Connect with us

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከጠ/ሚ ዐብይ ጋር ያደረጉት አስገራሚ ውይይት

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከጠ/ሚ ዐብይ ጋር ያደረጉት አስገራሚ ውይይት
Photo: Facebook

ጥበብና ባህል

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ ከጠ/ሚ ዐብይ ጋር ያደረጉት አስገራሚ ውይይት

በሐምሌ ወር መጨረሻ ይመስለኛል፤ከዐምስት ወራት በፊት። በምንይልክ ቤተመንግሥት አዲስ በገነቡት ቢሮአቸው ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይን አገኘኋቸው። ገና እንደአገኙኝ አቅፈው ተቀብሉኝ።

ከእዚያም የእኔ የኦሮሞ እና አማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ መፅሃፍ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳበር እና የኢትጵያን ዐንድነት ለማጠናከር እንደሚረዳ አበሰሩኝ። መፅሃፉንም የሥራ ባልደረቦቻችው እንዲያነቡት እንዳደፋፈሩ እና ከውስጡም እያወጡ ይጠቅሱ እንደነበር አወጉኝ። የእዛን ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል ከማግኘቴ በፊት ግን ቤተመንግሥቱን እንድጎበኝ እድል ስጥተውኝ ነበር። ስለእሱ በመጨረሻ እመለስበታለሁ።

ከዶክተር ዐቢይ ጋራ በቢሮአቸው ውስጥ ለ አንድ ሰዐት ተኩል ያህል ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ተነጋገርን። በመጨረሻ፣ ህዝብ ስለእሳቸው አመራር የሚለውን አንዳንድ አስተያየት ባካፍላቸው ቅር ይላቸው እንደሆነ ጠየቅኳቸው። ቅር እንደማይላቸው ገለፁልኝ። እኔም የተለያዩ ህዝባዊ ቅሬታዎችን አቅርቤላቸው አጥጋቢ መልስ ሰጡኝ። ሁሉንም የእኔን ጥያቄዎችና የሳቸውን መልስ እዚህ ማስፈሩ ነገርን የሚጠመዝዙ እና የሚነታረኩ ሰዎች ሲሳይ እንዳይሆን ጥቂቶቹን ብቻ እጠቅሳለሁ። ለምሳሌ በአንዱ ለመጀመር “ህዝብ፣ ለምን ወንጀለኞችን አያስሩም” ይሉዎታል፣ አልኩአቸው። እሳቸውም “አሁን ደግሞ ወንጀለኞችን ለምን አትፈታም ይሉኛል። ወንጀላቸው ተረጋግጦ ያሰርናቸው ብዙ ሰዎች እሉ። ታዲያ እኔን ሁሉም ‘የእኔ ወገኖች ስለታሰሩ ፍታልኝ’፣” ይላል። የማንን ወገን ፈትቼ የማንን በእስር ላቆይ? ጥፋተኛ ጥፋተኛ ነው፤” አሉኝ።

በዛን ጊዜ የተወዳጅነታቸው ዝቅ ማለት ስለ አሳሰበኝ፣ ተወዳጅነታችው እንደመጀመሪያው ጊዜ ከፍ እንዲል አንድ ሥራ ቢሠራ መልካም መሆኑን ባማክራቸው፣ “አንደኛ አሁንም የሚወዱኝ ብዙ ሰዎች አሉ። ሁለተኛ፣ እኔ ህዝብ እንዲወደኝ ብዬ ምንም ነገር እላደርግም። ደግሞም እውነትና ትክክል ነው ያልኩትንም አቋም ለመወደድ ብዬ አልለውጥም። እርስዎን እንደምሳሌ ልውሰድዎት። እርስዎ የኦሮሞ እና የእማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ብለው የፃፉትን መፅሃፍ ከማሳተምዎ በፊት ዐያሌ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችን እና የተለያዩ መጣጥፎችን ፅፈው እንደነበር አውቃለሁ። ሆኖም ይህን ወሳኝ እና ሃቀኛ ታሪካዊ መፅህፍ ለህትመት ካበቁ በኋላ ተቃዋሚዎች ተነሱቦት። መቼም መፅሃፉን የፃፉት እውነተኛነቱን አምነውበት ነው። ታዲያ በመፅሃፉ ምክንያት ተቃዋሚዎች ስለተነሱብዎት ለመወደድ ብለው የመፅሃፉን ሃቀኝነት ይክዳሉ? የቆሙለትንስ እውነት አውግዝው ያፈገፍጋሉ? እኔም “በፍፁም!” አልኳቸው። እሳቸውም “እኔም እንደዛው ነኝ፣” ሲሉ በቆራጥነት የተሞላ ድምፃቸውን አሰሙኝ።

በመሃላችን ጥቂት ፀጥታ ከሰፈነ በኋላ ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ አሉ “እኔ ሰውን በግፍ አልገድልም። ሰው መግደል ፀያፍ ነው። እግዚእብሄርም አይወደውም። ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድም ገንዘብ አልሰርቅም። ደግሞ አንድ ቃል እገባልዎታለሁ።— የመጣው ቢመጣ የእኔ መሪነት ዘመን ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ እንድትበጣጠስ አልፈቅድም። በእዚህ ቀልድ የለም።” የኢትዮጵያን አንድነት አስመልክቶም ሆነ ስለሌሎቹም ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩኝ በግልፅነት፣ በቀጥታ እና በሃቀኝነት እንደነበር ዐይኖቻቸው፣ ድምፃቸው እና ቀትራቸው እማኝ ነበሩ።

ስለ ሥልጣናችው ደግሞ ዶክተር ዐቢይ እንዲህ አሉኝ።– የልቤን መሻት ብናገር እኔ የምፈልግው ሥልጣን ለቅቄ፣ ፖለቲካን ትቼ የምርምር እና የሳይንስ መስኮች ላይ መሰማራት ነው። መደመር የሚባል መፅሃፍ ፅፌ ልጨርስ ነው። ይሄው ይመልከቱት። እኔን ለሚተካው መሪ አቅልዬለታለሁ። ይሄን መፅሃፍ እያነበበ በቀላሉ ኢትዮጵያን ሊመራ ይችላል።”

እኔም በእዚህ ትርምስ እና ሁከት ውስጥ እንዴት ይህን መሰል መርሃ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሊፅፉ እንደቻሉ ተደነቅሁ። እራሳቸው እና ትከሻቸው እጅግ ደንዳና መሆናቸውንም አስተዋልኩ።

ስለ ውጪ ሃገር የመንግሥት መሪዎች ወዳጆቻቸው ሲያወሱኝ ደግሞ “እኔ ብዙ ወዳጆች አሉኝ” በማለት ገለጡልኝ “እነዚህ በአጭር ጊዜ ያፈራሁአቸው ወዳጆቼ ለኢትዮጵያ እድገትና ደህንነት በጣም ይጠቅማሉ። በማንኛውም ረገድ ኢትዮጵያን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።” ስለ መሪዎቹ ለትብብር መዘጋጀት ሌላም እዚህ የማይጻፉ ነገሮች ገለጡልኝ። እኔም እሳቸው ባሉት አመንኩበት።

የአፄ ምንይልክን የግል መኖርያ ቤት አቀማመጥና የእሳቸውን ለሀገር አርቆ አሳቢነት ሲያጫውቱኝ “እንዳየኸው ለአፄ ምንይልክ መኝታ ቤት በጣም ቅርብ ሆኖ የተገነባው ማረፊያ ቤት የኦሮሞው አማካሪያቸው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እንጂ የሚስታቸው የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አልነበረም። ይህን ማድረጋቸው አንደኛ፣ ምንይልክ ሰውን የሚያቀርቡት በችሎታው እንጂ በዘር ስላልሆነ፣ ሁለተኛ በቀንም ሆነ በሌሊት ስለሀገር ጉዳይ ከፊታውራሪው ከአባ መላ ጋራ ተወያይተው በፍጥነት መፍትሄ ለማግኘት ነበር።” በእዚህ ምክንያት አፄ ምንይልክን እኔም በልቤ አደነቅኩአቸው።

በመጨረሻም ልሰናበታቸው ቆሜ ሳለሁ እሳቸውም በትህትና “እባክዎን ይፀልዩልኝ” አሉኝ። እኔም እሺ በማለት ልፀልይላቸው ቃል ገባሁ።

እላይ እንደጠቀስኩት ከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋራ የተነጋገርነው በዛ ያለ ነው። ሆኖም የህይወት ታሪኬን ልፅፍ ከበቃሁ የተረፈውን በሱ ውስጥ አካትተዋለሁ። የቤተመንግሥት ጉብኝቴንም ዝርዝር እንዲሁ። እሱን አሁን በአጭሩ ለማለት ግን በዶክተር ዐብይ ግንባታ እጅጉን ተደምሜአለሁ። ሊፈራርሱ የነበሩትን የአፄ ምንይልክ እና የእፄ ኃይለሥላሤ ህንፃዎችን ነፍስ ዘርተውባቸዋል። የደርግ እና የኢህአዴግ የቅልብ ጦሮች ሰፍረውበት በቅራቅንቦ ያቆሸሹትን ስፍራ ሁሉ አፅድተው አበቦች ተክለውበታል። በቤተመንግሥቱ ውስጥ በግፍ ተገድለው ቅጥር ግቢው ውስጥ ተቀብረው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን አፅሞች አስቆፍርው አውጥተው በመቃብራቸው ቦታ ላይ ለምለም ሳሮች አብቅለውባቸዋል። ደርግ እና ኢህአዴግ ዜጎችን አስረው ይገርፉባቸው የነበሩትን ምድር ቤቶች መዘክር አድርገዋቸዋል። ብርቅዬውን ጥቁር አንበሳ ጨምሮ ለተለያዩ የዱር እንስሳት መሰማሪያ ቦታ ተመድቦላቸዋል። ግቢው በጠቅላላ 42 ሄክታር ሲሆን ከእሱ ላይ ለህዝብ መዝናኛ በማሰብ “አንድነት መናፈሻ” የሚባል አዘጋጅተዋል። በእዚህም ስያሜ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን የማያወላውል እቋም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ባህል የሚወክሉ ጎጆዎችም በመናፈሻው ውስጥ በየዐይነቱ ቁጭ ቁጭ ብለዋል። እነዚህን የቃኙ ሰዎች ዋናዎቹን ብሄር ብሄረሰቦች ሄደው እንዲጎበኙ የሚጋብዙ ናቸው። በሺህ የሚቆጠሩ የጎብኚ መኪኖች ማቆሚያም አለ። በፊት የዐፄ ኃይለሥላሤ ፅህፈትቤት የነበረውንም አስዘምነው፣ አሳድሰውና አሳምረው ከአፄ ኃይለሥላሤ እስከ እሳቸው ድረስ ኢትዮጵያን የመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ፎቶግራፎች (ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሳይቀሩ) በቅደም ተከተል ደርድረዋቸዋል። ቤቱን በዘመናዊ የመገናኛ እቃዎች (ኮምፒተሮችን እና ኢንተርኔትን ጨምሮ) አጭቀውም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ ሃገር ርእስብሄሮች ማረፊያ አውለታል። ለደህንነታቸውም ቢሆን ሆቴል ቤት እንዳይቆዩ በመትጋት የሆስፒታል ኮሪዶር ይመስል የነበረውን ቀፋፊ እና ጭልምልም የደርግ እና ኢህአዴግ ቢሮ ለመዘክርነት እዛው ትተው የእንግዳ መቀበያ እና የስብሰባ ክፍሎች ያሉት ብሩህ እና ለመንፈስ ደስ የሚል አዲስ ቢሮ ሠርተዋል። ቀድሞ በጦረኞች በብርቱ እየተጠበቀ ዜጎች ዘወር ብለው በሙሉ ዐይኖቻቸው ሊቃኙት የማይደፍሩት ቤተመንግሥት ተውቦ ዛሬ ለሁሉም ዜጎች ክፍት መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያስመሰግናቸዋል። በእንደዚህ ዐይነት ውጥረት ውስጥ ሆነው ይህን ሁሉ በ ዐስራሁለት ወራት በቤተመንግሥቱ ማከናውን ከቻሉ በተረጋጋ ሃገር እና አመፅኛ ባልሆኑ ህዝቦች መሃል ቆይተው ቢያስተዳድሩ ምን ያህል ዕፁብ፣ ድንቅ ተግባራት በፈፀሙ ያሰኛል። እኛ ያልታደልን ሆነን ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከልባቸው እጅግ የሚያፈቅሩ እና ብዙ ሊሠሩላት የሚሹ እና የሚችሉ ታላቅ መሪስ አግኝተን ነበር። የኢትዮጵያን የ 4300 ዐመታት ታሪክ እኔ የአቅሜን ያህል መርምሬአለሁ። የነገሥታቱንም ታሪክ አንብቤአለሁ። ዶክተር ዐቢይ እንደ አሉበት እንደኛ ዘመን ክፉ እና የተወሳሰበ ዘመን ውስጥ የኖሩ መሪዎች ግን አላጋጠሙኝም። ከእሳቸው የአመራር ዘመን ሲነፃፃር መጥፎ የተባለው የድሮው ዘመን እንኳን እንደጥሩ የሚታይ ነው። ለእኛ ግን ነገሮችን የሚያገናዝብ እና መልካም የሚያሳስብ ቅን ልቦና እግዚአብሄር ያድለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ስለተቀበሉ በዚህ እጋጣሚ የተሰማኝን ፍስሀ ልገልፅላቸው እወዳለሁ። ሽልማቱ የኛ የኢትዮጵያውያን፣ የኤርትራውያን እና የ የመላው አፍሪካውያን ነው። ሽልማቱን የተቀበሉ ዕለት ያደረጉትም ንግግር እጅግ መሳጭ ነበር። ወረቀት ሳይዙ ዘለግ ላለ ጊዜ በተሳካለት እንግሊዝኛ ያን የመሰለ ቁምነገር መናገራቸው ያስደንቃቸዋል። በሳቸው ምክንያት በሽልማት ሰጪዎቹ አፍ ኢትዮጵያ እንደትወደስ ማስደረጋችውም ያስመሰግናቸዋል። የኖቤል ሽልማቱን ሥነሥርዐት ያካሄዱት ሴትወይዘሮ “ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ስለሆነች እኛም ኢትዮጵያዊያን ነን፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተገዝታ የማታውቅ ሃገር ነች፤” ያሉት በእሳቸው ምክንያት ነው። እሳቸው ሽልማቱን ባያገኙ ኖሮ ሴትዮዋ ይህን ባላሉ ነበርና። ይህን ፅሁፍ ከመደምደሜ በፊት ለእሳቸው እና ለቤተሰባቸው ረጅም ዕድሜ እና ጤንነት እመኝላቸዋለሁ። ኢትዮጵያም በሠላም፣ በፍቅር እና በአንድነት ለዘላለም እንድትኖር እፀልያለሁ።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top