ፓለቲካ
የልደቱ “እስስታዊ ባህሪያት”
የልደቱ “እስስታዊ ባህሪያት” | (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የቀድሞ የትግል አጋሬ የነበረው አቶ ልደቱ አያሌው “የሽግግር መንግስት ይቋቋም” የሚል አጀንዳ አንግቦ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እያራገበው ያለው ሃሳብ ነው፡፡ ልደቱ ሰሞኑን የሚያደርገውን መዋከብ በተመለከተ በወቅቱ ያደረብኝን ስሜት “ልደቱ ሆይ! ማንኛውንም አምባገነን እንደማልታገስ ሁሉ ዓይኔ እያየ ሀገሬን ስታፈርስ ዝም አልልህም! ዱሮም ስታገልህ ነበር አሁንም ትግሌን እቀጥላለሁ! … ልደቱ ዱሮም ኢዴፓን አያውቀውም፡፡ ሲጀመር የመዐህድ አባል ነበር፡፡ እንደ አስተሳሰብ የሊበራሊዝምን ፍልስፍና “የጫንበት” ኢዴፓ ሲመሰረት እዚያ የነበርን (ከመዐህድ ያልመጣን) አባላት ነበርን፡፡ እኛ ከአካባቢው ስንጠፋ እነሆ ልደቱ ወደነበረበት መርህ ዐልባ አረንቋ ተመለሰና ያገኘውን ፈረስ መጋለብ ጀመረ… እናም ሰሞኑን ልደቱ እያራገበው ያለው ሃሳብ በመዐህድ መንፈስ ውስጥ ሆኖ ነው እንጂ በኢዴፓ መንፈስ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለመሆኑ ልደቱ የሰሞኑን አስተሳሰቡን እያራመደ ያለው እንደ ግለሰብ ነው ወይስ እንደ ኢዴፓ? … በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ነው ወይስ አቶ ልደቱ?…” በማለት በፌስቡክ ገጼ ላይ ገልጨ ነበር፡፡
የዚያ ማስታወሻዬ ዓላማ ልደቱም ሆነ የኢዴፓ አባላት “ነቃ በሉ” ለማለት ነበር፡፡ ያንን ማስታወሻ የተመለከቱ፤ የራሳቸውን ጩኸት እየሰሙ የሚደሰቱ እፍኝ የማይሞሉ የልደቱ “ደጋፊዎች” በተለያየ የፌስቡክ አካውንት እየተመላለሱ ያለ የሌለ ስድብ አወረዱብኝ፡፡ አሉባልታና የፈጠራ ስም ለጣጠፉብኝ፡፡ አንዳንዶቹ “ተው ልደቱን አትችለውም… ሃሳብ አምጣና ተከራከር” የሚል ምክርና ጥያቄ አቀረቡልኝና ስሜቴን ከመግለጽ በላይ ልሄድበት ወዳልፈለግኩት ገመድ ጉተታ ስበው አስገቡኝ፡፡ እኔም ነገሩን በፌስቡክ ከምናቆመው የ1960ዎቹ ፖለቲከኞች ያደርጉት የነበረው ዓይነት የሃሳብ ፍጭት ማድረግን እንድንለማመድና እንድንማማር በማሰብ ጉዳዩን ወደ ጋዜጣ መድረክ አመጣሁት፡፡
በዚህ አጋጣሚ ልደቱን አይነኬነቱ (ቅዱስ ላም – Holly Cow) አድርጋችሁ ለምታዩት ወዳጆቹ አንዲት ማስታወሻ ጣል አድርጌ ለማለፍ ወደድሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ልደቱ ምሉእ አይደለም፡፡ እንደ ሰው ይሰራል፣ ይሳሳታል፡፡ ስህተት ያለበት የአደባባይ ሰው ደግሞ ይተቻል፣ ይታረማል፡፡ እርሱ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር “አምባገነን ናቸው” እንደሚል ሁሉ እሱም ተለዋዋጭ (እስስታዊ) ባህሪ ያለው መሆኑ ቢነገረው ሊገርማችሁ አይገባም፡፡ የልደቱ አይነኬነት ለጭፍን አድናቂዎቹ ነው እንጂ ለማንኛውም ምክንያታዊ ሰው አለመሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ በአዛኝ ቅቤ አንጓችነት ከማለባበስ ይልቅ በሃሳብ ላይ የተመሰረተ ትችት የበለጠ ለልደቱ ይጠቅመዋልና ይህቺን መጣጥፍ በዚሁ መንፈስ እንያት፡፡ ሌላው ማሳሰብ የምፈልገው ነገር በዚች ጽሁፍ የማተኩረው ልደቱ ሰሞኑን ባደረጋቸው የተሳከሩ ሃሳቦች ላይ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እናም በድክመቱ ላይ ባተኩር ልደቱ ምንም ዓይነት በጎ ነገር አልተናገረም ለማለት እንዳልሆነ አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በቅድሚያ የማነሳው “አንድ ሰው ሀገር ማፍረስ አይችልም” የሚለውን በተመለከተ ነው፡፡ ልደቱ በመንግስት ላይ የጊዜ ገደብ (Ultimatum) በማስቀመጥ፤ “ከመስከረም በኋላ እኔም ጃዋርም “ጠቅላይ ሚንስትር ነኝ” ብለን ማወጅ እንችላለን፡፡ ሰራዊቱ አይታዘዝም…” ማለቱን ስሰማ አንድ ነገር ታወሰኝ፡፡ የቬንዙዌላው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሁዋን ዋይዶ በምርጫ “ተሸነፍክ” ሲባል፤ ራሱን የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰየመ፡፡ የቬንዙዌላን ፖለቲካ በረዥም እጃቸው ማማሰል የሚፈልጉት እነ አሜሪካም ደገፉት፡፡ እነሆ በዚያች ሀገር የተረጋጋ ህይወት እስከ አሁን የለም፡፡ እንዲህ ያለው ተሞክሮ አደገኛ መሆኑን ስለምገነዘብ ነው በፌስቡክ ገጼ ላይ “ልደቱ ሆይ! ማንኛውንም አምባገነን እንደማልታገስ ሁሉ ዓይኔ እያየ ሀገሬን ስታፈርስ ዝም አልልህም!” በማለት የጻፍኩት፡፡ አንዳንድ የልደቱ ጭፍን አድናቂዎች “አንድ ግለሰብ እንዴት ሀገር ያፈርሳል?” የሚል የየዋህ ጥያቄ በማቅረብ ሊሟገቱኝ ሞክረዋል፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ልደቱ አማራጭ ሃሳብ ማቅረቡ ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚሆነው ያቀረበው ሃሳብ መፍትሄ መሆኑ ቀርቶ የለየለት ሀገር አፍራሽ መሆኑ ነው፡፡
አንድ “ተራ ግለሰብ” ሀገር ሊያፈርስ እንደማይችል እንኳን እኔ የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጄ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ልደቱ ከላይ የተጠቀሰውን አስተያየት ዓይኑን እያጉረጠረጠ የተናገረው ብቻውን ሆኖ ባደረገው ቃለ ምልልስ ቢሆን ኖሮ ምንም አልልም ነበር፡፡ አሻሮ ይዞ ወደ ገብስ የተጠጋው ልደቱ ይህንን ሃሳብ የተናገረው “አባቄሮ ጃዋርን” ከጎኑ አስቀምጦ ያውም በOMN ቴሌቪዥን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ “አባቄሮ ጃዋር” ከኦሮሚያ ወጣቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ደግሞ (ዛሬ እዚያ ሁኔታ ላይ መሆኑን ባላውቅም) “ከከበባው” ማግስት በተፈጠረው ሁኔታ ያየን ይመስለኛል፡፡ ልደቱም በልበ ሙሉነት የተናገረው ይህንን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የፖለቲካ “ሀሁ” ለቆጠረ ሰው የተሰወረ አይመስለኝም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው “ጂኒውን ከጠርሙሱ ማስወጣት” በጣም ቀላል ነው፡፡ “ጂኒውን ወደ ጠርሙሱ መመለስ” አስቸጋሪ መሆኑን ግን ከብዙ ሀገራት ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እናም እንዲህ ያለው ነገር በእሳት መጫወት መሆኑን ልደቱም ሆነ በዙሪያው ያላችሁ ልትገነዘቡት ይገባል፡፡
ልደቱ በዶ/ር ዓብይ ላይ ያራመዳቸው ተለዋዋጭ ባህሪያት (Inconsistency)
ዶ/ር ዓብይ አህመድን ከ10 ዓመታት በፊት እንደሚያውቃቸው የተናገረው አቶ ልደቱ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በእርሳቸው ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲያስተጋባ አስተውለናል፡፡ መጀመሪያ ላይ የህዝብ ትግል በተፋፋመበት ወቅት የፋና ቴሌቪዥን ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝቶ፤ በኋላም በመቀሌ ህወሃት ባዘጋጀው መድረክ ላይ በማጥላላት የተቃኘ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ዶ/ር ዓብይ በፓርላማ በተመረጡ ማግስት ደግሞ “ጊዜ ልንሰጣቸው ይገባል፣ ነጥብ የምናስቆጥርበት ጊዜ አይደለም፣ ልናግዛቸው ይገባል…” በማለት ድጋፉን ገለጸ፡፡ ትንሽ ቆይቶ በተጣደፈ ሁኔታ መተቸት ጀመረ… አሁንም ትንሽ ቆይቶ… ዶ/ር ዓብይ ወደ ቢሯቸው ጠርተው ቡና ሲጋብዙትና የኮሚቴ አባል አድርገው ሲሾሙት… በ100 ቀን ስራ አፈጻጸማቸው ላይ “እንዲህ መሆኑን ባውቅ አልተቻቸውም ነበር” አለ፡፡ … ትንሽ ቆየት አለና “የዶ/ር ዓብይ መንግስት አምባ ገነን ለመሆን እንኳ አቅም የለውም” አለ፡፡
አሁንም ትንሽ ቆየት ብሎ (ዶ/ር ዓብይ ፊታቸውን ያዞሩበት ሲመስለው) “ዶ/ር ዓብይ አምባገነን ነው” አለ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ “ይህ መንግስት ሰላም የማስፈን አቅም የለውም፡፡ እየሟሟ የሚሄድ መንግስት ነው… እናም እኛ ያለንበት የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት” ይለናል አቶ ልደቱ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን፤ “ልፍስፍሱ” መንግስት አቶ ልደቱ ሲቀላቀለው “ጠንካራ” የሚሆንበትን ሎጂክ አልነገረንም አቶ ልደቱ፡፡
አቶ ልደቱ ተለዋዋጭ ባህሪውን ያሳየን በዶ/ር ዓብይ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን በተመለከተም ተመሳሳይ ነገር ሲያራምድ ታይቷል፡፡ “ዶ/ር ዓብይ አሥመራ ሲሄዱና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አዲስ አበባ ሲመጡ ዶ/ር ዓብይ የረዥም ጊዜ ህልሜን ስላሳኩት እንባየን መቆጣጠር አቅቶኝ አለቀስኩ” ይላል አቶ ልደቱ፡፡ እዚህ ላይ ልክ ነው፡፡ ልደቱ ማልቀስ ያውቅበታል፡፡ እኔም ሁለት ዋና ዋና የለቅሶ አጋጣሚዎችን ምንጊዜም አስታውሳለሁ፡፡ አንደኛ፤ ልደቱ ከሸዋ ሮቢት እስር ቤት መጥቶ ፍርድ ቤት በቀረበበት እለት ያነባውን እንባ አልረሳውም፡፡ ሁለተኛ በኢዴፓ ጉባዔዎች የአመራር ምርጫ ተደርጎ መመረጡን ካረጋገጠ በኋላ ልደቱ “እኔን ለምን መረጣችሁኝ” ብሎ ሲያለቅ በተደጋጋሚ አይቻለሁ፡፡ (መመረጡን ካልፈለገው እጩ ሆኖ መቅረቡን ለምን እንደማይቃወም እስከ አሁን አልገባኝም)
ሰሞኑን ደግሞ እንባውን የረጨላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “ቁጥር አንድ የኢትዮጵያ ጠላት” መሆናቸውን እየነገረን ነው አቶ ልደቱ፡፡ “ኢሱን ማቀፍ ኃጢያት ነው…” የሚል አስተያየት አሰማን አቶ ልደቱ፡፡ እዚህ ላይ ልደቱ ሁለት ነገሮችን ዘንግቷል፡፡ አንደኛ፤ “በፖለቲካ ዘላለማዊ ወዳጅም ሆነ ዘላለማዊ ጠላት የለም” የሚለውን ለዘመናት የቆየ አባባል ልብ አላለውም፡፡ ሁለተኛ፤ ኢዴፓ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ የሚታገልለትና ልደቱም በጻፋቸው መጽሐፍት ደጋግሞ የጻፈበትን “ብሔራዊ እርቅ” የሚለውን መሰረታዊ ሃሳብ ረስቶት ወይም የትም ጥሎት ጠላትነትን ሲሰብክ መታየቱ ልደቱ ምን ያህል የመርህ ሰው እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው ብየ አስባለሁ፡፡ ይህንን ስሰማ ኢዴፓ ውስጥ ለዓመታት “ብሔራዊ እርቅ” የሚል አጀንዳ አንግበን ስንታገል የነበረው ለይስሙላ ነበር ማለት ነው? የሚል ጥያቄ እንዳነሳም አድርጎኛል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ልደቱን በተመለከተ “ወጥ በሆነ የፖለቲካ ቁመና የማይታይ፣ በገነገነ የሥልጣን ጥም የተለከፈ፣ በድሀ ልጆች ነብስ ቁማር መጫወት የለመደ፣ በእሣት የመጫወት የፖለቲካ የሚያራምድ፣ ከትናንት ለዛሬ መማር የማይችል፣… ሰው ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት ተለዋዋጭ ባህሪያት ያስተዋለ ሰው በልደቱ ላይ እንዲህ ያለ ትችት ቢያቀርብ የሚያስገርም ሆኖ አይታየኝም፡፡ ከባህሪው ወጣ እንበልና ከህገ መንግስት ትርጉምና ከሽግግር መንግስት መመስረት ጋር አያይዞ የሚያነሳቸውን ነጥቦች እንቃኝ፡፡
የሽግግር መንግስት እና ህገ መንግስታዊ ትርጉምን በተመለከተ
“ልደቱ መንግስት የደከመ ሲመስለው ውጥረት መፍጠር ልማዱ ነው” ይላሉ አንዳንድ በቅርበት እናውቀዋለን የሚሉ ሰዎች፡፡ በዚህ ወቅት “የሽግግር መንግስት ካልተመሰረተ ሞቼ እገኛለሁ” በማለት የራሱ ፓርቲ ኢዴፓ ተወያይቶ ያላጸደቀውን ሰነድ ዶ/ር ዓብይ ካልተቀበለኝ የሚለው ለሌላ በጎ ነገር ጓጉቶ ሳይሆን “የሽግግር መንግስት ሲቋቋም አጨቃጫቂ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መልስ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው” ይላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡ እንደኔ እንደኔ ይህ አካሄድ ግን የቂል መንገድ ነው፡፡ ምክንያቱም አንደኛ፤ ሀገሪቱ የጀመረቺውን ህገ መንግስታዊ ስርዓት የሚያፈርስ ነው፡፡ እድሜ ልካችንን ህገ መንግስት እየቀደድን ስንጥል፣ የሽግግር መንግስት ስናቋቁም መኖር የለብንም፡፡ ያለውን ህገ መንግስት ከነጉድለቱ ተቀብለን ራሱ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው አሰራር መሰረት ማሻሻል ነው የሚበጀን፡፡ ሁለተኛ፤ ይህ ህገ መንግስት እንዳይነካባቸው የሚፈልጉ፣ ይህ ከሆነ ግን ሀገሪቱን በመበተን የራሳቸውን መንግስት የማቆም ፍላጎት ያላቸው በቋፍ ላይ ያሉ ክልሎችና የፖለቲካ ኃይሎች መኖራቸውን ልደቱ ሆን ብሎ ይዘለዋል፡፡ እንዲህ ያለው የልደቱ መንገድ ፍፁም አፍራሽ ከመሆኑም በላይ፤ እውነት ይኸ ሰው ኢትዮጵያን ይወዳታል? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡
ህገ መንግስታዊ ትርጉምን በተመለከተ ልደቱ ያለውን ሀሳብ እንይ፡፡ ልደቱ “ህገ መንግስታዊ ክርክር (dispute) በሌለበት ሁኔታ ህገ መንግስታዊ ትርጉም አያስፈልግም” ይላል፡፡ ይሄ ሃሳብ ስህተት ብቻ አይደለም፤ የግንዛቤ ችግርም ሆኖ ነው የታየኝ፡፡ ምክንያቱም ህገ መንግስታዊ ትርጉም የሚሰጠው የትርጉም ችግር ለተገኘባቸው አንቀፆች ብቻ አይደለም፡፡ የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት “ጽንሰ-ሃሳባዊ ምልከታ” (Abstract Review) በሚለው የህግ ጽንሰ-ሃሳብና ተለምዷያዊ አካሄድ መሰረት ህገ መንግስቱ ግልጽ ባላደረጋቸው ጉዳዮች ላይ ትርጉም መስጠት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሰራር በበርካታ ሀገራት ሥራ ላይ መዋሉንም ልንገነዘበው ይገባል፡፡
ልደቱም ሆነ ደጋፊዎቹና የተወናበዱ አንዳንድ ሰዎች ግልጽ እንዲሆንላቸው የህግ ባለሙያዎች ስለ ምክር ቤት መበተን የሰጡትን አስተያየት ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ (ይህንን ሃሳብ ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት መጣጥፌ ውስጥ አካትቼው እንደበር አስቀድሜ ለማስገንዘብ እወዳለሁ) እንዲህ ይላሉ የህግ ባለሙያዎች፡- በሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 58/3 ላይ የተወካዮች ም/ቤት የሥራ ዘመን 5 ዓመት መሆኑና የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት ምርጫ መካሄድ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ከዐቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም በሌላ ሁኔታ በሰዓቱ ሳይደረግ ቢቀር ምን ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ ህገ መንግስቱ ግልፅ መልስ አላስቀመጠም። ከዚህ በተጨማሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመኑ ካበቃ እንደፈረሰ ተቆጥሮ ሀገሪቱ መንግሥት አልባ ትሆናለች ማለት ነው? ወይንስ ጊዜው ቢያልፍም ምርጫ ተደርጎ አዲስ ምክር ቤት ስልጣን እስኪረከብ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ይቀጥላል? ለሚለው ጥያቄ ግልፅ መልስ የለውም ህገ መንግስታችን። እናም ይህ ሁኔታ ትርጉም ያስፈልገዋል ይላሉ የህግ ባለሙያዎች። ከዚሁ ጋር አያይዘን መገንዘብ የሚገባን ሀገሪቱ ያለ መንግሥት ውላ እንድታድር ሕገ መንግስቱ የማይፈቅድ መሆኑን ነው። ህገ መንግስቱ “ስልጣን በመደራደር መያዝ ይቻላል” የሚል አንቀጽ የሌለው መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለ5 ዓመታት ነው” የሚለው አንቀጽ የተቀመጠው “የሥልጣን ዘመንን ለመገደብ” ነው እንጂ በተለያየ ምክንያት ምርጫ በሰዓቱ ሳይደረግ የቀረ እንደሆነ፤ “አዲሱ ምክር ቤት እስኪመረጥ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት እንደፈረሰ እንዲቆጠርና አገሪቱም መንግሥት አልባ እንድትሆን ለማድረግ” ሊሆን አይችልም። በመሆኑም “በሀገሪቱ አዲስ ምርጫ ተደርጎ፣ አዲሶቹ ተወካዮች ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም የመጨረሻዋ ሰኞ በኋላም ቢሆን የመሥራት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት” የሚል እምነታቸውን ይገልጻሉ የህግ ባለሙያዎች። ምክንያቱም “ነባሩ ምክር ቤት ህዝብ የሰጠውን ስልጣን ለማን አስረክቦ ነው የሚበተነው!? ምናልባት የህገ መንግስቱ አርቃቂዎች ይህንን ነጥብ በግልፅ ያላነሱት መልሱ ግልፅ ስለሆነ ነው ብሎ መውሰድም ይቻላል” በማለት ይከራከራሉ የህግ ባለሙያዎቹ።
በእኛ ሀገር ህገ መንግስት መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን የሚያበቃው በሁለት ዓይነት መንገድ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ይኸውም፡- አንደኛው – በመበተን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በምርጫ በመተካት ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚበተነው በአንቀጽ 60 መሰረት ነው። ከዚህ ውጪ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምርጫ አማካይነት በሌላ ምክር ቤት ይተካል እንጂ፤ ‘የስልጣን ዘመኑ አብቅቷል’ ተብሎ የሚበተን ስለመሆኑ በህገ መንግስቱ ላይ አልተደነገገም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ የህግ ባለሙያዎች። በሌላ አባባል “የስልጣን ዘመን ማብቃት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የመበተኛ ምክንያት ሆኖ አልተቀመጠም ማለት ነው። ስለዚህ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ቢጠናቀቅም ምርጫ ተደርጎ የተመረጠው አዲስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን እስከሚረከብ ድረስ ነባሩ ምክር ቤት ሥራውን መሥራት እንጂ አገሪቱን ምክር ቤት አልባና መንግሥት የለሽ አድርጎ መበተን አይገባውም፡፡ ይህንን ለማድረግ ህግ ብቻ ሳይሆን ሞራልም፣ ሎጂክም አይፈቅድም” የሚል አስተያየት ይጨምራሉ የህግ ባለሙያዎች።
የህግ ባለሙያዎችን አስተያየት እዚህ ላይ ላቁምና (ሙግቴ ከልደቱ ጋር ስለሆነ) የኢዴፓን ጉዳይ ላንሳ፡፡ ለአቶ ልደቱ አንድ ጥያቄ ላቅርብ፡፡ የኢዴፓ ምክር ቤት የስራ ዘመን 3 ዓመት ነው፡፡ አቶ ሙሼ ስልጣኑን ለዶ/ር ጫኔ ከበደ ካስረከበበት ጉባዔ ወዲህ (ለ6 ዓመታት?) ኢዴፓ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ ያውቃል? ታዲያ ኢዴፓ ለምን አልተበተነም? ኢዴፓ በምርጫ ቦርድ ለሁለት ዓመታት ገደማ ታግዶ ነበር የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፡፡ ከዚያ ወዲህ ለምን ጉባዔ አላደረጋችሁም? በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው እንደማይሉኝ እርግጠኛ ነኝ! ልደቱ ራሱ “ኢዴፓ ፈርሷል” ብሎ ማወጁንም አስታውሳለሁ፡፡ አንድ አባል “ፈርሷል” ስላለ ፓርቲ አይፈርስም፡፡ አንድ ፓርቲ “ከመስከረም በኋላ መንግስት ይፈርሳል” ስላለም መንግስት ህልውናውን አያጣም! ካለበለዚያ ለአንድ ጉዳይ ሁለት መለኪያ (Double Standard) መጠቀም ይሆናል፡፡ ለአንድ ጉዳይ የሁለት መለኪያ (Double Standard) መጠቀም ነገር ከተነሳ ይህንንም ከልደቱ ጋር አያይዤ ላንሳው፡፡
የሃሳብ መጣረስና “Double Standard”
ልደቱ በአንድ መድረክ ላይ “በህይወቴ የምጠላው ነገር የሽግግር መንግስት የሚባል ነገር ነው፡፡ የሽግግር መንግስት የውድቀት መፍትሄ ነው” ይልና በሌላ የቃለ ምልልስ መድረክ ላይ ደግሞ ስለ ሽግግር መንግስት አስፈላጊነት ያብራራል፡፡ ልደቱ በአንድ በኩል “የሽግግር መንግስት ይመስረት ማለት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው” ይልና፤ እነ ዶ/ር ዓብይ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲወስኑ ግን ስህተት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ አቶ ልደቱ “ይህ መንግስት ሰላም የማስፈን አቅም የለውም፡፡ እየሟሟ የሚሄድ መንግስት ነው” ይለናል፡፡ ይሁን እንጂ፤ እሱ ባቀረበው ሰነድ ላይ ደግሞ አሁን ያለው ገዢው ፓርቲ ይቀጥል ይላል፡፡ ልደቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ላይ ሆነው መስራት እንደማይችሉ ደጋግሞ ይናገራል፡፡ ዘወር ብሎ ደግሞ “የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ተቃዋሚዎች ተሳታፊ መሆን አለባቸው” ይላል፡፡ አሁንም ትንሽ አለፍ ብሎ ደግሞ ገዢው ፓርቲ የጎላ ድርሻ ይኑረው ይላል… “የኢዴፓን ሰነድ አቅርበናል” ይልና ትንሽ ቆየት ብሎ “የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚለውን ሰነድ ያቀረብኩት እኔ ነኝ” ይላል፡፡
“የእኔ ደጋፊዎች ድንጋይ አይወረውሩም፣ እኔ ያለኝ አፍና ሀሳብ ነው…” ይልና፤ ከዚሁ ጋር አያይዞ ሌሎች ኃይሎች ግን ይህንን ሊያስደርጉ እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ በአንድ በኩል ምርጫ ይራዘም ይላል፤ ምርጫው ህገ መንግስታዊ በመሆነ መንገድ ይራዘም ዘንድ “የህገ መንግስት ትርጉም ይሰጥ” ሲባል ግን ይህንን አልቀበልም ይላል፡፡ አልቀበልም ብሎ ቢረጋ ጥሩ ነው፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎ “ምርጫው እንዲራዘም የሚወስነው ኮሮና ቫይረስ ነው” ይላል፡፡ “የምርጫ ዋናው ቁም ነገሩ ሂደቱና ተሳትፎው ነው” ይልና ኢዴፓ ጭምር በተሳተፈበት የምርጫ ሂደት ስልጣን የያዘውን ብልጽግና ፓርቲን ስልጣን ህጋዊነት በማንሳት ያጣጥላል፡፡ በአንድ በኩል በዴሞክራሲ አግባብ በድምጽ ብልጫ መወሰንን “እቀበላለሁ” ይላል፤ በሌላ በኩል እነ ኦነግ፣ ኢዜማ፣… ሌሎች ተቃዋሚዎች ሁሉ “ምርጫው ይራዘም፣ ህገ መንግስታዊ ትርጉም ይሰጥ” ብለው ሲወስኑ ለብዙሃኑ ድምፅ ተገዢ መሆን ሲገባው ብቻውን ወጥቶ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት ይላል፡፡ አሁን ያለው መንግስት ደካማ ነው ይልና የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ አንድ መሆን የማይችሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ብንጨመር ትንሽ ጠንከር ይላል” ይላል…
የልደቱ የተጣረሱ ሃሳቦችና ለአንድ ጉዳይ ሁለት መለኪያ የመጠቀም አካሄዱን በበርካታ ምሳሌዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ ለናሙና ያህል ይኸው ይበቃል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ እንደኔ ዓይነት የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ የሌለ ተራ ዜጋ በየሰዓቱ ሃሳቡን ቢቀያይር ችግር የለውም፡፡ እንደ ልደቱ ያለ “የፖለቲካ ጉሩ” ግን ይህንን ማድረግ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም ተዓማኒነትን ያጣል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሩጫና መዋከብ የወለዳቸው የተፋለሱ ሃሳቦችና ለአንድ ጉዳይ ሁለት መስፈሪያ የመጠቀም አካሄዶች ልደቱ የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ያለ መሆኑን የሚያመለክቱ ሆነው ነው የታዩኝ፡፡ እናም የልደቱን የስነ ልቦና ችግር በተመለከተ ሰፋ አድርገን እንየው…
ልደቱና የስነ ልቦና ቀውስ…
ልደቱ የዛሬ 7 ዓመት በእንግሊዝ ሀገር በትምህርት ላይ በነበረበት ወቅት ራሱን እስከ ማጥፋት ድረስ የተፈታተነው የስነ ልቦና ቀውስ (ድብርት – depression) ተፈጥሮበት እንደነበር “ቴአትረ ቦለቲካ” በሚለው መጽሀፉ ከገጽ 276 – 287 በዝርዝር ገልፆታል፡፡ የተወሰኑ ነጥቦችን ልጥቀስ… “በዚያ ወቅት… እንቅልፍ እምቢ አለኝ፡፡ ቅዠት አስቸገረኝ፡፡ ነጭናጫና ብሶተኛ ሆንኩ፡፡ … ስለ ሰው ልጅ ኑሮና ህይወት፣ ስለ ዓለም… ያለኝ ፍልስፍና ተቀየረ፡፡ ጨለምተኛና ተስፋ ቢስ ሆንኩ፡፡ ስላለፈ የፖለቲካ ህይወቴ በማብሰልሰል ተጠመድኩ፡፡ ራሴን እድለቢስ አድርጌ አየሁ፡፡ ህዝቡ ለምን ከሀዲ አለኝ? ብየ ጠየቅኩ… የከፈልኩት ዋጋ ከንቱና ፋይዳቢስ ሆኖ ተሰማኝ… እንዴት በወሬ ለሚፈታ ህዝብ ወጣትነቴን መስዋእት አደረግኩ? ብየ ጠየቅኩ… በራስ መተማመኔ እንደ ጉም በነነ… የሚጠሉኝ ሰዎች ቆራርጠው ይጥሉኛል የሚል ፍርሃት አደረብኝ… ከብዙ ስቃይ በኋላ ወደ ሀኪም ዘንድ ሄድኩ… የስነ ልቦና ሀኪም ተመደበልኝ… የስነ ልቦና ሀኪሙም አንድ ሰው ድብርት ውስጥ ሲገባ ‘አሉታዊ አመለካከት ይኖረዋል፣ ጥቃቅን ነገሮችን አጋኖ ያያል፣ ዓለም ጠልቶኛል ብሎ ያስባል…’ አለኝ፡፡ መፍትሄው መድኃኒት መውሰድና ማገገሚያ ውስጥ መግባት እንደሆነ ነገረኝ… ማገገሚያ መግባቱን ስላልፈለግኩ መድኃኒቱን ከምክር ጋር ሰጠኝ … ተሻለኝ… ትምህርቴን ጨርሼ ልመለስ ስል ‘ወደ ሀገርህ አትሂድ’ ብሎኝ ነበር ሀኪሙ…” ይላል ልደቱ፡፡ ሰሞኑን ልደቱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ከላይ ከተጠቀሰው የስነ ልቦና ቀውስ ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዛሬም ልደቱ ጤነኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ብሎ ለማሰብ አያስቸግርም? ፍርዱን ለአንባቢ እተዋለሁ፡፡
የልደቱ ቂመኛነት
በበኩሌ ልደቱ ከሚያለማው ዶ/ር ዓብይ ቢያጠፋ እመርጣለሁ፡፡ ለዚህ አባባሌ ምክንያት አለኝ፡፡ ልደቱ የዛሬ 7 ዓመት የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ በነበረበት ወቅት “… ህዝቡ ለምን ከሀዲ ይለኛል? … እንዴት በወሬ ለሚፈታ ህዝብ ወጣትነቴን መስዋእት አደረግኩ?…” በማለት መጸጸቱን ነግሮናል፡፡ ሰው አእምሮውን ሲያመው እውነተኛ ስሜቱን እንደሚገልጽ የስነ አእምሮ ሊቃውንት ይነግሩናል፡፡ እናም ዛሬ ሀገሪቱ በቋፍ ላይ ሆና፣ ህዝቡ በኮረና ቫይረስ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ባለበት ሁኔታ ልደቱ እያሳየው ያለው መዋከብ “ከሀዲ” ያለውን “ህዝብ” ባገኘው አጋጣሚ ለመበቀል አላደፈጠም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡
ሌላው ልደቱ በተደጋጋሚ “ብሔራዊ እርቅ” እያለ ቢናገርና ቢጽፍም በ10 ዓመት የአብሮነት ቆይታየ የተገነዘብኩት ነገር ልደቱ ቂመኛ መሆኑን ነው፡፡ “በፖለቲካ ዘላለማዊ ጠላትም ሆነ ዘላለማዊ ወዳጅ የለም” የሚለውን አባባል ወደ ጎን በመተው ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር የሚያደርገውን እሰጥ አገባ እና ቂም የወለደው የ“ይዋጣልን” 15 ዓመታት የዘለቀ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለአብነት መውሰድ ይቻላል፡፡
ይህንን ቂመኛነቱን በትግል አጋሮቹ ላይ ጭምር በተግባር አሳይቷል፡፡ በልደቱ ምክንያት ከኢዴፓ የለቀቁ ወይም “የተባረሩ” አባላት ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ለምሣሌ፤ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ አንዷለም አራጌ፣ አቶ ብሩ ብርመጂ፣ አቶ ሙሐመድ አሊ፣ አቶ ግዛቸው፣ አቶ ካሳዊ አዲሱ፣ አቶ አበበ ቀስቶ፣ አቶ ዘለሌ ፀጋ ስላሴ… የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዛሬ ልደቱ ኢዴፓ ውስጥ ብቻውን ቀርቷል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው በሁሉም መድረክ ላይ ልደቱ ብቻውን እየተገኘ ፓርቲው አቋም ያልወሰደባቸውን የተለያዩ ሃሳቦች ማንጸባረቁ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ደግሞ (እዚያ ላሉ ልጆች ክብርና ሞራል ስንል ነው እንጂ) ኢዴፓ የልደቱ የግል ኩባንያ (PLC) የሆነ ያህል እንድናስብ እያደረገን ነው፡፡
ህልምና ጥንቆላ…
ልደቱ “ቴአትረ ቦለቲካ” በሚለው መጽሀፉ ከገጽ 117 – 127 ስለ ህልም ይነግረናል፡፡ በዚህም ትረካው አንዲት የማታውቀው ሴት ስለ ልደቱ ህልም ታይና የማታውቃትን አክስቱን በአጋጣሚ ቤተ ክርስቲያን ታገኛትና ተዋውቃት በአክስቱ አማካይነት ቤቱ ድረስ መጥታ ህልሟን ትነግረዋለች፡፡ የህልሙ አጠቃላይ መንፈስ… “ከሰዎች ጋር በአንበሳ አውቶቡስ እንደሚሄድ – አውቶቡሱ መንገድ ላይ ችግር እንደሚገጥመው – ፀጉሩ እንደሚቃጠል – አውቶቡሱ ለገሃር አደባባይ ላይ ሲሽከረከር ዘሎ ወጥቶ በሩጫ ሲያመልጥ የአይጥ መንጋ እንደሚቦጫጭቀው – ያንንም እንሚያመልጥ – በረሀ አቋርጦ የሆነ ቦታ እንደሚደርስ – አይጥ የቦጨቀው ሰውነቱ ድኖ ወደ ከተማ እንሚመለስና እንደሚነግስ…” የሚተርክ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዶ/ር ዓብይ አህመድ 7ኛው ንጉስ እንደሚሆኑ እናታቸው ህልም አይተው እንደነበር ነግረውናል፡፡
የልደቱ “የሽግግር መንግስት ካልተመሰረተ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት እና የዶ/ር ዓብይ “ህገ መንግስታዊ ትርጉም ይሰጥ፣ እኔው አሻግራችኋለሁ” ግብግብ “የሁለቱን ህልሞች” መጋጨት እያሳየን ይሆን? ለማንኛውም… ተማሪ እያለን ተመሳሳይ “ማርክ” ያላቸው ተማሪዎች ተደራርበው 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣… ሲወጡ በብዙ አጋጣሚዎች አይተናል ወይም ሰምተናል፡፡ ልደቱ ይህንን ህልም በምን መልኩ እንደተረጎመው ባላውቅም ሰሞኑን እያደረገው ያለውን “የሽግግር መንግስት ይመስረት” የሚል በድርቅና የተሞላ ሩጫ ሳይ “ተደራርቦ ንጉስ መሆን ይቻላል ብሎ አስቦ ይሆን?” የሚል ጥያቄ ድቅን ይልብኛል፡፡ በሌላ በኩል “አባቄሮ ጃዋርም” ያልነገረን ህልም ይኖረው ይሆናል… ለማንኛውም እናት ኢትዮጵያ ለብዙ “ህልመኞች” ትበቃለች፡፡ ብቻ በየተራ ለመንገስ መጣር ነው፡፡ ካልሆነ እንደ ዘመነ መሳፍንት አንዱን አንግሰን ሌሎቹን ወደ አምባ ግሸን ለመውሰድ እንገደድ ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር አያይዤ ማንሳት ወደድሁ፡፡ ይኸውም፡- ምርጫ 97ን አፈር ድቤ ካስጋጡት ነገሮች አንዱ የቅንጅት አመራር አባላት በህልምና በጥንቆላ ውስጥ መዘፈቃቸው ነበር ብየ አስባለሁ፡፡ አንዳንዶቹ የቅንጅት አመራር አባላት ወደ ቅንጅት የመጡት በዚያ ምርጫ ኢህአዴግ እንደሚወድቅ ጠንቋይ ነግሯቸው የዚያ ታሪካዊ ሂደት ተዋናይ ለመሆንና የሚገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ እንደነበር (አንድ የቅንጅት አመራር ያ ጠንቋይ ነው ጉድ የሰራኝ ማለታቸውን) ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን ከእስር ከወጣ በኋላ “የቃሊቲ ምስጢሮች” በሚል ርእስ በጻፈው መጽሐፍ ጠቅሷል፡፡ ለልደቱ ደግሞ ህልም ከነፈቺው ቤቱ ድረስ መጣለትና ከአይጥ ተርፎ እንደሚነግስ ተነገረው… እነሆ ያንን ህልም እውን ለማድረግ በፖለቲካው መድረክ ራሱን ቋሚ ተሰላፊ አድርጓል፡፡ ልደቱ በህልም የተነገረው እውን እስኪሆን መጠበቅ መብቱ ነው፡፡ መቼስ ህልም አይከለከልም ተብሏል አይደል! ይሁን እንጂ የእርሱ ህልም እውን እንዲሆን ምስኪኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ጭዳ ለማድረግ መዋከብ ተገቢ አለመሆኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
የልደቱ እስስታዊ ባህሪያት
“ልደቱ ትናንት የተናገረውን ዛሬ አይደግመውም” እየተባለ ይታማል፡፡ ይህንንም ባህሪውን አንዳንዶች ከእስስት ጋር ያመሳስሉታል፡፡ እንደሚታወቀው ከእንስሳት ሁሉ “እስስት” የተሰኘቺው ተሳቢ እንስሳ የሚገርም ተፈጥሯዊ ባህሪ አላት፡፡ እስስት ቀይ ነገር ስታይ ቀይ፣ አረንጓዴ ስታይ አረንጓዴ፣ ቢጫ ስታይ ቢጫ፣ ዳለቻ ስታይ ዳለቻ፣… አድርጋ መልኳን በመቀያየርና ከአካባቢዋ ጋር በመመሳሰል ከመጣባት “ጠላት” ለማምለጥ የሚያስችል ተፈጥሯዊ ችሎታ አላት፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው አቶ ልደቱ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ አቋሞችን በማራመድ “የመጡበትን ጠላቶች” ሳይሆን፤ በርቀት የተደረደሩ የፖለቲካ ባላንጣዎቹን ለማቸነፍ ይወራጫል፡፡ በርግጥ የፖለቲካ ባላንጣን ለማቸነፍ የተለያዩ ስልቶችን (ስትራቴጂዎችንና ታክቲኮችን) መጠቀም ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጎምቱ የፖለቲካ ሰው ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብሎ ለዘመናት ሲያራምደው የነበረውን ርዕዮተ-ዓለማዊ መሰረት በመናድ እንደ ማእዘን ድንጋይ የሚታዩ አቋሞቹን እንደ እስስት መቀያየር ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሞት (Political Suicide) ሆኖ ይታየኛል፡፡
ጽሁፌን ላጠቃል፡፡ ኢዴፓ ሲመሰረት ብዙዎቹ መስራች አባላት ብዙም የፖለቲካ ተሞክሮ ያልነበረን፣ እድሜያችን በ20ዎቹ አጋማሽ የሆነ ወጣቶች ነበርን፡፡ ልምድም ተሞክሮም አልነበረንም፡፡ እናም በሂደቱ ብዙ ስህተቶችን ሰርተናል፤ ብዙ መልካም ነገሮችንም አከናውነናል ብየ አስባለሁ፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ጎልማሳዎች ሆነናል፡፡ ከስህተታችን የምንማርበትን ደረጃ አልፈነዋል፡፡ ከስህተታችን ብቻ ሳይሆን እድሜ ብዙ አስተምሮናል፤ ልምድ ብዙ አስተምሮናል፡፡ በትምህርታችንም ገፍተን ብዙ እውቀት አካብተናል፤ በቀሰምነው እውቀት አእምሯችን በልጽጓል፡፡ ከሌሎች ድክመትና ውድቀት ተምረናል፡፡ ከሌሎች ብልጠትና እውቀት ተምረናል፡፡ ልደቱን የማስበው በዚህ ደረጃ የሚገኝ እንደሆነ ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ ተግባራቱ ግን ይህንን የሚያሳዩ ናቸው?
ጽሑፌን የማጠቃልለው ልደቱ በዓባይ ሜዲያ ያደረገውን ቃለ ምልልስ በቋጨበት መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፤ “እኛ የዚህ መንግስት ወዳጅ ነን… የምንተቸው ለዚህ ነው” ይላል፡፡ – አዎ! እኛም የልደቱ ወዳጅ ነን፤ የምንተቸው ለዚህ ነው!!!
ጸሐፊውን Email: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡