Connect with us

የዓባይ ውኃ ሙግት እና ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን

የዓባይ ውኃ ሙግት እና ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን
Egypt’s Pope Tawadros II greets Ethiopia’s Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tawahedo Church in a visit to Egypt in 2015 – Press photo

ባህልና ታሪክ

የዓባይ ውኃ ሙግት እና ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን

የዓባይ ውኃ ሙግት እና ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን

ክፍል- ፩

 

በተረፈ ወርቁ

‘‘በጠንካራ ትስስር ላይ የተመሠረተው የሁለቱ አገሮች (የኢትዮጵያና የግብጽ) ግንኙነት ከዓባይ የሚመነጭ ውኃ የማያቋርጥ የጋራ ሀብት በመሆኑ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተጠቃሚ የሚኮንበት ነው፤ ሁላችንም ከአንድ ዓባይ ውኃ እንጠጣለን፡፡ ይህም በመጣጣምና በመተሳሰር ለመኖር አስችሎናል፡፡ ጥንታዊው ዝምድናችንም ለዘለዓለሙ እንደሚፀና እምነቴ ነው፤”

(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስፓትርያርክ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ)

 

‘‘ኢትዮጵያና ግብጽ እንዲሁም ሁለቱ አኀት አብያተ ክርስቲያናት በዓባይ ወንዝና በሃይማኖት አማካኝነት ጽኑ የኾነ ትስስርና ኅብረትን ፈጥረዋል፤ በክርስትና ሃይማኖት ደግሞ ግብጽ እና ኢትዮጵያ መቼም ሊበጠስ የማይችል የመንፈስ አንድነት መፍጠራቸው- ‘በራስህ ላይ እንዲሆን የማትፈቅደውን በሌላው ላይ እንዲሆን አትፈቀድ፤’ በሚለው ክርስትያናዊ አስተምህሮ መሠረት በዓባይን ውኃ በተመለከተ፤ ሁለቱ ሕዝቦች በሰላም፣ በመተሳሰብና በመፈቃቀድ መርሕ እንደምንቀጥል እምነቴ የጸና ያው፡፡’’

(ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ፓትርያርክ)

 

  1. እንደ መንደርደሪያ

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ በግብጽ መንግሥትና በግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ግብዣ ብፁዓን አባቶችን ያካተተ ልዑካንን በመምራት በግብጽ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት በተመለከተ፤ ዋልአ ሁሴን የተባለች የግብጽ ፓርላመንት ዘጋቢ፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ኤክስፐርትና ተንታኝ፤ ‘‘Egypt Uses Church to Bolster Ties with Ethiopia’’ በሚል ርእስ ሰፋ ያለ ዘገባ አስነብባ ነበር፡፡

 

ዋልአ በዚህ ዘገባዋ የግብጽ መንግሥት ኢትዮጵያ ‘‘የግብጻውያን ሕይወት’’ በኾነው በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን ታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ አማካኝነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሰላማዊ የሆነ ድርድርና ስምምነት እንዲኖር ማድረግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን በሁለቱ አኀት አብያተ ክርስትያናት መካከል ለሺሕ ዘመናት የዘለቀው ግንኙነት ከፍጥረት ማግሥት ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ ይህ ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ትላለች የአፍሪካ ጉዳዮች ኤክስፐርቷ ዋልአ ሁሴን፤ ‘‘ይህ ተፈጥሮአዊ ግንኙነት በኋላም በክርስትና ሃይማኖት ዋልታና ማገርነት ወደ ልዩ መንፈሳዊ/መለኮታዊ አንድነት ማደጉን፤’’ ታብራራለች፡፡

 

ይህን የታሪክ እውነታ መሠረት ያደረጉት የአልሃዛር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የኾኑት ፕሮፌሰር ሼኽ አሕመድ አል ጣይብ በወቅቱ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና ከልዑካኑ ጋር በነበራቸው ቆይታም፤ ‘‘የኢትዮጵያ ሕዝብ የዓባይ ውኃን በመተመለከተ- በሃይማኖትና በታሪክ በጥብቅ በተሳሰረው የግብጽ ሕዝብ ላይ ያልተገባ፣ ከክርስትና ሃይማኖትና ከሰብአዊነት እሴቶች ያፈነገጠ ርምጃ መቼም ቢሆን ይወስዳል ብለን አናስብም፡፡’’ ሲሉ ለቅዱስነታቸውና ለልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ ላይ ያላቸውን በጎ ተስፋ ገልጸውላቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የዓባይ ውኃን በተመለከተ ይህ የግብጽ መንግሥትና የግብጻውያን ሐሳብ/አቋም በየጊዜው ተለዋዋጭ ከመሆኑም ባለፈ፣ ግትር፣ የሚያዝና የማይጨበጥ እየኾነ እንዳለ ለበርካታ ጊዜያት ተስተውሏል፡፡

 

እንደሚታወቀው ከመቼውም ጊዜ በላይ ግብጽና ግብጻውያን ከሰሞኑን ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እያካኼደች ያለውን የታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ የተለመደው የብሶትና የእሮሮ ድምፅ ዳግመኛ ጎላ ብሎ እየተሰማ ነው፡፡ ለአብነትም በሱዳን ካርቱም ከመስከረም 19 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ ግብፅ ባቀረበችው ምክረ ሐሳብ፤ ‘‘የግብፅ የዓባይ የተፈጥሮ ፍሰት በማንኛውም መልኩ ሳይዛባ እንዲቀጥል ጠይቃለች፡፡ ከዚህም ሲያልፍ አንዳችም ጠብታ ውኃ ከግድቡ ራስጌ እንዲነካ እንደማትፈልግም መገለጽዋን፤’’ የመገናኛ ብዙኃን በስፋት ዘግበዋል፡፡

 

በዓባይ ውኃ ጉዳይ ‘‘ከእኔ ውጪ…’’ የሚል አቋም የጸናችው ግብጽ ጉዳዩን ወደ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ድረስ በመውሰድ- ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሩጫዋን ተያይዘዋለች፡፡ በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጋራና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲባል ግብጽ ከግትር አቋሟ ይልቅ በሰላማዊ ድርድር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ተመራጭ መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

 

ይህ አጭር መጣጥፍ የግብጽንና የግብጻውያንን ፈር የለቀቀ ‘‘ዓባይን ውኃ አንድ ጠብታ እንኳን ብትነኩ በዓይኔ መጣችሁ’’ ዓይነት ማሳሰቢያና መሠረት የለሽ እሰጥ-አገባ መሠረት አድርጌ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የዓባይን ውኃ እና የኅዳሴውን ግድብ በተመለከተ የነበራት ታሪካዊ ሚና ነበር? አሁንስ ምን ዓይነት ሚና ልትጫወት ትችላለች? የሚለውን ሐሳብ በጥቂቱ ለማየት ይሞክራል፡፡

 

  1. የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን፣ የዓባይ ውኃ ሙግት እና ግብጽ

የታሪክ መዛግብትና ሊቃውንት የሚነግሩን ታላላቅ የዓለማችን ሥልጣኔዎች መነሻ ወንዞች እንደሆኑ ነው፡፡ በዚህም በዓለማችን ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ከመዘገባቸው ታላላቅ ሥልጣኔዎች (The Great World Civilizations) መካከል የሜሴፖታሚያ፣ የፋርስ፣ የባቢሎን፣ የቻይና፣ የአሲሪያን፣ የግብጽ እና የእኛይቱ ኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች መነሻ ወንዞች እንደሆኑ ልብ ይሏል፡፡ ለእነዚህ ግዙፍ ሥልጣኔዎች ከፍተኛውን ሚና ካበረከቱት ወንዞች መካከል የኤፍራጥስና የጤግሮስ፣ ያንጊቲዝና የቢጫ፣ አማዞን እና ዓባይ/ናይል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የኦሪት መጽሐፍ ጸሐፊ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኤደን ገነትን ስለሚከቡ ወንዞች በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ እንዲህ ገልጾታል፦

 

‘‘… ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤደን ይወጣ ነበር፤ የአንደኛው ስም ፊሶን ነው፤ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፣ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል፡፡’’ (ዘፍ. ፪፥፲-፲፬)፡፡

 

በተለምዶ ‘‘የታሪክ አባት (The Father of History)’’ ተብሎ የሚጠራው ግሪካዊው ሊቅ ሄሮዶቱስ ሰለዓለማችን ታላላቅ ሥልጣኔዎች በጻፈው የታሪክ ድርሳን ውስጥ ግብጽን ‘‘የዓባይ ስጦታ (The Gift of Nile)’’ ሲል ጠቅሷታል፤ ስለኢትዮጵያ በጻፈው የታሪክ ዘገባ ላይም ሰለሀገራችንና ስለሕዝባችን ሲናገር፦ “የተፈጥሮን ውብትና ሀብት የታደሉ፣ የቅዱሳን አማልክት ሀገር፣ ሰዎቻቸው ጥበበኞችና መልከ መልካሞች፣ ወንዞቻቸው በተራራ ላይ የሚፈሱ፣ ለሰው ልጆች ፈውስና መድኃኒት የሚሆኑ ናቸው፤” በማለት ጽፎአል፡፡

 

በርግጥም ሄሮዶቱስ እንዳለው በዓለማችን ረዥሙ የሆነው የናይል ወንዝ፣ በዓለማችን ታሪክ የሰው ልጅ ያለፈበትን እጅግ ታላላቅና ውስብስብ የሆኑ ሥልጣኔዎችን ለተቀረው ዓለም በማበርከት ረገድ ለግብጾች ከባለውለታ በላይ ነው ቢባል ያንሰበታል እንጂ አይበዛበትም፡፡ ጥንታውያኑን አገራት- ኢትዮጵያንና ግብፅን ከሚያስተሳስሩ ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ እውነታዎች መካከል በዓለማችን ካሉ ወንዞች ሁሉ ረጅሙ የሆነው ትንግርተኛው የዓባይ ወንዝና የክርስትና ሃይማኖት (የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማለቴን መሆኑን ልብ ይሏል) በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡

 

በዚህ የታሪክ እውነታ መሠረትነት ጥንታዊውና ታሪካዊው የዓባይ ወንዝ ለሰው ልጆች የዘመናት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ፣ ለአፍሪካውያን ወይም ለጥቁር ሕዝቦች ገናና ሥልጣኔ፣ ታላቅ ታሪክ፣ ግዙፍ ባህልና ቅርስ ሕያው ምስክር ሆኖ የቆመ ወንዝ ነው ብል ከእውነታው እምብዛም የራቅኩ አይመስለኝም፡፡

 

በጥንታውያኑ ግሪካውያን የታሪክ አባቶችና ጸሐፍያን ዘንድ ‹‹የዓባይ ስጦታ››በሚል ቅፅል በምትታወቀው በሀገረ ግብፅ፣ የዓባይ ወንዝ የአምላክ ያህል ሲፈራ፣ ሲመለክና ሲወደስ የቆየ ወንዝ ነው፡፡ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱትም ጥንታውያኑ ግብፃውያን የህልውናቸውና የታሪካቸው መሠረት የኾነውን ዓባይን ‹‹ሀፒ›› የሚል ስያሜ ሰጥተውትና በአማልክቶቻቸው ተርታ ውስጥ አስገብተውት ለዘመናት ሲያመልኩትና ሲሰዉለት እንደነበር ጽፈዋል፡፡ ግብፃውያኑ በዓባይ ወንዝ ላይም የተመረኮዙ ከአሥር ሺሕ የሚልቁ ሥነ-ቃሎች እንዳሏቸውም ይነገራል፡፡ በሟቹ ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙርሲ ዘመን ደግሞ ዓባይ/ናይል በግብጽ ሕግ መንግሥት እንዲካተት ተደርጓል፡፡

 

ይህ የሰው ልጆችን ወይም የአፍሪካውያንን የዘመናት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ መልክና ቅርፅ በመስጠት ገናና ስም ያለው ዓባይ ወንዛችን በእነዚህ ጥንታዊ በሆኑት አፍሪካውያኑ አገራት ግብፅና ኢትዮጵያ መካከል ትልቅ የሆነ የታሪክ አሻራ አለው፡፡ ይህ ታሪካዊ አሻራ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ የጠነከረና ዘመናትን የሚሻገር እንዲሆን በ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት የመሆን ስፍራንና ክብርን ማግኘቱ ደግሞ በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ሌላ የታሪክ ድልድይ እንዲቆም፣ ሌላ የግንኙነት መስመር እንዲዘረጋ ትልቅ ምክንያት ኾኗል፡፡

 

በዓባይ ወንዝ አማካኝነት የተፈጠረው የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ትስስር የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ መግባት በኋላ ደግሞ እስከእነ ስንክሳሩም ቢሆን ሌላ የሃይማኖትና የታሪክ የቃል ኪዳን ውልን መፍጠር ቻለ፡፡ ከ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን በፊት የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ፣ ቅርስና ሥልጣኔ ልጅ ናት ተብላ የተጠቀሰችው ግብፅ ዳግመኛ ለኢትዮጵያውያን ‘‘የመንፈስ/ሃይማኖት እናት’’ ሆና በታሪክ መድረክ ብቅ አለች፡፡

 

እነዚህ ሁለት ሀገራት ግብፅና ኢትዮጵያ የተሳሰሩበት የሃይማኖት ግንኙነት ዐረባዊቷ ሀገር ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ለምታራምደው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ መሠረት የጣለ መሆኑን የታሪክ ምሁር፣ ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር)፤ ‹‹The Modern History of Ethiopia 1855-1991›› በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-

 

‹‹… በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ታሪክ እንደ ግብፅ ጉልህ ስፍራ የያዘ ኖሮ አያውቅም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ክርስትና ከተቀበለችበት ከ፬ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ በእስክንድርያው ፓትርያርክ የሚሾም ግብፃዊ መኾኑ ያቺን አገር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሪ ተዋናይ አድርጓታል፡፡›› ሲሉ የሁለቱን አገራት ጥብቅ የኾነ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ትስስር በኋለኛዋ ዘመኗ ኢትዮጵያ በሃይማኖት ሰበብ የተለየ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ ይዞ ብቅ እንዳለ ያስምሩበታል፡፡

 

ይህን የታሪክና የሃይማኖት ትስስር ውል እንደያዝን ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን የታላቁን የኅዳሴ ግድብ በተመለከተ ግብፅ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በኩል የተማሕጽኖ ጥያቄ ስታቀርብ ነበር፡፡ በተለይ ግብጻውያን ለሺሕ ዘመናት የኮፕቲክ ግብጽ ቤተክርስትያን ከኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ- የዓባይ ውኃን በተመለከተ በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በኩል ጥያቄያቸውን ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ለማቅረብና ግፊት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራ አድርገዋል፡፡ የዚህ እሳቤ መነሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ከነበራቸው ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት የሚመዘዝ ነው፡፡

 

ወደኋላ ተጉዘን የታሪክ መዛግብትን ስናገላብጥ የቀደሙ ኢትዮጵውያን ክርስትያን ነገሥታትና ገዢዎች የዓባይ ውኃን ከግብጽ የሃይማኖት አባቶች ሊቀ ጳጳሳትን ለማስመጣትና በክርስትያን ግብጾች በእምነታቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው ግፍና መከራ እንደ መደራደሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለአብነትም ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ (ቀዳማይ) በጻፉት ‘‘የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ’’ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፤ ‘‘በዛግዌ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ለመገደብ በተደረገ እንቅስቃሴ የተደናገጡት የግብጽ ገዢዎች የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ የኾኑትን አቡነ ሚካኤልንና አቡነ ገብርኤልን ብዙ ስጦታ አስይዘው ወደ ኢትዮጵያ ልከው ነበር፡፡’’

 

በሌላ በኩልም ግብጻውያን ክርስትያኖች ይደርስባቸው የነበረውን ግፍና መከራ በተመለከተ ዜና የደረሳቸው፣ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ለግብጽ ሱልጣን/ገዢ በመልእተኞቻቸው በኩል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልከውላቸው ነበር፡፡ ይህን ከስድስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ገዢ/ሱልጣን የላኩትን የማስጠንቀቂቀያ ደብዳቤ በተመለከተ- ጁሊያን ጂ. ፕላንቴ የተባሉ አውሮፓዊ ምሁር፤ ‘‘The Ethiopian Embassy to Cairo of 1443 A Trier Manuscript of Gandulph’s Report, with an English Translation’’ በሚል ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ባቀረቡት ጥናታዊ ድርሳናቸው ለንባብ አብቅተውት ነበር፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃም ይህ ኢትዮጵዊው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለግብፁ ሱልጣን የላኩትን ደብዳቤ በሮም፣ ቫቲካን በብሎቲክ ቤተ-መጻሕፍት በማይክሮ ፊልም ቁጥር MS 477 fol. 251r- 252v ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ስድስት መቶ ዓመታት ያስቆጠረውን፣ ኢትዮጵዊው ንጉሥ ዐፄ ዘርዓያዕቆብ ለግብጽ ሱልጣን የላኩትን የማስጠንቀቂያና የማሳሰቢያ ታሪካዊ የደብዳቤ፤ ‘ከዓባይ ውኃ ሙግት እና ከኢትዮጵያ ቤተክርስትያን አስተዋጽኦ’ አንፃር የሚቃኘውን ተከታይ ጽሑፌን በቀጣይ ልመለስበት እሞክራለኹ፡፡

ይቀጥላል…

ሰላም!

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top