ታግተው የነበሩ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ በቅረቡ ለህዝቡ ይፋ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታወቀ፡፡
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች መታገታቸው ይታወሳል።
እነዚህን ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ የሚገመግም በፌዴራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአሃዱ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
“ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው ነው” ያሉት ሃላፊው፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ መረጃውን ደረጃ በደረጃ መስጠት በሚገባ መልኩ ለመስጠት ቃል ብንገባም ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ብለዋል።
ጉዳዩ ውስብስብ ከመሆኑም በላይ በጉዳዩ ዘንድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት በመሆኑ ጊዜ ሊወስድ ችሏል ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው 28 ሰዎች ተይዘዋል ብለዋል ።
ለዚህም በማህበራዊ ድረ ገጽ የተሳሳተና ያልሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ እየደረሰው ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፤ “ታግቼ ነበር ተማሪ ነበርኩ ”ብለው በተለያየ መልኩ የቀረቡ ወደ 4 ያህል ተማሪዎች እንደተያዙ ጠቁመዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ለማድበስበስ የሞከሩም ተይዘዋል ብለዋል።
በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቋቋመው ግብረ ሃይል ስራውን ሌት ተቀን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ዝርዝርና የተሟላ መረጃውን በቅርቡ ለህዝቡ ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ንጉሱ በማከልም “እገታው እንዲከሰት ያቀዱ፣ ያቀነባበሩ መረጃ የሰጡና ያሰማሩ የተለያዩ ወገኖች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው” ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ጉዳዩን በማድበስበስ ሌላ መልክ እንዲይዝ በማድረግ በሰፊው እየሰሩ ያሉ ሰዎችና ግለሰቦችም አሉ ብለዋል። ጉዳዩን በመደበኛ መረጃ ለመስጠት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ሲጠናቀቅ ዝርዝሩ ለህብረተሰቡ ይሰጣል ብለዋል።
ጉዳዩ በርካታ አካባቢዎችንና አካላትን አነካክቷል ያሉት አቶ ንጉሱ፤ “የአማራ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፌዴራል ጋር ሆነው እየሰሩ ነው” ብለዋል። በከፊልም ከቤንሻንጉል ክልል የሚያገናኘው ነገርም ስላለ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ግብረ ሃይል፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ 24ኛ ክፍለ ጦርና ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በመሆን ቀደም ብለው በህዳር 25/2012 ተይዘው የነበሩ የአካባቢው ወጣቶች፣ አንዳንድ አመራሮችና እነዚሁ 21 ተማሪዎች ተለቀው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና የከተማዋ ከንቲባ ባሉበት ወደ ዩኒቨርሲቲው መልሰው ከዚያ በኋላ ሌሎች ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተማሪዎች ወጥተው እንደነበር በሰነድም በቦታው ተገኝተን አረጋግጠናል ብለዋል።
በጥቅሉ ሁኔታው የብዙ አካላት ዕጅ ያለበት መሆኑ፣ እጅግ ውስብስብ እንዲሁም በጉዳዩ የሚካሄደው ፍተሻ እንዳይሳካ እግር በእግር በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራበት ቢሆንም አስፈላጊው መረጃ እየተሰበሰበ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በየጊዜው የሚመጡ መረጃዎች ልጆች ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚያሳይ አንዳችም መረጃ የለም ብለዋል አቶ ንጉሱ።
“መንግስት መስራት ያለበትን ስራ እየሰራ ነው” ያሉት አቶ ንጉሱ መረጃዎች ተሰብስቦ ሲጠናቀቅ ለህዝቡ ይፋ እናደርጋለን ብለዋል። #ኢዜአ