የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም የለገሰው ምክረ ሃሳብ፦
መግቢያ
የኮቪድ-19 (ኮሮና ቫይረስ) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በክልል እና የፌዴራል መንግሥት እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች እንዲሁም በፌዴራሉ መንግሥት መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊነት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይገነዘባል፡፡
ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በተሟላ መልኩ ሕገ መንግሥቱንና ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ያከበረና የሚያስከብር መሆኑን ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዝርዝር ደንቡ ላይ አስቸኳይ ጥናት በማድረግ ሊስተካከሉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ለመንግሥት ምክረ ሀሳብ የሚያቀርብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን በስራ ላይ የዋለውን አዋጅ እና ደንብ አፈጻጸም በተመለከተ ሁሉም የሕግ አስከባሪ ተቋማት በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሊከተሉ ስለሚገባቸው መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መርሆች እና ግዴታዎች የሚከተለውን ምክረ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
የሕግ አስከባሪ ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና ደንቡን በሥራ ላይ ሲያውሉ እና ሲያስፈጽሙ ከዚህ በታች በተመለከቱት የሰብዓዊ መብቶች እና ሕገ መንግሥታዊ መርሆች እንዲመሩ፣ በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ መሠረታዊ መብቶችን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና የሙያ ሥነ ምግባር እንዲመሩ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በከፍተኛ አደራ ጭምር እያሳሰበ አፈጻጸሙንም በስልታዊ መንገድ የሚከታተል መሆኑን ይገልጻል፡፡
1. የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሰብዓዊ መብት መርሆች
(በሕገ መንግሥት አንቀጽ 9፣ 13(2)፣ 93፣ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 4(1 – 3) እንደተመለከተው)፡፡
1.1 የሕጋዊነት መርሕ (Principle of Legality)
ማንኛውም አገር በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን የመንግሥት በሕግ የበላይነትና (Rule of Law) እና በሕጋዊ ሥርዓት የመተዳደር ግዴታ ቀሪ አይሆንም፡፡ መንግሥት ከመደበኛው ሁኔታ በተለየ የተፈቀደለት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ልዩ ሥልጣን ቢኖረውም፤ ይህ ስልጣን በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በሥራ ላይ የሚውል፣ በሕግ የተቀመጠውን ገደብ የሚያከብር፣ እንዲሁም ከሌሎች ሕገ መንግሥታዊና ዓለም ዓቀፋዊ ግዴታዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ የሚተገበር ነው፡፡
የሕጋዊነት መርሕ ሌላው መገለጫ በማናቸውም ጊዜ የነጻ ዳኝነት ሥርዓት የተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ውስጥ ቢሆን መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተቀመጠውን ገደብ አለመጣሱንና የማይታገዱ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ፤ በነጻ ፍርድ ቤት የመዳኘት እና ይህንኑም የማረጋገጫ ሕጋዊ ሥነሥርዓቶች (Judicial and Procedural Remedies) አስፈላጊነት ሊቋረጥ ወይም ሊገደብ አለመቻሉ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ደንብ በአንቀጽ 6 ስር ስለ ዳኝነት፣ የጊዜ ቀጠሮ፣ ፍርድ ቤት የመቅረቢያ ጊዜና የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ ያስቀመጠው ገደብ እና ሌሎች ጉዳዮች ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ዓላማ አንጻር እጅግ አስፈላጊነቱን በመመርመር ከሕገ መንግሥቱና የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊቀረጽ የሚገባበትን መንገድ ኮሚሽኑ ለመንግሥት ያቀርባል፡፡
1.2 በጥብቅ አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ የመሆን መርሕ (Principle of Strict Necessity and Proportionality)
በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለመንግሥት የሚሰጠው ልዩ ሥልጣን የሚፈቀደውም ሆነ በሥራ ላይ የሚውለው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ያስፈለገበትን ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት እጅግ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ እና ለነገሩ ሁኔታ በጥብቅ ተመጣጣኝ እርምጃ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡ በተለይም ከህብረተሰብ ጤና ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ መመስረታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
1.3 መድልዎና አግላይነት የተከለከለ ስለመሆኑ (Principle of Non-Discrimination)
በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሚደረግ የመብት ዕገዳም ሆነ ማናቸውም ሌላ እርምጃ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በቋንቋ ወይም ይህን በመሰለ ሁኔታ ልዩነት ሊደረግበት አይችልም፡፡
እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደ ሴቶች፣ ህፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው የበለጠ ተጎጂ ወይም ተጋላጭ እንዳይሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና መከላከያ እርምጃዎች ሊወስድ ይገባል፡፡
1.4 በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የማሳወቅ ግዴታ (Principle of International Notification)
በዓለም ዓቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 4(3) መሠረት፤ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት ገደብ ያደረገባቸውን መብቶች ዝርዝር ከነምክንያቱና እንዲሁም ገደቡ የሚያልቅበት ጊዜ ጭምር፤ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አማካኝነት በአስቸኳይ ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የማሳወቅ ግዴታ መንግሥት ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎቹን በአግባቡ መወጣቱን ጭምር መከታተያ መንገድ ስለሆነ በአፋጣኝ ሊፈጸም ይገባል፡፡
2. በማናቸውም ሁኔታ ሊገደቡ የማይችሉ ሰብዓዊ መብቶች (Non-Derogable Rights)
(በሕገ መንግሥት አንቀጽ 93(4) (ሐ) እና ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 4(2) እንደተመለከተው)፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከዚህ በላይ በተገለጹት መርሆች በመመራት የተወሰኑ የፖለቲካና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ጊዜያዊ ዕገዳ ለማድረግ ይቻላል፡፡ ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ሆነ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በሕገ መንግሥቱ እና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት ሊገደቡ የማይችሉ መሠረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የማክበር እና የማስከበር ግዴታ ይቀጥላል፡፡ እነዚህ በማናቸውም ጊዜ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶች የሚከተሉትን ይጨምራሉ ፡-
2.1 በሕይወት የመኖር መብት
በማናቸውም ጊዜ የሰዎች ሁሉ በሕይወት የመኖር መብት የተጠበቀ ስለሆነ በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መንግሥት በሕይወት የመኖር መብት እንዳይጣስ የመከላከል፣ ተጥሶ ሲገኝም የማጣራትና የአጥፊውንም በሕግ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ግዴታ አለበት፡፡
2.2 ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ
በማናቸውም ጊዜ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ሰብዓዊ ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ እንዲሁም በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም፡፡
ስለሆነም በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሕግ አስከባሪ ተቋማት በሙሉ ማናቸውም ሰው ከኢሰብዓዊ አያያዝ መጠበቁን የማረጋገጥና የሁሉንም ሰዎች ሙሉ ሰብዓዊ ክብር የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡
2.3 የእኩልነት እና የሕግ ጥበቃ መብት
ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውና በመካከላቸው ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ እኩል እና ተጨባጭ የሕግ ጥበቃ የማግኘት መብት በማናቸውም ጊዜ ሊገደብ የማይችል ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ ተጨባጭ የሕግ ጥበቃ የማግኘት መብት ሌላው መገለጫ ከዚህ በላይ በተራ ቁጥር 1.1 ስር ስለ ሕጋዊነት መርሕ የተገለጸው በነጻ የዳኝነት ሥርዓት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ሊጠበቁ የሚገባ መሆኑ ነው፡፡
2.4 የሃይማኖት፣ የማሰብ እና የሕሊና ነጻነት
ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት እና እምነት የመከተል እንዲሁም የማሰብና የሕሊና ነጻነቱ በማናቸውም ጊዜ ሊገደብ የማይችል መብት ነው፡፡
ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት በሕግ በተመለከተውና ለነገሩ ሁኔታ አስፈላጊ በሆነው መጠን ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሰብሰብ እና በይፋ የሚደረጉ የማምለክና የማስተማር ተግባሮች ላይ ገደብ ሊደረግ ይችላል፡፡
2.5 የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሰራ ስለመሆኑ
ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ወቅት ሥራ ላይ ባልነበረ የወንጀል ድንጋጌ ጥፋተኛ ያለመባልና እንዲሁም ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ የከበደ ቅጣት ያለመቀጣት መብት ሊታገድ አይችልም፡፡
2.6 የፍትሐብሄር የውል ግዴታን ባለመፈፀም ምክንያት ያለመታሰር መብት
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ቢሆንም ማንኛውም ሰው የፍትሐ ብሔር የውል ግዴታን ባለመፈጸም ምክንያት ያለመታሰር መብት ሊገደብ አይችልም፡፡
3. የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሚና
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ሥጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከልና ጉዳቱን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ለመንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም፤ ይህ በአገራችን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመሪያ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በሕገ መንግሥቱ እና የዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ተከናውኖ ግቡን እንዲመታ ለማስቻል፤ በተለይ የሕግ አስከባሪ ተቋማት ልዩ ሚና እና ኃላፊነት አለባቸው፡፡
• የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሚና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ደንብና እርምጃዎች ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት መሠረታዊ መብቶች እንዳይጣሱ መከላከል፣ ሊገደቡ የማይችሉ መሠረታዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ በሕግ በተቀመጠለት ገደብ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ ነው፡፡
• የሕግ አስከባሪ ተቋማት የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡንና ዓላማውን ሲያስፈፅሙ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት፣ የሃይል እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብና ከቀጪነት ይልቅ በአስተማሪነት መንፈስ መመራት ይገባል፡፡ የሀይል እርምጃ የግድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም ፍጹም ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል፡፡
• በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ ወቅትም ቢሆን ነጻ እና ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ሥራቸው የሚቋረጥ ወይም ለሌላ አካል የሚሰጥ ሳይሆን፤ በዳኝነቱ አካል ነጻ አመራር ከአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው አንጻር የሚደረጉ አስተዳደራዊ ማስተካከያዎች ብቻ እንደተጠበቁ ሆነው የፍትሕ አስተዳደር ሥራ ሊቀጥል ይገባል፡፡
• በተመሳሳይ መልኩ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግና ሌሎችም የሕግ አስከባሪ ተቋማት፤ የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡንና ዓላማውን ከማስፈጸም ጐን ለጐን፤ በተለይ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ማስከበር የበለጠ ትኩረት በመስጠት፣ የደንቡን መተላለፍ ጨምሮ ሁሉንም ጥፋቶች የማጣራትና በሕግ ተጠያቂነት ማረጋገጥ ሊቋረጥ የማይገባ ተግባርና ኃላፊነት ነው፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ሕብረተሰብ ሕግና ሥርዓትን እንዲሁም ከጤና ባለስልጣኖች የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪውን በድጋሚ ያስተላልፋል፡፡