የጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ መልዕክት!!
~ “ችግኝ ተከላ፣ ኮቪድ19ን ከመከላከል ርምጃ ጋር አብሮ የሚከወን ነው”
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ19 የተያዘ ሰው ከመገኘቱ አስቀድመን፣ የመከላከል ሂደቱን በበላይነት የሚመራ የሚኒስቴሮች ኮሚቴን አቋቁመናል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ፣ ልዩ ልዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው፣ ቫይረሱን የመከላከል እና ሥርጭቱን የመግታት ሥራ በበቂ ዝግጁነት እንዲከናወን እና ተመጣጣኝ መፍትሔዎችን ለመስጠት እንዲቻል ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡
እነዚህ ንዑሳን ኮሚቴዎች ለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን በሀገር ደረጃ በማቋቋም፣ በግለሰብ ደረጃ ቫይረሱን ለመከላከል እንዲቻል ከሚረዱ ግብአቶች አንሥቶ ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያዎችን በመግዛት እና ድጋፍ በማፈላለግ፣ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማሰባሰብ ግብአቶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ቢከሠት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙበትን ምግብ በማከማቸት እንዲሁም፣ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ደንቦችን በማውጣት እስካሁን ሥራቸውን ከውነዋል፡፡
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቢጨምር፣ ሕዝቡ ተገቢው ዝግጅት ሊኖረው እንዲችል ልዩ ልዩ ርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥሩ ጨምሮ በኅብረተሰቡ መካከል መዛመት መጀመሩ የሚስተዋል ነው፡፡
መንግሥት ባለፉት ሦስት ወራት ቫይረሱን ለመግታት እና ሥርጭቱን ለመከላከል ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም፣ እያንዳንዱ ግለሰብ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደ ሆነ ሊስተዋል ይገባል፡፡
የዚህ ዓመት የ #አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መጀመሩ፣ መንግሥት በምንም ዓይነት ዜጎች የጥንቃቄ ርምጃዎችን ቸል እንዲሉ እንደ ፈቀደ ወይም አቋሙን እንዳላላ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም፡፡
የመከላከል ርምጃዎችን በጥብቅ መፈጸም አሁንም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የተቀመጡልንን ቫይረሱን የመከላከል ርምጃዎች ተግባራዊ እያደረግን፣ ምርታማነታችንን መቀጠል እና ግባችንን ማሳካት አለብን፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ቀን ሥራ አይደለም፡፡ መላውን ክረምት የሚከናወን ሂደት ነው፡፡ ተግባራዊነቱም በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ የሚፈጸም ነው፡፡
ስለዚህ፣ በቤተሰብ ደረጃ ርቀታችንን እየጠበቅን የምናደርገው ችግኝ ተከላ፣ ኮቪድ19ን ከመከላከል ርምጃ ጋር አብሮ የሚከወን ነው፡፡ ደግሞም፣ የፈጠራ ሥራን ለሚሠሩ እና ጠቃሚ ሐሳቦችን ለሚያመነጩ ሰዎች እንደ ዕድል ተደርጎ ሊወሰድ ያስፈልጋል፡፡ ሁኔታው የኮቪድ19 መከላከል ርምጃዎችን እየተገበርን እንዴት እና በምን መንገድ 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅዳችንን እንደምናሳካ በርካታ ሐሳቦችን እንዲያፈልቁ የሚጋብዝ ነው፡፡
*በአካል ተራርቀን፤ ንጽሕና ጠብቀን፣ እርስ በርስ ተረዳድተን- ኢትዮጵያን ከኮሮና እንታደግ*