የቤተ መንግሥቱ ፒኮክ ጉዳይ፤
አንበሳን በፒኮክ መቀየር ወይስ ፒኮክን ከአንበሳ ጋር መደመር፤
ፒኮክና ኢትዮጵያዊነት፤
ከሄኖክ ስዩም /ተጓዡ ጋዜጠኛ/
ሰሞኑን ሰፊ መነጋገሪያ የኾነው የቤተ መንግሥቱ ፒኮክ ጉዳይ ነው፡፡ የሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጲስ ጋዜጣ ላይ አንድ ጸሐፊ ጉዳዩን ሰፊ ትኩረት ሰጥተው ብዙ ነገር ሲሉበት የግል ዕይታቸው መስሎኝ ነበር፡፡ ውሎ አድሮ ማኅበራዊው ሚዲያም “ፒኮክ ለምን?” ማለት ጀምሯል፡፡
ከዚያ በፊት ግን በስሟ መናፈሻ የሰየምንላት፤ ብዙ የንግድ ስያሜዎች በኢትዮጵያ እውን የኾኑባት ፒኮክ ማን ናት የሚለውን በአጭሩ እንመልከት፡፡
ፒኮክ መልከ መልካሟ ወፍ ናት፡፡ Peafowl የሚለው የወል ስማቸው ሲኾን ወንዱ Peacocks ሴቷ ደግሞ Peahens በሚለው ስም ሳይንሱ ይጠራቸዋል፡፡ ፒኮክ ለህንድ ልዩ ትርጉም አላት፡፡ ፓቮ ክሪስታተስ የሚባለው የህንድ የጣዋስ ወፍ የሀገሪቱ ብሔራዊ ወፍ ነው፡፡
ዳክዬ የሚያኽል መጠን ያለውና በቀለማት ህብር ያጌጠው ይኽ ወፍ በህንድ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ተረክ የቆመበት ድንቅ ፍጥረት ነው ይሉታል፡፡ ማራገቢያ የመሰለ ላባ አለው፡፡ ዓይናቸው ስር ነጭ ልጥፍ ነገር ይታያል፡፡ አንገታቸው ቀጭንና ረዥም ነው፡፡ የወንዱ ላባ ከሴቷ ይልቅ ውብ ሲኾን ህብረ ቀለማዊነቱ ይጎላል፡፡ ሰማያዊ ቀለም ያለው ደረቱ ያንጸባርቃል፤ ሴቷ በመጠን ከወንዱ ስታንስ ቡናማ ቀለም አላት፡፡ ይህ ህንዶች ብሔራዊ ወፍ ያደረጉት የፒኮክ ዝርያ መገለጫ ነው፡፡
የቤተ መንግስቱ በራፍ የቆሙት ፒኮኮች አንዳንዶቹ አንበሳ ጠል ሀሳብ እውን የኾነባቸው ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ይኽንን ለማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንበሳ ጠል ናቸው ወይ የሚለውን በበለጠ መረጃ መፈተሽ ይፈልጋል፡፡ ወይም ዛሬስ ቢኾን አንበሳ ከቤተ መንግስቱ ተነሳ? የአንበሳ ክብር ከቤተ መንግስቱ ጠፋ? የሚለውን በመረጃ መሞገት ይሻል፡፡
አንዳንዶቹ ይኽንን ያስባለን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት እርካብና መንበር ላይ ለአንበሳ የምንሰጠውን ቦታ ከዱር እንስሳው ተፈጥሮና ባህሪ አንጻር አንስተው ይሞግታሉ፡፡ አዳኙ አንበሳ የሚወደስበትና ሰራተኛው አህያ የሚወቀስበት ማንጸሪያ ለዚህ ጥርጣሬ አብቅቷቸዋል፡፡
የኔ ጥያቄ ፒኮክ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ምን ግንኙነት አላት? ለቤተ መንግስቱ በራፍ ጌጥነት የሚያበቃ ዝምድናዋስ? የሚለው ምላሽ የሚሻ ኾኖ ሳለ፤ አንበሳ ተነስቶ ፒኮክ ተሰቅላለች ወይስ የሚለውም መመለስ ያለበት ነው፡፡
በቤተ መንግሥቱ ቅጥር በወረደ አንበሳ ምትክ የተሰቀለች ፒኮክ መኖሯን ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በምትኩ ከዚህ ቀደም “ከአብዮታዊ መሪያችን ከጓድ ሊቀ መንበር አመራር ጋር ወደፊት” ዓይነት የኢሰፓ ታፔላዎች እንደሚቆሙት “ግንቦት ሃያ የኢትዮጵያ ህዳሴ መሰረት” እንደሚለው ግዙፍ ታፔላ ሁሉ ለቅጥሩ ውበት ፒኮክ መደረጓ አንበሳን ማሳደድ ተደርጎ መቆጠሩ ሙግቱን ያፋልሰዋል፡፡ በተቃራኒው ተፈጥሮ ዓለም አቀፋዊነት ይዘት ያለው ፍልስፍና እንደመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢኾኑ በአንበሳ ላይ ፒኮክ ተደመረች እንጂ አንበሳ መች ተቀነሰ ሊሉ የሚችሉበት ተጠየቅ አለ፡፡
ይልቁንስ ዝም ብሎ እንዲህ ያለ ነገር እንዲህ ያለ ቦታ ማኖር ምን ይረባል? የሚለው ጥያቄ መሰረት ያለው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዶክተር አብይ ያኖሯት ፒኮክ ከስነልቦናችንና ከታሪካችን ጋር መስተጋብር ከሌላት ሌላው መሪ እንደመጣ ነቅሎ የሚጥላት የታፔላዎቹ ዓይነት ኮተት ትኾናለች፡፡ ከዚህ የቀደመውን ከመንቀል አባዜ የሚገላግለን ትርጉም ያለው፤ ትርጉሙ ከህዝቡ ጋር የሚስማማ፣ ህዝብ የኔ ብሎ በሚገባው መንገድ የሚሰራ ቢኾን ለትውልድ የሚቀር ስራ ይኾናል፡፡
ለመኾኑ ብሔራዊ እንስሳ፣ ብሔራዊ ወፍ፣ ብሔራዊ አበባ የሌለን ለምንድን ነው? ይቀጥላል……