የአፍሪካ መሪዎች ኩምክና ሁሌም እንዳሳቀኝ ነው | (ጫሊ በላይነህ)
ዛሬ የሚጠናቀቀውን የአፍሪካ ህብረት 33ኛ ስብሰባ መሪ ቃል በእንግሊዝኛው (ቲም – the theme) ስሰማ ሳቄ ቀድሞኛል፡፡ መሪ ቃሉ “Silencing the Guns: Creating Conducive Conditions for Africa’s Development”. የሚል ሲሆን ወደአማርኛ ሲመለስ የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማባትን አህጉር መመስረትን የሚመለከት ነው፡፡ ይኸ የአፍሪካውያን የኩምክና መሪ ቃል እየተነገረ ያለው ቤተክርስቲያን ልሰራ ብሎ የጠየቀ ሕዝበ ክርስቲያን በለሊት በተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተገደሉባት ከተማ ላይ ቁጭ ብለው ነው፡፡
ቃሉ እየተነገረ ያለው፤ ከ17 በላይ ወጣት ልጃገረዶች በታጣቂዎች ታፍነው ሕግና ሥርዐት የማስከበር ግዴታ ያለበት መንግሥት አድራሻቸውን ጠፋኝ እያለ በሚናገርበት መናገሻ ከተማችን ነው፡፡ ይኸ ቃል የሚነገረው፤ ከአራት ወራት በፊት አንድ ግለሰብ “በለሊት ጠባቄዎቼን ሊያነሱብኝ ነው” ከማለቱ ጋር ተያይዞ ከ86 በላይ ዜጎች በጠራራ ጸሐይ በተገደሉበት፣ አጥፊዎችም ያለጠያቂ ደረታቸው ነፍተው በሚንቀሳቀሱባት አገር ነው፡፡
አዎ!…ዛሬ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ ዜጎች መርጠው ባልተወለዱበት ማንነት የሚገደሉባት፣ የሚሰደዱባት፣ የሚዋረዱባት…አገር ናት፡፡ ዜጎች ለትምህርት ወደዩኒቨርሲቲ በማምራታቸው ብቻ የዘር ሐረጋቸው እየተመዘዘ ለጥቃት የሚጋለጡባት፣ የሚሞቱባት፣ ይህንም የዜጎች ሰቆቃ ማስቆም የማይችል ደካማ መንግሥት ባለበት አገር ላይ ለስብሰባ የተቀመጠው የአፍሪካ ህብረት የጦር መሣሪያ ድምጽ ስለማይሰማባት አህጉር ማሰቡ በራሱ ድንቅ የሚል ነው፡፡ ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ ይሏል ይኸ ነው፡፡
የእርስ በእርስ ግጭትና ጦር መማዘዝ ለአፍሪካ ኃላቀርነትና ዕድገት ማነቆ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ድህነት እና ችጋር የሰፈነባት አህጉር ሕዝቧን ለመመገብ ከመጣር ይልቅ በእርስ በእርስ ጦርነት መታመሷ ጉዳቱ ለአህጉሪቱ ነው፡፡ ይኸን ለመቅረፍ ግን በደም ወደሥልጣን የተሳቡ፣ በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ስም ኮሮጆ የሚገለብጡ፣ የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለሥልጣን ሲሉ የሚጨፈልቁ፣ ከተቀመጡበትን ወንበር ላለመነሳት ሕገመንግሥት እስከማሻሻል የሚደክሙ መሪዎች ግን ስለሠላምና ከመሳሪያ ድምጽ ስለጸዳች አህጉር የማውራት ምን ሞራል አላቸው የሚለው በቅድሚያ መመለስ ይኖርበታል፡፡
ዛሬም ጎረቤት ደቡብ ሱዳን የሚታየው ዘግናኝ እልቂት ፖለቲከኞች የፈጠሩት ሰው ሰራሽ ጠብ ውጤት እንጂ ሕዝቡ ተጣልቶ አለመሆኑን ዓለም ያውቀዋል፡፡ እንደሊቢያ ያሉ አገራት ፍርክስክሳቸው ወጥቶ ሕዝቦቻቸው የተማገዱት፣ እንደጨው ዘር በዓለም ላይ የተበተኑት በግትር መሪዎች የማይመለስ ጥፋት ነው፡፡
እናም የአፍሪካ ህብረት መሪዎች በቅድሚያ የሕዝባቸውን የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የህግ የበላይነት፣ የዳቦ… ጥያቄዎች በአግባቡ ይመልሱ፡፡ በቅድሚያ በየአገሮቻቸው የሚንቀሳቀሱ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎችን እንደጠላት በመፈረጅ ከሰዶ ማሳደድ ለመላቀቅ ስለመቻላቸው አፋቸውን ሞልተው ለመናገር ይብቁ፡፡ በቅድሚያ ሚዲያ እና ጋዜጠኞችን ከማሳደድ እና አፋኝ ሕጎችን ለማውጣት ከመዳከር ይቆጠቡ፡፡
አዎ!…ምናልባት ተሳክቶላቸው ይኸን ካሟሉ ያኔ ከጦር መሳሪያ ድምጽ ስለጸዳችው አፍሪካ ለመጨነቅ፣ ቁጭ ብለው ለማውራት፣ ያወሩትንም ለመተግበር አቅም ይኖራቸው ይሆናል፡፡ አዎን!.. ማን ያውቃል?!