ከምረቃ ዜና ወደ ዩኒቨርሲቲ ዘግተናል መርዶ
ከወንድሙ ዱላ ሲተርፍ መኪና የሚፈጀው ትውልድ | ከሰለምን ሃይሉ
ፓለቲካችን የስግብግብ ስለሆነ ለራሳችን ልጆች አናስብም። የትም ዓለም ትግሉም ዘመቻውም መካረሩም ለትውልድ ነው። የእኛው በትውልድ ይቆምራል። ዩኒቨርሲቲዎች የፓለቲካ ሜዳ ሲሆኑ የደሃ ልጅ ይሞት ጀመር። ለውጡ ሰላም እንዳያገኝ ኩርፊያን መግለጫው መንገድ የደሃውን ልጅ መቅጠፍ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ውህደት እውን ሲሆን ከማየት የአንድ ፍሬ ልጆችን ህልም ማጨናገፍ የሚመርጥ ቆሻሻ ፓለቲካ ውስጥ ገባን። ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ በስውር የተሰራው ስራ በአደባባይ ሬሳ ለቃሚ አደረገን። ፎቅ ይሰራል ካልነው ትውልድ ከፎቅ ሰው መወርወርን የመሰለ የሳጥናኤል ድርጊት አየን።
ሰሞኑን ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከአቅም በላይ ሆኖበት ለጊዜው ትምህርት ማቋረጡን ወስኖ ዘጋ። ማስተማር መቻል ቀላሉ ተግባር ነበር ጤና ባጣ ፓለቲካ ማስተማር ሰው መቅበር ስለሆነ የዩኒቨርስቲውን ውሳኔ አደንቃለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ሲዘጋ ተማሪው ዶርምተሪና መማሪያ ክፍል ብቻ አይዘጋም። ዩኒቨርሲቲው ያለበት ከተማ አብሮ ይከረቸማል። ብዙ የንግድ ስራዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠረውን ተማሪ ተማምነው ተከፍተዋል። እቁብ የጀመረው የከተማዋ ነዋሪ ደንበኛው የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ነው። እንጀራ ዳቦ የፅሁፍ ቁሳቁሶች ብዙ ብዙ ነገር አቅራቢው ህይወቱ ይናጋል።
ዩኒቨርሲቲ እንዲዘጋ ስናደርግ የማናውቀው የመሰለንን ግን ደግሞ ወንድማችን የሆነውን መጤ የሚባል ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ማድረግ ብቻ አይደለም። ችግሩ የከተማን ጉሮሮ መዝጋት ነው። የሀገር ህልውና መናድ ነው። ስላልገባን በክፍ ተግባር ተሳትፈን ሰላምን ካቀለልነው ውሎ አድሮ እኛኑ ወደሚፈጀን መከራ ይወስደናል።
ወለጋም በተመሳሳይ እንደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር መቸገሩና ችግሩ አለመፈታቱ ተማሪዎችን ንብረት መልሳችሁ ወደየቤታችሁ ለማለት ተገዷል። የሰላም ጉዳይ ባለቤት የለውም ህዝባዊ ነው። ባልጠበቅነው ሰላም እንደ ሀገር መጎዳት ጀምረናል።
አንድ ሰሞን የምንሰማው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን ማስመረቅ ነበር። አንዱን ዩኒቨርሲቲ ተከትሎ ሌላውም ቁጥሩ እንዲህ የሚደርስ ተማሪ ሴት ወንድ እያለ ማስመረቁን ይነግረናል። ዛሬ አንዱ በሰላምና ፀጥታ ምክንያት ማስተማር አልቻልኩም ብሎ መዝጋቱን ሲነግረን ሌላው አካባቢ ከዚህ ተምሮ መንቃት ሳይሆን እርሱም የኔም ይዘጋልኝ ባይ መስሏል።
ስግብግብነት የተመረ ፓለቲካ ፈጥሮ በዩኒቨርሲቲ ተማሪ ህይወት ቁማር እምትጫወት ሀገር ባለቤት አድርጎን አላበቃም ዩኒቨርስቲው ሰላም መፍጠር ባለመቻሉ ወደየቤታችሁ ሂዱ ብሎ ህይወት ማትረፍን ዋጋ በመስጠት ያሰናበታቸው ተማሪዎች በሌላ ምክንያት ያልቃሉ።
ትዕግስትና ሥርዓት ጠፍቷል ከምሞት ብሎ በግማሽ አመቱ ከተዘጋ ዩኒቨርስቲ ወደቤትህ ሂድ የተባለ የዩኒቨርስቲ ተማሪ በመኪና አደጋ ያልቃል። የሁሉም ሞታችን ምክንያት ቆም ብሎ አለማሰብ ነው። ለራስ ህይወትና ለሀገር ነገ አለመጨነቅ ነው። እንዲህ ሆነን መድረሻችን የት ይሆን ብሎ የሚጠይቅ ጥቂት ነው። ሌላው በማያደርስ መንገድ አስቀሪ ድርጊቶች ውስጥ በንቃት ይሳተፋል። ውጤቱ ግን ሁላችንንም አክሳሪ ነው።