Connect with us

ጥያቄ፤ በታፈኑት ተማሪዎች ዙሪያ፤

ጥያቄ፤ በታፈኑት ተማሪዎች ዙሪያ፤
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ጥያቄ፤ በታፈኑት ተማሪዎች ዙሪያ፤

ጥያቄ፤ በታፈኑት ተማሪዎች ዙሪያ፤
(ያሬድ ሀይለማርያም)
—-
~ ተማሪዎቹ ከታፈኑ አንድ ወር አልፏቸዋል፤ ለዚህን ያህል ጊዜ ጉዳዩ ለምን ተሸፋፍኖ ቆየ?

~ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን፣ የፌደራል እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ሹማምንት፣ #የጠቅላይ_ሚኒስትሩ_ቃል_አቀባይ፣ የደንቢዶሎ ዩንቨርሲቲ አመራሮች እና ሌሎች የመንግስት አካላት ለምን በተለያየ ጊዜ የተለያየ እና እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ ሰጡ?

~የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ እንዳሉት 21 ተማሪዎች በድርድር እና በሽምግልና ተፈተዋል፣ 6ቱን ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። የተፈቱት ልጆች እነማን ናቸው? የት ነው ያሉት? አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

~ ለምን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ አልተደረገም? መቼ ነውስ ድርድሩ አልቆ ነጻ የወጡት? ባለሥልጣናቱ እንኳ ይህን መግለጫ ከሰጡ ውሎ አደረ፣ ቤተሰቦችም የልጆቻችንን ድምጽ አሰሙን እያሉ ተሟጽኗቸውን እያሰሙ ነው። ታዲያ መንግስት ይህን ማድረግ ለምን ተቸገረ?

~ በአንድ ሴት ላይ የሚደርስ ጥቃት የሚቆረቁራቸው ባለሥልጣናት እና የተለያዩ አካላት ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ታፍነው ሲወሰዱ ዝምታን ለምን መረጡ? ከዚህ በፊት ተደጋግሞ እንደተስተዋለው አንዲት ሴት በባሏ ወይም በአንድ ግለሰብ በአሲድ እና በሌሎች መንገዶች ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጸምባት ትልቅ አገራዊ ቁጣ ይስተዋል ነበር።

እነዛ በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸም ግፍ የሚያስቆጣቸው ባለሥልጣናት፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት አባቶች እና ፖለቲከኞች ምነው በዚህ የአፈና ጉዳይ ዝምታን መረጡ?

~ ለሴት ትልቅ ክብር አላቸው ብለን እንደ ጥሩ ምሳሌ የምናነሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህን ያህል ጊዜ በዚህ እጅግ አሳዛኝ እና አሳሳቢ ጉዳይ ዝምታን መርጠው ቆዩ?

~ የመንግስት ባለሥልጣናትን ጭራ እየተከተሉ እገሌ ቆላ ወጣ፣ እገሌ ደጋ ወረደ እያሉ የሚነዘንዙን መገናኛ ብዙሃን ለምን ለዚህ የጠለፋ ጉዳይ በቂ ሽፋን መስጠት አቃጣቸው?

~ ፕሬዝዳንቷን ጨምሮ የመንግስቱ ካቢኔ እኩሌታው በሴት ሹማምንት ሲሞላ የሴቶች ጸሃይ በኢትዮጵያ እየወጣች ነውን ብለን ደስ እንዳላለን ዛሬ ሴት ተማሪዎች ነፍሰ በላ በሆኑ ታጣቂዎች ታፍነው ሲወሰዱ አንዳቸውም ሴት ሹማምንት ዝምታን መምረጣቸው ምነዋ? በተለይም ለሴቶች መብት መከበር በመታገል የሚታወቁት እና ዝናን ያተረፉት የአሁኗ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዴንት ወ/ሮ #መዓዛ_አሸናፊ ምን ለጎማቸው?

~ እርዕስ እና ጉዳይ እየመረጡ በሶሻል ሚዲያ ጭምር ብቅ እያሉ ተቆርቋሪነታቸውን የሚገልጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ #ብርሃኑ_ጸጋዮ እና #የኦሮሚያ_ክልል_ባለሥልጣናት ከወዴት ገቡ?

~ ድርጊቱ የተፈጸመበት #የኦሮሚያ_ክልል ለዚህን ጊዜ ያህል ዝምታን ለምን መረጠ? አሁንስ ባለሥልጣናቱ ለምንት እርስ በርስ የሚጋጭ መረጃ ለሕዝብ ይሰጣሉ?

~ ከታፈኑት ልጆች መካከል ማምለጥ የቻለችው ልጅ አፋኞቹ ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ ገልጻለች። ይኸውም ተማሪዎቹ የሚለቀቁት አማራ ክልል የሚገኙት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በሙሉ ወደ ክልላቸው ሲመለሱ ነው የሚል እንደሆነ ገልጻለች።

ጉዳዩ ይህ ከሆነ በቅርቡ በ #OMN ሚዲያ ላይ አቶ #በቀለ_ገርባ ከአንድ ሌላ ብሔረተኛ ጋር ቀርበው በአማራ ክልል ጥቃት ስለሚደርስባቸ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎ ጉዳይ አምርረው ከገለጹ በኋላ ለመንግስት ጥብቅ እና የመጨረሻ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ማሳሰቢያቸውም ቃል በቃ እንደሰማሁት በአፋጣኝ የኦሮሞ ተማሪዎች ከአማራ ክልል ካሉ ዩንቨርሲቲዎች ለቀው ይውጡ የሚል እና ይህም በአፋጣኝ ካልተከወነ ለሚደርሰው ችግር መንግስት ኃላፊነቱን ይወስዳል ሲሉ ዝተዋል። የአቶ በቀለ ገርባ ማሳሰቢያ እና #የኦነግ_ሽኔ የአፈና ምክንያት እንዲህ ሲገጣጠም ጉዳዩ የተነካካ ፖለቲካዊ ምክንያት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ ስህተት ይሆናል ወይ?

~ ለአንድ ግለሰብ ወታደር መድቦ እና በጀት በጅቶ ጥበቃ የሚያደርግ መንግስት የድሃ ልጆች ከየዩንቨርሲቲው አስከሬናቸው ሲመለስ እና እንዲ ታፍነው ሲሰወሩ ጥበቃው ይቅር እና ስለሁኔታው ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ፤ በተለም ለታፋኝ እና ለጥቃት ሰለባ ቤተሰቦች መግለጽ ሲሳነው ማየት አገሪቱ የገባችበትን አዘቅት አያመላክትም?

~ ማነው ለእኔስ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠኝ?

መንግስት በታፈኑት ተማሪዎች ዙሪያ አሁንም ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ያድርግ፣ ተለቀዋል የተባሉት ልጆችም እውነት ከሆነ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እና የስነ አዕምሮ ባለሙያ ድጋፍ ይደረግላቸው።

ጠቅላዩም ዝምታዎትን ይስበሩ!

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top