Connect with us

መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባስቸኳይ ይወጣ! – የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

የታገቱት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በፍጥነት ከእገታ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባስቸኳይ ይወጣ!
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባስቸኳይ ይወጣ! – የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

የታገቱት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በፍጥነት ከእገታ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባስቸኳይ ይወጣ!

ጥር 2 ቀን 2012 ዓ·ም

የ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) በመላው ሀገራችን በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚነሱ ግጭቶች እና በተማሪዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን እየገለፀ ግጭት እና ጥቃቶቹን በጽኑ ያወግዛል፡፡ እስካሁን በደረሱ ግጭቶች ሕይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ቤተሰቦች መጽናናትን፣ በግጭቱ ምክንያት የተለያየ ጉዳት ለደረሰባቸው ተማሪዎች ብርታትን ይመኛል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ በተደጋጋሚ ችግር እየተከሰተ የትምህርት ሂደቱ በተደጋጋሚ ሲቋረጥ እና በተማሪዎች ሕይወት ላይ አደጋ ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ ተማሪዎች ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው አዳዲስ እውቀት እና ክህሎት አግኝተው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውም ብሎም የሀገርን ችግር ፈተው በበጎ መለወጥ የሚችሉበት ሂደት መሆኑ ቀርቶ እርስ በርስ በሚፈጠር ግጭት ሕይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅበት እና ለጥቃት የሚዳረጉበት መድረክ ሆኗል፡፡ ይህ ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ ሊመጣ አልቻለም፡፡

ይህ አልበቃ ብሎ፣ ለትምህርት ከቤታቸው የወጡ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደቤተሰባቸው በመመለስ ላይ ያሉ ተማሪዎች የጥቃት ሰለባ እንደሆኑ ከሰሞኑ ሰምተናል፡፡ ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደቤተሰባቸው በመመለስ ላይ ያሉ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ላይ እገታ እንደተፈጸመባቸው እና ያሉበት ሁኔታ በእርግጥ እንደማይታወቅ ለመረዳት ችለናል፡፡ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ደኅንነት ደግሞ ከምንም በላይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የታገቱት ተማሪዎችን ሁኔታ ዝርዝር መረጃ የሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ እና የመንግሥት የደኅንነት ተቋማት በአፋጣኝ ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቁ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ ተማሪዎቹን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በፍጥነት ከእገታ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የደኅንነት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲው፣ በአካባቢው የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ርብርብ እንዲያደርግ ኢዜማ ይጠይቃል፡፡

ከምንም ነገር በላይ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተማሪዎች በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እውቀት የማግኘት ዓላማቸውን አሳክተው እንዲጨርሱ የማስቻል ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ በየጊዜው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት በተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል እና ለማስቀረት ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት ኢዜማ ያምናል፡፡

በዚህ መሠረት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን፣ አስተማሪዎችን፣ የዩኒቨርሲቲዎቹ የአስተዳደር ሠራተኞችን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚገኙበት አካባቢ ማኅበረሰብን ያሳተፈ አጠቃላይ ንቅናቄ በመፍጠር፣ ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደኅንነት እና ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በጋራ ዘብ እንዲቆሙ አፋጣኝ ሥራ እንዲጀመር እንጠይቃለን፡፡

የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top