ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ያደረጉት መልካም ነገር እጅግ የሚመሰገን ነው፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንጂ የደርግ ሠራዊት የሚባል የለም፡፡ ይኽንን ያስከበሩት መሪ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
ስናፍቅሽ አዲስ በድሬቲዩብ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፋሲካ በዓል ካደረጓቸው ተግባራት መካከል ከቀድሞ የሰራዊት አባላት ጋር የነበራቸው ቆይታ እጅግ ልቤን የነካው ነው፡፡ አሁን ያለውን ሠራዊት ሀገር ጠብቅ ለማለት የትናንትናውን እንዲህ ማክበር ያስፈልጋል፡፡
ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የቀድሞ ሰራዊት የተሃድሶ ማእከልን በተደጋጋሚ ጎብኝተዋል፡፡ አይዞአችሁ በማለት የከፈሉት መስዋዕትነት ለሀገር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በትናንትናው ዕለት የትንሳኤ በዓልን ከካቢኔያቸው ጋር በመሆን ከእነዚሁ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ጋር አብረው ማሳለፋቸው የሚመሰገን ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ወረተኛ ሚዲያዎች የቀድሞ ሠራዊት አባላትን የደርግ ሰራዊት ሲሉ ነውረኛ አፋቸውን ከፍተውባቸዋል፡፡ እነኚህ የሰራዊት አባላት ግን በተራራ የቀሩት፣ በውሃ የተበሉት፣ ግንባራቸውን ለጥይት የሰጡት አንዲት ኢትዮጵያ ብለው ነው፡፡ ተከብረሽ የኖርሽው በሚል የሀገር ፍቅር ዜማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተሰኘ የአባቶች ቃል ኪዳን ዜማ ነው፡፡
እነኚህ ጀግኖች አድዋና ማይጨው በወደቁት አባቶች ፍቅር ለሀገራቸው የዘመቱ ሆነው ሳለ የጥላቻ ታርጋን በመንግስት ደረጃ ለጥፎ እንደ ወንጀለኛ የማየቱን መንፈስ በከፍተኛ ደረጃ ወረተኞቹ ሚዲያዎች ሲያግዙት ከመንግስት ፍላጎትም በላይ ከፍተው ሲያበላሹት የነበረን ስም የወታደርን ክብርና ፍቅር ወታደር ያውቃል ነውና ኮለኔሉና ዶክተሩ አብይ አህመድ ቦታና ክብር በመስጠት ከአስቀየምናቸው ጀግኖች ትውልዱን አስተናግደውታል፡፡
ወታደራዊው የመንግስት ስርዓትን ከዚህ ማገናኘት ተገቢ አልነበረም፤ ሀገሬን ብሎ ለሀገሩ የገባ ወታደር ሌላ ነው፡፡ የፖለቲካና የፖለቲከኞች ሀሳብ ወቅታዊ ነው፤ የሀገር ሠራዊት ሞቶ የሚያሻግራት ሀገር ግን የትውልድ ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እጅግ የሚመሰገን ስራ ሰርተዋል፡፡ እነኚህን ከካራ ማራ እስከ አፋበት ለሀገር ሲሉ አካላቸውን ያጡ ጀግኖች እንዲህ በመሪ ደረጃ ሲከበሩ ማየት የሚያስመሰግን ነው፡፡
ይሄንን ማድረግ አሁን ያሉትን ጀግኖች ማመስገን ብቻ ሳይሆን ቀጣዩ ትውልድ ለሀገሬ ምንም መስዋዕትነት ብከፍል የሚረሳኝ ትውልድና መንግስት የለም ብሎ እንዲያስብና ሀገሩን እንዲወድ ያደርገዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አብሮ ፋሲካን ማሳለፍ ደግሞ ጀግኖቹ የከፈሉትን መስዋዕትነት በደማቁ መጻፉን ማረጋገጥ ነው፡፡