Connect with us

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸው 26 ተግባራት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸው 26 ተግባራት
Orthodox Christians pray outside the closed Medhane Alem Cathedral as the government recommends to avoid large gatherings to curb the spread of the Covid-19 in Addis Ababa, Ethiopia, on April 5. Photographer: Michael Tewelde/AFP via Getty Images

ህግና ስርዓት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸው 26 ተግባራት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የከለከላቸው 26 ተግባራት:-

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከሉ ተግባራት ይፋ ሆነዋል። በዚህም መሠረት ከዚህ በታች ያሉት ጉዳዮች የተከለከሉ መሆናቸውን ቅዳሜ ሚያዚያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ላይ በይፋ ተገልጿል።

1. ለሀይማኖታዊ ወይም ማህበራዊ አላማ፣ ለመንግስታዊ ወይም ፖለቲካዊ ስራ ወይም ሌላ መሰል አላማ አምልኮ በሚደረግባቸው ቦታዎች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በማናቸውም የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በማናቸውም ቦታ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት የተከለከለ ነው፤

2. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይም በኮሚቴው የሚቋቋሙና ውክልና የሚሰጣቸው በክልሎች፣ በከተማና በወረዳ ደረጃ ባሉ ንዑሳን ኮሚቴዎች ስብሰባ እንዲደረግ ሊፈቅድ ይችላል፡፡

3. ማንኛውም ሰው ለሠላምታና ሌላ ማንኛውም ዓላማ በእጅ መጨባበጥ ክልክል ነው፣

4. ማንኛውም ሀገር-አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በማንኛውም ጊዜ ከተሸከርካሪው ወንበር ብዛት 50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤

5. ማናቸውም የከተማ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡስ ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር 50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤

6. ማንኛውም የግል ተሸከርካሪ ሾፌሩን ሳይጨምር ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር 50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤

7. የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከዚህ በፊት ሲጭን ከነበረው አቅሙ 25 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤

8. የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ከወንበር ቁጥሩ 50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ ተከለከለ ነው፤

9. ማንኛውንም ታራሚን ወይም ተጠርጣሪን በአካል በመገኘት በማረሚያ ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ መጠየቅ ክልክል ነው፤ ሆኖም ይህ ድንጋጌ በፖሊስ ጣቢያ ለሚገኝ ተጠርጣሪ፣ ከተጠርጣሪው ጋር በአካል ሳይገናኙ ስንቅ ማድረስን አይከለክልም፤

10. በጭፈራ ቤቶችና በመጠጥ ቤቶች ማናቸውንም የመጠጥና መዝናኛ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፤

11. በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፤

12. የሲኒማ፣ ቲያትርና በአንድ ቦታ ብዙ ሰዎችን የሚያሰባስቡ መሰል የመዝናኛ አገልግሎቶችን መስጠት ክልክል ነው፣

13. ሆቴሎች፣ ካፌዎች ወይም ምግብ ቤቶች አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከሶስት ሰው በላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ተገልጋዮች በሚቀመጡባቸው ጠረጴዛዎቹ መካከል ያለው ርቀትም ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት፤ ሆኖም ተገልጋዮች የሚገለገሉት በጠረጴዛ ላይ ካልሆነ በመካከላቸው የሚኖረው ርቀት ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት፤በድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች በኩል ወደ ሀገር ውስጥ መግባትም ሆነ ወደ ውጪ መውጣት የተከለከለ ነው፣

14. .በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 11 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኬላዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል፤

15. ለዚሁ አላማ ከተቋቋመው ኮሚቴ ወይም በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ደረጃ በሚቋቋሙ ንዑስ ኮሚቴዎች ወይም ተመሳሳይ አደረጃጀቶች አማካኝነት ፈቃድ ከተሰጠው ሰው ውጪ በማንኛውም የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን ወይም ባለሙያ ኮቪድ-19ኝን በተመለከተ የፌዴራል ወይም የክልል መንግስትን ወክሎ መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው፣

16. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 11 የተመለከተው ክልከላ ቫይረሱን አስመልክቶ የወጡ ህጎችን በተመለከተ የሚደረግ የሙያ ትንተናን ወይም በህክምና ባለሙያዎች የሚደረጉ ማብራሪያዎችን ወይም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየእለቱ የሚሰጡ መረጃዎችን አይመለከትም፤

17. ማንኛውም የመኖሪያም ሆነ የንግድ ድርጅት ቤት አከራዮች በተከራዩ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ቤቱን እንዲለቅ ማድረግ ወይም የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የተከለከለ ነው፤

18. ማናቸውም በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚተዳደሩ ሰራተኞችን የሚያስተዳደሩ የግል ድርጅቶች በስራቸው ያሉ ሰራተኞችን የስራ ውል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚያስቀምጠው ሥርአት ውጪ ማቋረጥ የተከለከለ ነው፣

19. ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማናቸውም ቦታ አስተማሪና ተማሪዎች በአካል ተገናኝተው መማር ማስተማር ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ወይም ማስተማር የተከለከለ ነው፤

20. ማንኛውም ሁለትና ከዚያ በላይ ሰው በመሆን የሚጫወቱባቸውን ጨዋታዎች፣ ማጫወትም ሆነ መጫወት የተከለከለ ነው፤

21. ማናቸውንም የስፖርት ውድድሮች ወይም የቡድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተከለከለ ነው፤

22. የህፃናት ማጫዎቻ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፣

23. ማንኛውም ሰው የባንክ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች፣ በገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ በሱቆች፣ በመድሀኒት መሸጫ አካባቢዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃዎ በታች በሆነ ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ የተከለከለ ነው፡፡

24. መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንደ መብራት ሀይል፣ ከውሃ አቅርቦት ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ የሚሰሩ ተቋማት ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የህክምና ተቋማት፣ ባንኮች፣ ከምግብ አቅርቦት ጋር ግንኙት ያለው ሥራ የሚሰሩ ተቋማት፣ የጽዳት ስራዋችን የሚሰሩ ተቋማትና ባለሙያዎች፣ ከድንገተኛ ና የእሳት አደጋ መከላከል ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት፣ ከጥበቃና ደህንነት ጋር የተያያዙ ድርጅቶች እና ተቋማት በማንኛውም መልኩ ስራን አለመስራት፣ ማቋረጥ፣ ማስተጓጎል እና መሰል ተግባራትን መፈጸም የተከለከለ ነው፤

25. የደረቅና የፈሳሽ ጭነት አገልግሎትን፣ የምርት ሥራን፣ የእርሻ ሥራን ወይም የግንባታ ስራን ማቋረጥ፣ ማሰተጓጎል ወይም አለመስራት የተከለከለ ነው፣

26. ኮቪድ-19ኝና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋ የሚያደርግና በማህበረሰቡ ላይ ሥነ-ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ማናቸውንም መረጃ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top