Connect with us

ሁለት ዐይነት ስጋዎች

ሁለት ዐይነት ስጋዎች

ጥበብና ባህል

ሁለት ዐይነት ስጋዎች

ሁለት ዐይነት ስጋዎች
(ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ)

ባለፉት ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ተገኝቼ አዲስ ነገር ተማርኩ። —ስጋን አስመልክቶ። በጎችና በሬዎች በተለያዩ ክፍለከተማዎች ሊሸጡ ይተራመሳሉ። ዶሮዎች ደግሞ በጭነት መኪናዎች ውስጥ ተኮልኩለዋል። የስጋና የክትፎ ቤቶችም እንዲሁ ድግሣቸውን አስጥተዋል። ክርስትያኖቹ አዲስአበቤዋች (አረ ሂጃብ የለበሱ ሙስሊሞችም አሉበት) እሉካንዳ ቤቶቹ ደጃፍ ላይ ሰልፍ ይዘው በህይወታቸው ለመጀመርያና ለመጨረሻ ጊዜ ስጋ ይበሉ ይመስል እየተንሰፈሰፉ የበሬ ስጋ ያስቆርጣሉ። እንደተነገረኝ ለወትሮው በኪሎ ከ 300 ብር የማይበልጠው ስጋ አንዳንድ ቦታ እስከ 600 ብር ሆኖአል። —ስጋቤቶቹ በበላተኛው ፍላጎት ተጠቅመው ከሚገባ በላይ ለማትረፍ። ለሁለት ወራት ስለሚዘጉ በአጋጣሚው ለመዝረፍም።

ስጋውን አስቆርጦ ወደቤቱ የሚወስድ ጥቂት ቢኖርም አብዛኛው ሰው እዛው ቁርጥ ወይም ጥብስ የሚበላ ነው። እኔ ታድያ በመገረም “ህዝቡ፣ ሁለተኛ ስጋ አትበላም የተባለ ይመስል ለምን እንዲህ ስጋ ላይ ይራኮታል፣ ደሞስ ወዶ እንጂ ተገዶ ነው እንዴ የሚጾመው?'” ብዬ ጉዋደኞቼን ጠየቅኩ። እነሱም እየሳቁ ሳሉ ከእነሱ አንደኛው ” ጾም ሊገባ ሲል አንበሳና ጅብም የኢትዮጵያን ህዝብ ያህል ስጋን አይሰለቅጥም፣” አለኝ።

ሁለተኛው ደግሞ “ጾም ሊገባ ሲል የሚወደደውና ወንደላጤውን የሚያቅነዘንዘው መቼ የበሬ ስጋ ብቻ መሰለህ? ሌላም ስጋ አለ፣” አለኝ። ከዛም ሁለቱም ተንከትክተው ሳቁ። “አልገባኝም፣” አልኩት። እሱም “ባለፈው ሳምንት በከተማው ውስጥ እና በቡና ቤቶች ሴቶች በገፍ ይገኙ ነበር፣ አሁን ተወደው እና ተይዘው ጠፍተዋል፣ ዐየህ የበሬ ስጋውም የወንድና የሴት ስጋውም የጾም መያዣ ይባላል፣” ሲል አስደነገጠኝ። እኔ ጅሉ ስደነግጥ እነሱ ከመንከትከት አላባሩም።

አብዛኛውን እድሜዬን ከኢትዮጵያ ውጪ በማሳለፌ ”ወይ የኢትዮጵያ ጉድ! መቼም የእስዋ ጉድ አያልቅም፣” ብዬ እየተደመምኩ ከጉዋደኞቼ ተለየሁ። ዘይገርም!!!

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top