ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን አለማድነቅ አይቻለኝም!! | (ጫሊ በላይነህ)
የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባዔ የሆኑት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከዋልታ ቴሌቭዥን ባልደረባ ስሜነህ ባይፈርስ ጋር ያደረጉትን ቃለምምልስ ተከታተልኩት፡፡ በእውነቱ የሴትየዋ ጠንካራና የማያወላውል አቋም እንዲሁም ለፓርቲያቸው ህወሓት/ኢህአዴግ ያላቸው ታማኝነት በእጅጉ አስደንቆኛል፡፡ በተለይ የያዙትን ሹመትና ጥቅማጥቅም ላለማጣት ስንትና ስንት አጸያፊ ተግባራትን ጭምር የሚሰሩ አጎብዳጅና አስመሳይ የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናት በበዙበት በዚህ ወቅት የወ/ሮ ኬሪያ የማያወላውል አቋም ማስገረሙ የሚጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ላይ ቀለል ባለ መንገድ ሃሳባቸውን ለመግለጽ ያደረጉት ጥረት መሳጭ ነው፡፡
ወ/ሮ ኬሪያ ምንድነው ያሉት?
ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባዔ ለዋልታ ሲያስረዱ ካነሱት ዐብይ ጉዳይ አንዱ ሲሾሙ የገቡትን ቃለመሀላ የሚመለከት ነበር፡፡ የቀድሞው አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ ለምክር ቤቱ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክርቤት አፈጉባዔ ሆነው የተሸሙት ሚያዚያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፡፡ ወይዘሮዋ በህወሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ካሉት ጥቂት ሴቶች አንዷ ሲሆኑ፤የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በትግራይ ክልል ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ባሉ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡
ወ/ሮ ኬሪያ “መቐሌ ሲሄዱ ሌላ እዚህ ሲመጣ ሌላ ይሆናሉ” ስለመባሉ ተጠይቀው የሰጡት ምላሽ ግልጽና ቀጥተኛ ነበር፡፡ “አዎ መሆን አለብኝ” የሚል፡፡ ይኸን ሲያብራሩም “…የማምንበት ፖለቲካ አለኝ፡፡ እዚህ ስመጣ ደግሞ (ፌዴሬሽን ም/ቤት ማለታቸው ነው) የተሾምኩበት አለ፡፡ ለሕገመንግሥቱ ነው የተሾምኩት፡፡ ለሕገመንግሥቱና ለፌዴራል ሥርዓቱ ጥብቅና አለኝ፡፡ ….እኔ ስሾም ህወሓትን ወክዬ ነው፡፡ እዚህ ፌዴሬሽን ምክርቤት ስሾም የማልኩት ኢህአዴግ ሆኜ ነው፡፡ …ሁለተኛ መሀላ አልፈጸምኩም” ብለዋል፡፡
የወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ቃለምልልስ በእኔ አረዳድ ፓርቲያቸው ህወሓት ከውህደት ሀሳብ ጋር ተያይዞ ያሳለፈውን ውሳኔ የሚደግፍ ነው፡፡ የኢህአዴግን መፍረስ የማይቀበል ነው፡፡ ይህ ሃሳባቸው እነጠ/ሚ ዐብይን የሚያስኮርፍ ነው፡፡ ምናልባትም የብልጽግና ፓርቲ አስተሳሰብ ባለመደገፋቸው ብቻ ከሥልጣን ሊነሱ ወይንም በሥልጣን እያሉም መገለል ሊደርስባቸው የሚችልበት ዕድሉ ሰፋ ያለ ነው፡፡ እንግዲህ የሴትየዋ ጠንካራ የፓርቲ ዲሲፒሊን የሚገርመው ከዚህ አንጻር ነው፡፡ እንደአንዳንዶች ሆዳቸውን አላስቀደሙም፡፡
ከሴትየዋ አነጋገር ለመረዳት እንደቻልኩትም የመጣውን ሁሉ ለመቀበል፣ ተገቢውን ዋጋ ለመክፈል የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ በሰሞኑ የፓርላማ ጥያቄና መልስ ቆይታቸው በቅርቡ የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትርዋን ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ከሥልጣን ያነሱበት ምክንያት ከህወሓት ማፈንገጥ ጋር እንደማይገናኝ ለማስረዳት የወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም አለመነሳት መጥቀሳቸው የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ወ/ሮ ኬሪያ የገዥው ፓርቲ አስተሳሰብ በዚህ መልክ እየነቀፉ በከፍተኛ የመንግሥት አመራርነት ቦታ ምን ያህል ርቀት ሊጓዙ ይችላሉ የሚለው ነው፡፡ በሰለጠኑ አገራት ቢሆን እንዲህ ዓይነት የልዩነት ሃሳብ የሚያነሱ ባለሥልጣናት በገዛ ፈቃዳቸው ከሥልጣን ለመነሳት ለደቂቃም ቢሆን አያንገራግሩም፡፡ በጥቅሉ በኢትዮጵያ ግን ይህ ባህል እንደጎጂ ልማድ ስለሚቆጠር አስፈጻሚው የበላይ አካል እስኪያሰናብት ባለሥልጣናት ወንበራቸው ላይ እያንጎላጁም ቢሆን መክረም የተለመደ ነው፡፡ የወ/ሮ ኬሪያም ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ከዚህ ውጪ ባይሆን ሊገርም አይገባም፡፡
ያም ሆነ ይህ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እሳቸው ላመኑበት አቋም ያሳዩት ጥንካሬ በግሌ የማደንቀው ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ ብዙዎቹ አመራሮች ላመኑበት እንዲህ ያለ ጠንካራ የፓርቲ ዲሲፒሊን ቢኖራቸው ኖሮ አሁን በየደረጃው ያለው ቀውስ ባልተፈጠረም ነበር ብዬ አስባለኹ፡፡ ደህና ክረሙልኝ!