የሱማሌዎች ቀዬ የአቶ ሙስጠፌ ክልል ሰላም ነው የሚለው ቃል አይገልጸውም፡፡ ገራሌ ብሔራዊ ፓርክን ፍለጋ፡፡
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የኢትዮጵያን ቀጭኔዎች ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥግ ተጉዣለሁ እያለን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በበርካታ ብሔራዊ ፓርኮች ይገኙ የነበሩት የቀጭኔ ዝርያዎች ዛሬ በጥቂት ስፍራዎች ብቻ እንደሚኖሩ ነው የሚነገረው፤ ተከታዩ የሄኖክ ስዩም ዘገባ በገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ያደረገውን ቆይታ ይመለከታል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ኡደት ቀን ትሞቃለች፡፡ ምሽት አየሯ ደስ ይላል፡፡ አንዳንዱ ሰው አፉ ላይ ሲጠራት ሁደት ይላታል፡፡ የሱማሌ ክልል ዳዋ ዞን ዋና ከተማ ናት፡፡ ስያሜዋ ድምጸ ቀድ ነው ይላሉ፡፡ ከወፍ ዜማ በተቀዳ ድምጽ የምትጠራዋ ከተማ የገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ዋና ጽ/ቤት ይገኝባታል፡፡

ሰላም ነው፡፡ ከመሀል ሀገሩ የተሻለ ሰላም ብቻ ሳይኾን የምንመኘው ዓይነት ሰላም አለ፡፡ አቶ ሙስጠፌ ተሳክቶላቸዋል፡፡ እዚህ አንድም ሰው መሳሪያ አነግቶ አላየሁም፡፡ ስጋትም የለም፡፡ ይህ ስፍራ ከጥቂት አመታት በፊት “በወንድማማቾች መካከል እንዴት እንዲህ ያለ ጦርነት ይደረጋል?” የተባለበት ከባድ የግጭት ቦታ ነበር፡፡
ገራሌ ብሔራዊ ፓርክ በብዙ ምክንያት ተደብቆ የኖረ ፓርክ ነው፡፡ ስጋት ከሀገር ልጅ እንዲሸሸግ አድርጎታል፡፡ መምጣት ለብዙ ሰው የሞት ያህል መርግ ነው፡፡ መጥቼ ያየሁት ግን የዚህን ሁሉ ተቃራኒ ነው፡፡ ገራሌ መድረስ ብሔረ ጽጌን የመጎብኘት ያክል ፍጹም ሰላም እና ስጋት አልባ ነው፡፡
ሳሚ ቆይታችንን በተመለከተ አናገረን፡፡ የብሔራዊ ፓርኩ ሃላፊ ነው፡፡ ከገለጻው እንደተረዳሁት የብሔራዊ ፓርኩ ሰራተኞች መሳሪያ አይዙም፡፡
የዱር ሕይወት ጀግኖቹ ሬንጀራቸውን ይለብሳሉ፤ ቀለባችንን እንጭናለን፡፡ ኢትዮጵያ ከኬኒያ እስከምትለይበት የድንበር ጥግ ድረስ እንጓዛለን፡፡

እዚህ ከከባድ መሳሪያ በላይ የጎሳ መሪዎች ቃል ኒውክለር ነው፡፡ የሀገር እንግዳ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ የክርክሩ ድምጽ ይሄንን ገለጸልን፡፡ ምሳ የምንበላበት ድረስ የመጣው የኡደት ሰው “የፓርክ እንግዶች የእኔ እንግዶች ናቸው” ብሎ ካልጋበዝሁ ሲል ሰውና ፓርክ መግባባታቸው ገባኝ፡፡
ወደ ሙባረክ ልንጓዝ ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያው ሱማሌ ክልል የዳዋ ዞን አካባቢዎች ናቸው፡፡ የአቶ ሙስጠፌ ክልል ሰላም ነው የሚለው ቃል አይገልጸውም፡፡ አንዳች ስጋት የለብኝም፡፡ መሳሪያ ያነገተ አላየሁም፡፡ ከየት መጣህ የሚል ዝር አላለም፡፡ የማያውቀኝ እንኳን እጁን ዘርግቶ ሰላምታ ያቀርባል፡፡ ሰላም እንዲህ ላለው ምድር ይሁን፤ ቀጭኔዎችን ፍለጋ ጉዞ ቀጥያለሁ፡፡