“የእርምት እርምጃ በመወሰዱ እናመሰግናለን” – የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር
የወ/ሪት ኤልሳቤጥ ከበደን የፍ/ቤት ሂደትና ጉዳዩ ያለበትን ስለማሳወቅ፡፡
የህግ ባለሙያዋና የኢትየጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አባል የሆነችው ወ/ሪት ኤልሳቤጥ ከበደ መጋቢት 26ቀን 2012ዓ.ም በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዛ ወደ ሀረሪ ክልል ከተወስደችበት እለት አንስቶ ማህበሩ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑ ይታወቃል፡፡
የሀረሪ ክልል ፖሊስ ለ2ኛ ጊዜ የጠየቀባት የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶ መዝገቡ ለ26/8/2012ዓ.ም መቀጠሩ እና የዋስትና አቤቱታውን በተመለከተ ዓ/ህግ በድጋሜ ምላሽ ይስጥበት በሚል ለሚያዚያ 29/2012ዓ.ም መቀጠሩ ይታወሳል፡፡
ሆኖም በችሎት ከተነገረው የቀጠሮ ቀን ውጭ ዓ/ህግ ባቀረበው አቤቱታ መሰረት መዝገቡ ወ/ት ኤልሳቤጥ በሌለችበት ሚያዚያ 22/2012ዓ.ም ቀርቦ ፍ/ቤቱ የ20ሺ ብር ወይም 10ሺ ብር ደሞዝተኛ (የሰው ዋስ) አስይዛ እንድትወጣ ወስኗል፡፡
ምንም እንኳን ዋስትና መፈቀዱ ተገቢ ቢሆንም በተደጋጋሚ ወ/ት ኤልሳቤጥ በሌለችበት በአንድ ጎን ብቻ በሚቀርቡ አቤቱታና ምላሾች በፍርድ ቤቱ ሲሰጡ የነበሩ ትእዛዞች የተጠርጣሪዋን ራሷን የመከላከል መብት ያላከበረና ተገቢነት የሌለው ነው፡፡
ኤልሳቤጥ በዋስትናው አሰጣጥ ላይ የነበረውን ያልተገባ አካሄድ በመቃወም ዋስትናውን ባለመፈጸም በእስር ላይ የቆየች ሲሆን በ26/8/12ዓ.ም በችሎት ቀርባለች፡፡ በእለቱም ዓ/ህግ የክስ መመስረቻ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱ ዓ/ህግ ክሱን አዘጋጅቶ እንዲያቀርብ በሚል እና ወ/ት ኤልሳቤጥም የምታቀርባቸው ማስረጃዎች ካሉ እንድታቀርብ በሚል መዝገቡ ለ29/8/12ዓ.ም ተቀጠረ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀን 28/8/12ዓ.ም ወ/ት ኤልሳቤጥ ከሀረሪ ክልል ወደ አዲስ አበባ እንድትመለስ የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዋስ ተለቃለች፡፡ የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር እንዲሁም የማህበሩ አባልና ጠበቃ በስፍራው በመገኘት ወ/ት ኤልሳቤጥን ተቀብለዋታል።
ወ/ት ኤልሳቤጥ ወደሀረር እንድትወሰድ የተደረገበትን አግባብ ስንቃወም የነበረና በተጠረጠረችው ወንጀልም ምርመራው ሊከናወን የሚገባው ድርጊቱን ፈጸመች በተባለበት ቦታ(ነዋሪ በሆነችበት አዲስ አበባ) ላይ መሆን እንደሚገባው፣ እንዲሁም ክስ የሚያስመሰርት ከሆነም ስልጣኑ የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍ/ቤት በመሆኑ ጉዳዩ በሀረሪ ክልል ላይ ሊታየ እንደማይገባው መግለጻችን ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት የወ/ት ኤልሳቤጥ ጉዳይ ወደ አዲስአበባ እንዲዛወር መደረጉ በአዲስ አበባ ፖሊስና በጠቅላይ ዓቃቢ ህግ በኩል የተወሰደ የእርምት እርምጃ በመሆኑ ለተሰጠው ተገቢ ምላሽ ማህበራችን አድናቆቱን እየገለፀ፤
በቀጣይ የሚኖሩ የምርመራ እና የፍ/ቤት ሂደቶችም በተገቢው የህግ አግባብ እንደሚታዩ ተስፋ እያደረግን ማህበራችን ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ በቅርበት የሚከታተለው መሆኑንም ለማሳወቅ ይወዳል፡፡
ማህበሩ ጉዳዩን በሚከታተልበት ወቅት ስራችንን በማገዝ ለረዱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ የሐረማያ ዩንቨርሲቲ የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከል፤ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ የህግ ባለሙያዎች እና ሚዲያዎች ላቅ ያለ ምስጋናን ያቀርባል።