በዐለት ላይ የሚጻፍ ታሪክ
(ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
ሰሞኑን ከሰማናቸው መልካም ዜናዎች አንዱ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ያለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሬት የማግኘቷ ጉዳይ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠይቁ ለነበሩ የኤምሬት አባቶችና ምእመናን ዜናው ገነትን የማግኘት ያህል የሚያስደስት ነው፡፡
በኤምሬት ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሰጥታለች፡፡ ምእመናኑ ዕድለኞችም ጸሎተኞችም ናቸው፡፡ የሚያገጥሟቸው አብዛኞቹ አባቶች ለጸሎት፣ ለትምህርትና ለማኅበራዊ አገልግሎት ይተጋሉ፡፡ አብዛኞቹ እኅቶች የሆኑት የኤምሬትስ ምእመናን ከኑሮና ከሥራ ጋር እየታገሉም ቢሆን አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ጊዜያቸውንም ገንዘባቸውንም ያለ ስስት ይለግሣሉ፡፡ ትልቁ ችግራቸው የነበረው የራሳቸው የሆነ ቦታ አለማግኘታቸው ነበር፡፡
በኤምሬትስ ያሉት አጥቢያዎች የግብጽ ቤተ ክርስቲያንና የሕንድ ቤተ ክርስቲያን ጥገኞች ነበሩ፡፡ አገልግሎት ለማግኘት፣ አገልጋዮችን ለማስመጣት፣ የካህናትን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት፣ ንዋያተ ቅድሳትንና ሌሎች ነገሮችን ለማስመጣት ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ደጅ መጥናት የግድ ነበር፡፡ በዕጣን ጢስ ምክንያት ቅዳሴ የተከለከለበት፣ በሕዝብ ብዛት ምክንያት ንግሥ የታገደበት ዘመን ነበር፡፡ የጥምቀትና የንስሐ አገልግሎት ለመስጠት የፈቃጆቹን መልካም ፈቃድ ይጠይቅ ነበር፡፡ ከዚያም ካለፈ የግለሰቦችን ቤት ለመጠቀም አባቶች ይገደዱ ነበር፡፡ በውሰት የሚገኙት የአገልግሎት ቦታዎች ከልካቸው በላይ ስለሚሞሉ ከፖሊስና ከቦታው ባለቤቶች ጋር ዘወትር ጭቅጭቅ አይጠፋም0፡፡ ሌላው ቢቀር የቤተ ክርስቲያንዋን ገንዘብ እንኳን በትክክል ለማስቀመጥ ይቸገሩ ነበር፡፡
በኤምሬትስ ያለች ቤተ ክርስቲያን ባለ ሙሉ መብት የምትሆነው የራስዋ ቦታ ኖሯት የራስዋን ቤተ ክርስቲያን ስትገነባ ወይም የራስዋን ቤተ ክርስቲያን በሌላ መንገድም ቢሆን ስታገኝ ነው፡፡ የሀገሩ ሕግ ይሄንን ያዛል፡፡ ያለበለዚያ ግን በሌሎች ፈቃድ የምታገለግል አጥቢያ ነው የምትሆነው፡፡ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በኋላ የግብጽ፣ የሕንድና የሩሲያ አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ገንብተዋል፡፡
በኤምሬትስ የምትገኘው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሬት የማግኘት እንቅስቃሴ የጀመረችው ወዲያው እንደተተከለች ነው፡፡ ነገር ግን ከሁለት ወገን ጠንካራ ጥረት ሊደረግ አልቻለም፡፡ ከቤተ ክህነቱና ከቤተ መንግሥቱ፡፡ በአንድ በኩል ምእመናኑ በአካል ወደ አዲስ አበባ እየመጡ፣ በሌላ በኩልም አባቶች ወደ ኤምሬት ሲሄዱ ችግራቸውን እያቀረቡ ጥረት አድርገዋል፡፡ ደጅ ጠንተዋል፡፡ ቤተ ክህነቱ ግን ጉዳዩን ሥራዬ ብሎ አላገዛቸውም፡፡
በኤምሬት ለሃይማኖት ተቋማት መሬት የሚሰጠው በንጉሡ አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ የግብጽና የሩሲያ አብያተ ክርስቲያናት መሬት ያገኙት በፕሬዚዳንት ሙባረክና በፕሬዚዳንት ፑቲን ቀጥተኛ ጥረት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቀረበችው ጥያቄ እንዳይሳካ ዕንቅፋት የሆነውም ጉዳይዋን የሚይዘው ከፍተኛ የመንግሥት አካል በማጣቷ ነበር፡፡
ከመንግሥት ኃላፊዎች መካከል ሁለት ታላላቅ ባለ ሥልጣናት ጉዳዩን በኃላፊነት ለመያዝ ተነሥተው ነበር፡፡ አቶ ስዩም መስፍንና ፕሬዚዳንት ግርማ፡፡ አቶ ስዩም መስፍን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ የኤምሬት ምእመናንን ጥያቄ ተቀብለው ነበር፡፡ ቤተ ክህነቱ ጉዳዩን በዋናነት ከያዘው መሥሪያ ቤታቸው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄው እንዲመለስ እንደሚሠራ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ከቤተ ክህነቱ በኩል ግን ተገቢውን ድጋፍ ያገኙ አይመስለኝም፡፡
ነፍሰ ኄር ፕሬዚዳንት ግርማ በአካል ወደ አቡዳቢ ሄደው ንጉሡን ለማነጋገር ፈቃደኛ ነበሩ፡፡ ዲፕሎማሲያዊ መንገዱን የሚያመቻችና ሎጅስቲኩን የሚያሳልጥ አካል ግን ያስፈልግ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁለቱንም እንዳላገኙ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የኤምሬት ምእመናን ጥያቄ ወደ ቢሯቸው መጣ፡፡ በውጭ ሀገር ከነበሩ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የመጡ ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ የዴር ሡልጣን የጥገና ጉዳይና የኤምሬት የመሬት ጥያቄ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱንም ጉዳዮች ከየሀገራቱ መሪዎች ጋር ተነጋግረውባቸዋል፡፡ መጀመሪያ የዴር ሡልጣን ጉዳይ እንዲሳካ አድርገዋል፡፡ በመቀጠልም በኤምሬት የሚገኙ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በቅደም ተከተል ቦታ እንዲያገኙ ለመሥራት ወሰኑ፡፡
በጉዳዩ ላይ ሁለት መልክ ያለው ጥረት ተደርጓል፡፡ ቢሮክራሲያዊ ሥራውን በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትጋት አከናውኗል፡፡ በተለይ ደግሞ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በኤምሬት ከተመደቡ በኋላ በተለመደው ትጋታቸው ጉዳዩን አጥብቀው ይዘውት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኤምሬት አቻዎቻቸው ጋር በተገናኙበት ጊዜ ሁሉ ጉዳዩን አንሥተዋል፡፡ ወደ ኤምሬት የሚሄዱበት ጊዜ ሲደርስም እንደ አንድ የውይይት አጀንዳ እንዲያዝ አድርገዋል፡፡ የኤምሬት ባለ ሥልጣናት ለኢትዮጵያውያን መልካም አመለካከት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር፡፡ ሁኔታዎችን አመቻችተው ለኢትዮጵያውያን የእምነት ተቋማት መሬት ለመስጠትም ቃል ገብተው ነበር፡፡ እነሆ የስጦታቸውን መጀመሪያ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመስጠት ጀምረውታል፡፡
የሦስት ሰዎች ዋነኛ ሰዎች ጥረት ይህንን ውጤት አምጥቷል፡፡ የአቡነ ድሜጥሮስ ጸሎት፣ የአምባሳደር ሱሌይማን ትጋት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን ጉዳያቸው አድርገው መያዝ፡፡ ታላቁ አባት፣ ትጉኁ፣ እንደ ዋርካ ተተክለው በአንድ ቦታ ያፈሩት፣ ለረዥም ዘመናት የዓረቡን ዓለም ውጣ ውረድና እንግልት ችለው የጣሩት፣ አቡነ ድሜጥሮስ ሊደነቁ ይገባል፡፡ ከሰሞነኛነት እስከ ጵጵስና ሕዝቡን አገልግለዋል፡፡ የሕዝቡን ችግር ችግራቸው፣ መከራውንም መከራቸው አድርገው ተቀብለዋል፡፡ የእርሳቸው ትጋት ባይጨመር ኖሮ ይህንን ተአምር ማየት ሕልም ይሆን ነበር፡፡
አምባሳደር ሱሌይማን ከሰበካ ጉባኤው በላይ ሰበካ ጉባኤ፣ ከአስተዳዳሪው በላይ አስተዳዳሪ፣ ከጳጳሱ በላይ ጳጳስ ሆነው ያደረጉት ጥረት በታሪክ ምእራፍ ላይ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ተሰሚነታቸውንና ተቀባይነታቸውን ተጠቅመው፣ ከመነሻው የሕዝቡን ጥያቄ የመንግሥት ጥያቄ አድርገው፣ ከኤምሬት ጉዟቸው ጋር የሕዝቡን ጥያቄ ይዘው በመጓዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ በዚህም ታሪክ ምንጊዜም ሲያነሣቸው ይኖራል፡፡ የሕዝቡም ጸሎት ይረዳዎታል፡፡
ዐፄ ላሊበላ ከሳላሕ ዲን የኢየሩሳሌምን ርስት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንዳስፈቀደ ሁሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ከኤምሬቱ ንጉሥ ርስት አሰጥተዋል፡፡ በዚያ ሥፍራ ለጸሎት የሚቆሙ ሁሉ በዓይነ ኅሊናቸው እስከ ዘለዓለም ያስታዉሱዎታል፡፡ ይህ ውለታ በአሸዋ ላይ ሳይሆን በዐለት ላይ የሚጻፍ ታሪክ ነውና፡፡