#የጎንደር_ሊቀጳጳስ_አባታዊ_መልዕክት
“አታድርግ የተባለውን አድርጎ የሞተ ራሱን እንዳጠፋ…ይቆጠራል!!”
የማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የ2012 ዓ.ም የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለምዕምናኑ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ “‘ሞቼ ነበርሁ፤ እነሆ እስከ ዘላለም ሕያው ነኝ” እያለ ከሞት በኋላ ሕያውነቱን የሚናገር የብቸኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች የሆናችሁ ሁሉ ምግባራችሁን አሳምሩ” ብለዋል።
እንደ ብፁዕነታቸው መልእክት ክርስቶስ በተነሳበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ሠላም አጥተው ደጅ ዘግተው ተቀምጠው ሳለ በተዘጋው በር ገብቶ “ሠላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን የትንሳኤውን የሠላም አዋጅ አወጀላቸው፡፡ መልኩን ሲያዩ፣ ድምፁን ሲሰሙ፣ የተወጋ ጎኑን፣ የተቸነከሩ እጆቹን እና እግሮቹን ሲያዩ፣ ፍርሃታቸው ተወግዶላቸዋል፤ ሠላማቸውም ተመልሶላቸዋል። በሙሉ ልባቸው የትንሳኤው ምስክሮች የሚሆኑበትን ፀጋም አድሏቸዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ዛሬም በአጭር ጊዜ ዓለምን ከወረረው የቸነፈር ሞት፣ ፍርሃት የተነሳ፣ በዓለማችን የሚኖረው የሰው ልጅ እንደ ጌታ ደቀ መዛሙርት ቤቱን ዘግቶ ሠላሙን አጥቶ፣ በፍርሃትና በጭንቀት ተውጦ፣ እጅግ ግራ ተጋብቶ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “ታዲያ ለዚህ ወረርሽኝ ፍቱን መድኃኒት አራት ነገሮችን ብናደርግ በእርሱ ቸርነት ግራ ከመጋባት እንድናለን። ወረርሽኙን የምናሸንፍበት ጥበብም እናገኛለን” ብለዋል።
“ለተወሰነ ጊዜ እየጸለያችሁ በቤታችሁ ተቀመጡ፤ የሚለውን የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ስሙ፣ መንግሥት ቸነፈሩን በተመለከተ እንደዬአስፈላጊነቱ በየጊዜው ለሚያወጣው መመሪያ ተገዥ ሁኑ፤ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ያለምንም ቸልተኝነት ተግባራዊ ማድረግ እና ድሆች ተርበው ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኹ እና ጩኸታቸው እንዳያስፈርድብን እንረዳዳ፤ እነርሱን ትተን አንብላ” ብለዋል፡፡
ሁሉም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ወገንን ለመርዳት በቆራጥነት በገንዘብ፣ በጉልበት እና በዕውቀት የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ወዳጅ ወዳጅነቱ የሚታወቀው በክፉ ጊዜ ነው” ያሉት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ምዕመናን ዜጎች እንዳይጎዱ የሚቻላውን ሁሉ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
“የዚህ ዓለም የችግር ምንጭ አለመታዘዝ ነው፤ ቃልንም አለመጠበቅ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው ሰውም ከዚህ ችግር ለመውጣት በስነምግባሩ ምስጉን እና ከእንስሳዊ ባሕሪ የተለዬ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል። ሰው ሁሉ ፈጣሪውን እየፈራ ቢኖር ከደዌው ሁሉ እንደሚጠበቅና ደዌ በጥንቃቄ ጉድለት እና የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር መንገድ ሲወጣ መቅሰፍት እንደሚመጣ አሳስበዋል።
“እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ። እንቢ ብትሉ ብታምፁ ግን ሰይፍ ይበላችኋል” እንዳለ ሁሉ አመፀኛው ሁሉ እንዳይቀጣ መጠንቀቅ እንዳለበት አሳስበዋል። የሃይማኖት አባቶችም አውቀው ማሳወቅ፣ መምራት እና ትክክለኛውን ሕግና ሥርዓት ማስተማር እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል። ‘‘የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል፣ ክብሩን ለመውረስ ስሙንም ለመቀደስ የተፈጠረ ስለሆነ ይህን ታላቅነቱን ለማክበር ትዕዛዙን መጠበቅ ይገባል’’ ብለዋል።
“አታድርግ የተባለውን አድርጎ የሞተ ራሱን እንዳጠፋና እግዚአብሔርንም እንደተፈታተነ ይቆጠራል” ያሉት ብፁዕነታቸው “እሳት እንደሚያቃጥል እያወቅን ብንጨብጥ ራሳችንም እንደገደልን እግዚአብሔርንም እንደተፈታተን ይቆጠራል። ደዌው በምን እንደሚተላለፍ ጠባዩ ታውቋል፤ ዕያወቅን ተደፋፍረን ተጎጂዎች ብንሆን ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል” ሲሉም ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ አሳስበዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንም ይኼን ተረድታ “በቤታችሁ ተወስናችሁ ጸሎት አድርጉ” ማለቷን እና ምዕመኑ የተባለውን ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ “አዳም የሞተው ያልተባለውን ስላደረገ ነው። እናንተም ያልተባላችሁትን አድርጋችሁ እንዳትሞቱ ተጠንቀቁ” ብለዋል።
(ምንጭ:- አብመድ)