Connect with us

የመንግሥት ዝምታ ግን አልበዛም?

የመንግሥት ዝምታ ግን አልበዛም?
Photo: Social Media

ህግና ስርዓት

የመንግሥት ዝምታ ግን አልበዛም?

የመንግሥት ዝምታ ግን አልበዛም?
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

የሰኔ 16 ቀን 2010 የመሰቀል አደባባይ የቦምብ ፍንዳታ እነሆ ሁለት ዓመት ቆጠረ። ወንጀሉ በአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ እየተጣራ መሆኑ ሲነገረን ቢያንስ በአደባባይ ሊፈጀን የቋመጠውን ጠላታችንን እናውቃለን በሚል ተስፋ አድርገን ነበር። ለመሆኑ የምርመራውን ውጤት አሜሪካኖቹ ከምን አደረሱት? መቼም ወንጀል በተሰራ በሁለት ዓመቱ እንዲህ አይነት ጥያቄ መጠየቅ ቀርቶ ማሰብ ከጅል ሊያስቆጥር ይችላል። ግን መንግሥት በዝምታ አፉን ለጉሞ ሲቀመጥ ደጋግሞ ከመጠየቅ ውጭ ምን አማራጭ አለ?

አዎ!..ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አዲስ አስተዳደር ደግፈን ያለምንም ጎትጓች በመሰቀል አደባባይ ሰልፍ የወጣን የትየለሌ ነን። ያ ሰልፍ ግን በቦምብ ፍንዳታ መበተኑ፣ በክስተቱም ሰዎች መሞታቸው መጎዳታቸው የሚያሳዝን ነበር።

ክስተቱ እንደተፈፀመ የአሜሪካው ኤፍ ቢ አይ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በምርመራው ላይ እየተሳተፈ መሆኑንና ውጤቱ ለህዝብ እንደሚገለፅ በመንግሥት ቃል ተገብቶም ነበር። እነሆ ሁለት አመት ሙሉ የኤፍ ቢ አይን ምርመራ የበላው ጅብ አልጮህ አለ። ሌላው ቀርቶ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ላይ ስለተሰጠ ፍርድ የተነገረ ስለመኖሩ በግሌ መረጃ የለኝም። መንግሥት በጉዳዩ ላይ ግልፅ መረጃ ለህዝብ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ የቀረበለትን ጥያቄ በዝምታ ቀርጥፎ በልቶታል።

ግን የአንድ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትርን ያህል የግድያ ሙከራ ተደርጎበት ውጤቱ ባላየ፣ ባልሰማ በዝምታ የሚታለፈው ጥቃት አድራሹ የቱን ያህል ጉልበታም ቢሆን ነው? ደግሞ የእንዲህ አይነት ክስተት መደጋገም በመንግሥት ላይ ዜጎች ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ ቢገፋ ምን ይገርማል?

ሰኔ 16 ቀን 2010 በአደባባይ የግድያ ሙከራ በተደረገ በአመቱ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር እና በአዲስአበባ በሰአታት ልዩነት የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ተሰማ። በክስተቱ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣አቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የመከላከያ ሰራዊት ጀኔራል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሌ/ጀ ገዛኢ አበራ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። የባህርዳሩ በብ/ጀነራል አሳምነው ፅጌ ተመካኘ። የአዲስአበባው ግድያ ማን፣ ለምን አላማ ፈፀመው? የሚለው አሁንም ሆድ ይፍጀው የተባለ መስሏል። የሟች ቤተሰቦች እንዳሉት ከግድያው በላይ የመንግሥት ዝምታ ይጎዳል፣ ያማል።

የሚገርመው በሰኔ 16/2010 እና በሰኔ 15/2011 ግድያዎች ተጠርጣሪ የተባሉ ግለሰቦች ተይዘዋል። አንዳንዶቹ ከእስርም ተፈተዋል። ነገርግን የተፈቱት ሰዎች ከወንጀሉ ነፃ ሆነው ነው? የታሰሩት ሰዎች በእርግጥም ወንጀለኛ ናቸው? ከሆኑስ ምን ተፈረደባቸው? ከጀርባቸው ያሉት አካላት (ማስተር ማይንድ የተባሉት) እነማን ናቸው? የሚለው አሁንም ግልፅ አይደለም፤ አልታወቀም።

እናም መንግሥት በረዥም ዝምታው በህዝብ ላይ የተቃጣ ወንጀል እያድበሰበሰና ወንጀለኞችም እንዳይታወቁ ከለላ እየሰጠ እንዳይሆን ያሰጋል። ይህ ድምዳሜ ስህተት ነው ካለ እጅግ ቢዘገይም ስለእነዚህ ወንጀሎች ግልፅ የሆነ መረጃ ለህዝቡ ሊሰጥ ይገባል።

አዎ!..መንግሥታችን ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን መልስ እስካልሰጠ ድረስ ከተጠያቂነት የሚድን አይሆንም። በዚህ አጋጣሚ በጥቃቱ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ያስተናገዳችሁ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ብርታቱን እንዲያድልልኝ ፈጣሪን እማፀናለሁ።

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top