የአ/አ እስልምና ጉዳዮች ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት ቅሬታውን ለፓርላማው ገለፀ። (ደብዳቤው ተያይዟል)
***
በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፣
ጉዳዩ፡- ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቀረበውን ባለ 11 ገጽ ሠነድ በጥብቅ ማውገዝን ይመለከታል፣
እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የአገራችን መንግስት ሪፎርም እያካሄደ መሆኑ እና ሪፎርሙም አገሪቱን ከመፍረስ እና ከተለያዩ አደጋዎች በመታደግ ወደ ብልጽግና ጉዞ እንድትጀምር በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተያያዘም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለዘመናት በተለይም ያለፈው መንግስት በህገመንግስቱ እንኳን የሰጠውን መብት በመጨፍለቅ ብሎም መብቱ እንዲከበርለት ሲጠይቅ የተለያዩ አፈና፣ እስራትና ግድያ ደርሶበት በአገራችን ላይ ለውጥ እንዲመጣ የራሱን ፋና ወጊ ድርሻ መጫወቱም የሚታወቅ ነው፡፡ መንግስትም የሙስሊሙን ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄዎች ዘላቂ ምላሽ እንዲያገኙ 9 አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ አቋቁሞ ሚያዝያ 23 ቀን 2011 በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይም በሁሉም ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተፈጥሮ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ስምምነት ከተደረሰባቸው ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕግ ሰውነት በአዋጅ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ ነበር፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕግ ሰውነት በአዋጅ እንዲቋቋም የሚያስችል ሠነድ በዕውቅ የህግ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለመንግስት እንዲቀርብ በጉባኤው ስምምነት በተደረሠው መሠረት ረቂቁ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቦና ጸድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መመራቱ ይታወሳል፡፡ ምክር ቤታችሁም ረቂቅ አዋጁን ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ምርመራ መምራቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሕግ ሰውነት እንዲኖረው ከተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የማሻሻያ ሃሳብ በሚል ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች አማካኝነት ተዘጋጅቶ ለምክር ቤታችሁ እና ለሌሎች ለ11 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች በግልባጭ በማሳወቅ የተላከ ሠነድ መኖሩን በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ከደረሰን መረጃ ለመገንዘብ ችለናል፡፡
ለምክር ቤታቸሁ የቀረበውን ሠነድ በዝርዝር የመረመርነው ሲሆን በአጠቃላይ ይዘቱ መጅሊሱ በአዋጅ የሚቋቋምበትን ሂደት ለማደናቀፍ ያለመ የሚመስል እና ጽንፈኛ ዓላማ ያነገበ ከፋፋይ ሠነድ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ስለሆነም ሠነዱን ሙሉ በሙሉ የምናወግዝ ከመሆኑም በላይ ተቀባይነት እንዳያገኝ እና በረቂቅ አዋጅ የማጽደቅ ሂደት ላይ የቀረቡት ሃሳቦች በምንም አይነት መልኩ ሊካተቱ የማይገባቸው መሆኑን አጥብቀን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ስለዚህ፡-
1) ሠነዱ የቀረበው ከአዲስ አበባ ጥቂት ነዋሪዎች ስም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የከተማው ሙስሊሞች ተጠሪ እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም የአዲስ አበባ ሙስሊም ነዋሪን የሚመለከቱ ጉዳዮች ለመንግስት አካላት በሚቀርቡበት ወቅት በምክር ቤታችን በኩል መሆን ሲገባው ይህንን ሂደት ሳይከተል የቀረበው ሠነድ በመሆኑ ከምክር ቤታችን እውቅና ውጭ መሆኑን እንገልጻለን፣ በቀጣይም እንዲህ አይነት አካሄዶች ህገ-ወጥ በመሆናቸው እርምት ሊወሰድ የሚገባው መሆኑን እየገለጽን በተቋማችን የጀመርነውን ለውጥ በማስቀጠል በዘላቂነት እንዲታረሙ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ እንጠይቃለን፣
2) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም ሆነ በተዋረድ የተቋቋሙት ምክር ቤቶች አጠቃላይ ኢስላማዊ መርህን ተከትለው የሚሰሩ እና መላውን ሙስሊም ማህበረሰብ የሚያገለግሉ እንጂ የተወሰኑ የእምነቱ ተከታዮችን ብቻ ነጥሎ እንዲያገለግል የማይጠበቅበት ሆኖ ሳለ በቀረበው ሰነድ ላይ የአህለ-ሱና ወልጀማዓ አሽዓሪያ-ማቱሪዲያ አስተምህሮትን ብቻ እንዲያስተናግድ ሌሎችን ግን እንዳይቀበል የሚጠይቅ በመሆኑ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይገባው መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡
3) ምክር ቤታችሁ እንደሚገነዘበው ማንኛውም የህግ ማርቀቅ ሂደት እራሱን የቻለ ህጋዊ ሂደትን ተከትሎ የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ተገቢውን የህግ አካሄድ ተከትሎ ያልቀረበ ሰነድ ምክር ቤቱ ሊቀበለው እንደማይገባ እንገልጻለን፡፡
4) የቀረበው ሰነድ ለአንድነት ጠር መሆኑ መገንዘብ ተገቢ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ የአስተምህሮ ልዩነቶችን ወደ ተቋም በማስረጽ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በመከፋፈል እጅግ አስከፊ ታሪካዊ በደል ለመፈጸም እየጣረ ያለ ሠነድ በመሆኑ ከሐሳቡ ጀርባ ያሉ አካላት እያራመዱት ያለውን ስውር ደባ ምክር ቤታችሁ በግልጽ ሊረዳው የሚገባ መሆኑን ማስገንዘብ እወዳለን፣
5) በአጠቃላይ ይህ ሠነድ በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም በማስቀጠል ሂደት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑን በአንክሮ በመገንዘብ ምንም እንኳን ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብት ያላቸው ቢሆንም ይህን ሪፎርም ያጎናጸፋቸውን መብት በማስታከክ እንዲህ አይነቱን ኃላፊነት የጎደለው ሠነድ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ዑለማዎች፣ መሻኢኮች፣ ምሁራን፣ ዳኢዎች፣ የተቋማት አመራችን፣ ወዘተ… ሳያማክሩ በድብቅ እንዲዘጋጅ እና እንዲቀርብ ያደረጉ ግለሰቦች ማንነታቸው ተጣርቶ ተጠያቂም ሊደረጉ እንደሚገባም ለመግለጽ እንፈልጋለን፣
በመጨረሻም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ታሪካዊና ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን በመወጣት፣ መንግስትና ገዢው ፓርቲም ለመርህ ተገዢ በመሆን፣ ከጊዜያዊ እፎይታ ይልቅ ዘላቂ ጠቀሜታን የሚያመጣና የሀገርንና የህዝብን ደህንነት በአስተማማኝ መንገድ በሚያስጠብቅ ሁኔታ በፍጥነት አዋጁ ይፀድቅ ዘንድ ጥያቄያችንን እያቀረብን፤ ሁላችንም በጋራ እና በአንድነት በመተባበር በቀጣዩ ትውልድ ሁሌም በመልካም የሚዘከር ታሪካዊ እና አገራዊ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በዚህ አጋጣሚ በሃይማኖቱ አባቶች ለዘመናት ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ያገኝ ዘንድ መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።
ከሠላምታ ጋር
ግልባጭ፡-
ለኢፌዲሪ የሚኒስትሮች ም/ቤት
ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት
ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት
ለኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስቴር
ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት
ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲሰ አበባ