አወዛጋቢው የባሪያ ፈንጋይ ሀውልት እንዲፈርስ ተወሰነ
(ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)
በአሜሪካው ቨርጂኒያ ግዛት የሚገኘው፣የነጮች የበላይነትን የሚያገነው የጄኔራል ሮበርት ሊይ ሀውልት ከተተከለበት የታሪካዊው ሪችሞንድ አካባቢ ተነቅሎ ወደ መጋዘን እንዲወስድ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አስታወቁ ።
እ.ኤ.አ በግንቦት/ሜይ 29/1890 ሪችሞንድ፣ ቨርጂኒያ ውስጥ ከብር ንጥረ ነገር ተቀርጾ የተተከለው በወቅቱ ለጥጥ እና እና መሰል ተክሎች ስራ ማካሄጃ የሰዎች ጉልበትን፣ የጥቁር አሜሪካዊያኖች የባሪያ ንግድን የሚፈቅዱት (ፌደራሊስቶች) የወታደራዊው ክንፍ ሀላፊ የነበሩት ጄ/ል ሮበርት ሊይ ሀውልት በአንዳንድ ተቺዎች ዘንድ የነጮችን የበላይነትን የሚያጎላ፣ ዘረኝነትን እና መከፋፈልን ያሚያጎላ፣ የጥቁሮችን የበታችን የሚያገን ተደርጎ በመውሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙዎችን ሲያውዛግብ ነበር።
የቨርጂኒያ ግዛት አስተዳደሪ (ገቨርነር) ራልፍ ኖርትማን በሰጡት መግለጫ” ቨርጁኒያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ልብ በሉ ይህ የእርስ በርስ ጦርነትን ማካሄድ ሆነ ባርነትን እንደ ፍትህ አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን የውሸት ታሪክን የምንሰብክበት ጊዜ አብቅቷል። ይህ ሃውልት እዚህ መኖሩ ከአለም ዳርቻ ወደ ግዛታችን ለሚመጡ ጎብኝዎች እና ለልጆቻችን የሚያንጸባርቀው መልእክት በጣም የተሳሳተ ነው “በማለት በአካባቢው የመጀመሪያው ትልቁ ሀውልት በክብር ከቦታው ተነስቶ ወደ መጋዝን እንደሚወሰድ ተናግረዋል።የገቨርነሩ ውሳኔን በርካታ ጥቁር አሜሪካኖች፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና ደጋፊዎችን በእጅጉ ያስደሰተ ሲሆን “የረጅሙ ጉዞ የመጀመርያ እርምጃ” በማለት አወድሰውታል።
የቀድሞው የቻርሎቲ ክፍለ ከተማ ሀላፊ የሆኑት ዌስ ቤላሚ” ይህ በአሜሪካ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ የተገንጣዮች፣ የባሪያ ፈንጋዮች መታሰቢያ ሀውልቶች መካከል አንዱ የሆነው የጄ/ል ሮበርት ሊይ ሀውልት እንዲፈርስ መወሰኑ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ነው፣ በስተመጨረሻ ጌሊያድ ገነደስነው”በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።
በቨርጂኒያ ግዛት የዲሞክራቲክ ፓርቲ የህዝብ ተወካይ የሆኑት ጄኒፈር ማክሊናን በበኩላቸው” ይህ አጋጣሚ አንድ ቀን ይከናወናል ብዬ እጠባበቅ ነበር።የተባለው ቀን ደርሶ፣እነሆ ሀውልቱ ከስፍራው ከተነሳ ከትከሻዬ ላይ ትልቅ ሸክም እንደወረደልኝ እና በአግባቡ መተንፈስ እንደምችል እና ቁስሌም እንደሚጠግግልኝ ሆኖ ይሰማኛል” ብለዋል።
አሜሪካውያን እና የተቀረው የአለም ህዝብ የጥቁሩ ጆርጅ ፎሎይድ በነጭ ፖሊሱ ዴሪክ አሳዛኝ አገዳደልን ተከትሎ በሃዘን ላይ በወደቁበት በሰሞነኛው ክስተት የቨርጂኒያው አወዛጋቢ ሀውልት እንዲፈርስ መወሰኑ በአካባቢው ለስላማዊ ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰልፈኞችን በእጅጉ ያስደሰተ ሲሆን የጄ/ል ሮበርት ሊይ ቤተሰቦችም ሳይቀሩ እርምጃውን የተስማሙት መሆኑ ተነግሯል። በተቃራኒው በአንዳንድ ሪፐብሊካኖች እና የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሯል ተብሏል።