ለገጣሚዎች ስንኙን፣ ለአስጋሪዎች ዓሣውን፣ ለገዳማት ደሴቱን ሲቸር የኖረው ሐይቅ የቀበናን ያህል አስታዋሽ አጥቶ እንደ አለማያ ሲሆን… | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ
ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ወደ ጎጃም ያቀናሁበትን ዋነኛ ተግባር በጣና ዙሪያ እየተሸከረከርን የዘጌ ቡናን፣ እንዲሁም በርበሬና ቅመሙን ስንጎበኝ ውለን ወደ ባሕር ዳር ከተመለስን በኋላ… አመሻሽ ላይ ጣና ዳር ተቀምጬ የሮፍናንን ድንቅ ሙዚቃ እያዳመጥኩ ልረሳው የምፈልገውን ነገር አስባለሁ፡፡
አባይን ብከተል ሰጠኝ ለፈርኦን፣
መጨረሻው ሐዘን ያንቺ አፍቃሪ መሆን
አባይ ጣናን ሰንጥቆት ሲያልፍ ከርቀት ይታየኛል፡፡ ሮፍናን ደግሞ እንዲህ ይለኛል፡፡
ሁሉንም በጊዜው- ውብ አርጎ እንደሠራው
አባይ ሲደፈርስ ነው- ጣና የሚጠራው
ግድቡ ከመጀመሩ በፊት ወደ ባሕር ዳር ስሄድ ዓባይን መመልከት የሚያስጠላኝን ያህል ጣና ዳር መገኘት ደግሞ ደስ ያሰኘኝ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አባይ የሚል ሥም የተሰጠው ግዙፍ ጎርፍ ወንዛችን ሳይሆን ችግራችን ሆኖ መኖሩን ስለማምን ነው፡፡ ‹‹ሰከላ የአባይ መነሻ ብቻ ሳትሆን የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ናት›› የሚል አመለካከት ስላለኝ ነው፡፡ ይህ እንከፍ ጎርፍ ያለምንም ልማት አፈራችንን ጭኖ በሸለቆ ውስጥ እየተምዘገዘገ ከአገሩ ከወጣ በኋላ የግብጽን ምድረ-በዳ ደለልና ውሃ ያነጥፍበታል፡፡
ይሄን ካደረገ በኋላ ደግሞ ወላጅ እናቱን ለሚወጉ አማጺዎች ጦር መሳሪያ ጭኖ ይመለሳል፡፡ ምሥር የምትባል እራስ ወዳድ አገር አባይን ያክል ስጦታ ላበረከተችላት አገር ልዩ ጥቅምን በመስፈር ፈንታ ‹‹የኢትዮጵያ እድገትና መረጋጋት ለእኔ ሥጋት ነው›› በሚል አቋም አንድ ጊዜ ሠራዊቷን አዝምታ ስትወጋን፣ ሌላ ጊዜ ጳጳሳቷን እየላከች በተለያዩ ስልቶች ስታዳክመን ኖራለች፡፡ ባንዱ ዘመን ክርስትናን፣ በሌላ ዘመን እስልምናን ወክላ እየቀረበች በአክራሪነት ስብከት ስትመርዘን፣ ብሎም በአማጺ ጥይት ስታስደበድበን ዘመናትን አሳልፋለች፡፡
በመሆኑም ግድቡ እስኪጀመር ድረስ ወደ ባሕር ዳር ስሄድ ጣና መዝናኛዬ፣ አባይ ደግሞ ትካዜየ ነበሩ፡፡ ይሄን ሰላቢ ወንዝ ስመለከተው የመታመም እንጂ የመደመም ስሜት አይሰማኝም ነበር፡፡
አሁን ግን ነገሮች ተገለባብጠው አባይን ስመለከት የሚጎበኘኝ ነገር ተስፋ ሆኗል፡፡
ዛሬም ቢሆን ጣና ዳር ሆኜ ሳስበው የግብጽና የአረብ ሊግ ልጋግ ትዝ ቢለኝም እልክ እንጂ እንደ ድሮው ቁጭት አልተሰማኝም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ውሃ ማልማት ያለበት የግብጽን በረሃ ነው›› የሚለው የአሜሪካ ትዕዛዝ፣ ‹‹ለእኔ ጥጋብ ኢትዮጵያ ትራብ›› በሚል ዘላለማዊ ሕግ የምትመራው የካይሮ መቅበዝበዝ፣ ትናንት በኢትዮጵያ መንግሥት እገዛ የተረጋጋችው ሱዳን ዛሬ ፈርኦኖቹን ለማገዝ መወሰኗ ቢታወሰኝም….
የጦርነት ናፍቆት-
የባሩድ ጭስ ሽታ- ልክ እንደ ትንቦሃ
ውልፍ ላላት አገር
ሸጋ ምክንያት ነው- የግዮን ምንጭ ውሃ፤
በመሆኑም…
ምድር ቀዉጢ ሳትሆን- ሰማይ ሳይታረስ
ግድቡ አፉ ደርቆ- አባይ መቼም አይፈስ›› ብዬ አቋሜን ከመግለጽ ውጭ የተሰማኝ መጥፎ ስሜት የለም፡፡
በሌላ መልኩ ግን ድሮ ከመጠን በላይ የሚያዝናናኝ የጣና ሐይቅ አሁን ላይ ሕመም አዝሎ ነው የጠበቀኝ፡፡ ለዘመናት ለባሕር ዳር ነዋሪ ዓሣውን ሲመግብ፣ ለሞቃታዋማ ከተማ ቀዝቃዛ ንፋሱን ሲቀልብ፣ የሰማይ ስባሪ በሚመስል መልኩ ለጥንዶች ዳንሱን፣ ለብቸኞች መዝናናቱን፣ ለገጣሚዎች ስንኙን፣ ለሙዚቀኞች ዜማውን፣ ለባለሃብቶች ዳርቻውን፣ ለአስጋሪዎች ዓሣውን፣ ለገዳማት ደሴቱን፣ ለቡና ቤቶች ቀጤማውን፣ ለመስኖ መሬቶች ውሃውን…. ሲሰጥ የኖረው ሐይቅ ዛሬ በእንቦጭ ተወርሮ ለመጥፋት ሲቃረብ ያ ሁሉ ውለታው የአንድ ከንቱ ፖለቲከኛ ንግግርን ያህል ርዕስ መሆን አቅቶት መመልከቴ ሊያዝናናኝ ቀርቶ ሕመም ነው የቀሰቀሰብኝ፡፡
ስንቱን ዓለም ያስቀጨን ሐይቅ እንደ ወንድሙ አለማያ ሊሠዋ በሒደት ላይ መሆኑን መረዳቴ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ባሕር ዳር የምትባለው ውብ ከተማ ‹‹እንቦጭ ዳር›› ተብላ ልትጠራ እንደምትችል ማሰቤ፣ ሐይቁ መሃከል ካሉ ደሴቶች ላይ የተመሠረቱ እነዚያ ጥንታዊ ገዳማት ከሆነ ጊዜ በኋላ በጀልባ ሳይሆን በእግር ተጉዘን ልናያቸው እንችላለን ብዬ መስጋቴ የጣናን ውሃ ለመንካት ይቅርና ሐይቁን የምመለከትበት ድፍረት አሳጥቶኛል፡፡
የተሰማኝን ስሜት እንዴት አድርጌ ላስረዳህ?
ባልንጀሩን ከገደለ በኋላ ሬሳውን እንደሚመለከት ነፍሰ ገዳይ፣ የራሱን ጥንታዊ ከተማ በራሱ ታንክ ከደመሰሰ በኋላ ፍርስራሿ ላይ ተቀምጦ እንደሚቆዝም አማጺ… የዚያ አይነት ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡
ያም ሆኖ ታዲያ ጣናን ስመለከት…. መቀመጫውን ባሕር ዳር ላይ አድርጎ ሐይቁን የረሳውን የክልሉን መንግሥት፣ ያን የሚያክል የተፈጥሮ ሐይቅ በእንቦጭ እየተወረረ ባለበት ሰዓት ቀበናን አልምቶ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለመፍጠር የሚተጋውን የፌደራል መንግሥት፣ በጣና ሥም የሰበሰቡትን ገንዘብ እንቦጭን በማጥፋት ፈንታ በምርምርና ጥናት የሚጨርሱትን ቀፋዮች አልወቀስኩም፡፡
ይልቅስ ስለ ጥቃቅን ነገሮች አብዝቼ ስጽፍ ስንት ውለታና ትዝታ ለሰጠኝ ሐይቅ ብዕሬን አስንፌ በመክረሜ እራሴን ነው የወቀስኩት!