመት ልጆቿን ትበላለች” ይል የነበረ አንድ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረ የከተማዋ አርቲስት አባባል ነው ወደ አእምሮዬ የመጣው፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ እላለሁ፤ “ጂማ ተስፋና እድገቷን በማይፈልጉና በሚያጓትቱ ድመቶች እጅ ላይ ወድቃለች”፡፡ ከከተማው ፖሊስ ሌላ የምዕራብ እዝ ጦር ማዘዣ (ስሙን ካልተሳሳትኩ) ባለበት ከተማ፤ ያን የሚያህል ሆቴል እንደ ደመራ ነዶ ማለቁ የሚያፀናልኝ ይህንን እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

ያልተመለሰ ጥያቄ፣ የጎደለብን ነገር አለ የምትሉ እስቲ በስልጡን ወግ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብ ልኬት፤ በግልፅ በአደባባይ ቁሙና በሃሳብ ስትሞግቱ፣ በጥያቄ ስትፈትኑ እንያችሁ፡፡ የሚነግራችሁ ሳታገኙ ቀርታችሁ ከሆነ እንንገራችሁ፡- እየተደበቃችሁና እየተሽሎከሎካችሁ ንብረት ላይ እሳት መልቀቅ፣ ምንም የማያውቀውን ማህበረሰብ መግደል፣ ማስጨነቅና ማሸበር ከተራ ውንብድና ያለፈ የጀግንነት ወግ የለውም፡፡ ሃገር መገንባት፣ ከተማ ማልማት ከፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ፕሮፓጋንዳና ቅዠት በላይ የሆነ ከባድ ሃሳብ፣ ከፍ ያለ ተግባር ነው፡፡ ሰርቶ የማሰራት አቅም ባይኖራችሁ እንኳን የተሰራውን የመጠበቅ አቅም ያጣችሁ እናንተስ አስተዳዳሪዎች ትባላላችሁ? ቀድሞ ‘አይሆንም! ተመለስ!’ ከማለት ይልቅ ከሆነ በኋላ ሺዎችን ሰብስቦ ማሰር የቀለላችሁ እናንተ፣ እንዴት ነው የሕዝብ መሪ የምትባሉት? የአርቲስት ሃጫሉ መገደልን ተከትሎ ሁከትና ግርግር እንደሚፈጠር ገምታችሁ ያልተሰናዳችሁ እናንተ፣ እውነት የህዝብ አስተዳዳሪ ናችሁን? ወይንስ የበግ ለምድ የለበሳችሁ ተኩላዎች?

ከጥያቄዎቼ ጎን ለጎን እንዲህ እላለሁ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ሌሎች የበላይ አመራሮች ሆይ፤ የሹሞቻችሁን ጉያ አራግፋችሁ ፈትሹልን፡፡ እጅ ወደ ላይ አስደርጋችሁ የሸጎጡትን ሁሉ አራግፉልን፡፡ እንደ መሪ ሳይሆን እንደ ግለሰብ ቢደርስባችሁ የማትታገሱትን ነገር እንድንታገስና እንድንሸከም መወትወታችሁን ተዉን:: ይልቅስ ጫካ ከገባው በላይ በሹመት ወንበሮቻችሁ ላይ ተቀምጠው በስብሰባ እያመካኙ፣ ድንገት ሳንዘጋጅ ሆኖብን ነው እያሉ እንዳልሰማ እንዳላየ መስለው በእሳት የሚያስበሉንን፣ በካራ የሚያሰይፉንን የራሳችሁን ጉዶች አፅዱልን፡፡

(የሆነውና እየሆነ ያለው ካንገበገባቸው የጂማ ከተማ ነዋሪዎች አንዱ ነኝ)

ምንጭ:- አዲስ አድማስ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top