የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
***
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል በኢትዮጵያ ስም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት መመዝገቡን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
“አቀድም አእኵቶቶ ለእግዚአብሔር በእንተ እግዚእነ ኢየሱስ ክርሰቶስ እስመ ተሰምዐት ሃይማኖትክሙ ውስተ ኵሉ ምድር = ሃይማኖታችኹ በዓለም ዙርያ ኹሉ ተሰምታለችና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ማመስገንን አስቀድማለኹ፡፡”(ሮሜ ፩፥፩)
እጅግ የተወደዳችኹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ምእመናንና ምእመናት እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤
ሃይማኖታዊው፣ እጅግ ተወዳጁ እና ደማቁ የጥምቀት በዓላችን በዛሬው ዕለት የዓለም ቅርስ ኾኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ስለተመዘገበ እንኳን ደስ አላችኹ!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር እንደኾን ከምንታወቅባቸው ጉልሕ ማስረጃዎች አንዱ በየዓመቱ ጥር ዐሥራ አንድ ቀን በመላ ሀገሪቱ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በኅብረት፣ በአንድነት፣ በሰላም፣ በስምምነት እና በፍቅር ታቦቱን አጅቦ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እያመሰገነ በየወንዙ፣ በየዐደባባዩ እና በየመንገዱ በፍጹም ደስታ የሚያከብረው በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ነው፡፡
የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ዳግመኛ ተወልደው የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እና የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሚኾኑበት፣ የዘለዓለምን ሕይወትም የሚቀዳጁበት ምሥጢር ገሃድ የኾነበት ይህ በዓል፣ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቤተ ክርስቲያናችንና መንግሥታችን እንደዚሁም መላው ሕዝባችን በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሊቃውንት እና ዓበይተ ሀገር ምሁራን በአጠቃላይ ምእመናንና ምእመናት የማያቋርጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ በመኾኑም፣ ይህ የዘመናት ጥረታቸው በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ እውን ኾኖ ስለተመዘገበ ለደስታችን ወሰን የለውም፡፡
የተከበራችኹና የተወደዳችኹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን፤
ይህ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው ታሪካዊ ጉዳይ፣ የቤተ ክርስቲያናችን፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ላይ ደምቆ እና ጐልቶ እንዲታወቅ የሚያደርግ እንደዚሁም ሀገራችን በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትኾን ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡
ይህም እውን ሊሆን የሚችለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሪቱ ባህልና የቱሪዝም ተቋም እንደዚሁም በየሀገሩ የሚገኙ የቤተ ክርሰቲያናችን መሪዎችና አምባሳደሮች፣ ስለ በዓሉ ታላቅነት፣ ተወዳጅነትና ዕሴት ያለማቋረጥ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠሩ እንደኾነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡
በመኾኑም፣ የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገብ ለዚህ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ ተልእኮ ዕውቅና በመስጠት ረገድ የላቀ ሚና ስላለው ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ሥነ በዓሉን በማስተዋወቅ ሁሉም የበኵሉን እንዲወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን ማስተላለፍ እንወዳለን፡፡
በአበው ብሂል፣ “በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት” እንደሚባለው፣ ይህ ሳምንት ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝተው የተሸለሙበት ይልቁንም፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ የዓለም የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀዳጅተው ወደ መንበረ መንግሥታቸው በገቡበት ቀን የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ ይፋ መኾኑ ልዩ ክሥተት ያደርገዋል፡፡
የተከበራችኹና የተወደዳችኹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤
በዛሬው ዕለት በከፍተኛው የዓለም ድርጅት ዕውቅና አግኝቶ የተመዘገበው የጥምቀተ ክርስቶስ በዓላችን፣ እናንተው የአባቶቻችኹን እምነት እና ባህል፣ ሥርዐት እና ታሪክ ጠብቃችኹ በየዓመቱ በምታከብሩት ውብና ሳቢ፣ ማራኪ እና ተወዳጅ የአከባበር ሥርዐት የተገኘ መኾኑን ተገንዝባችኹ በቀጣይነትም ከነበረው ምንም ሳይጓደል በየዓመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡
ከዚህም ጋራ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በመንግሥታችን፣ በሕዝበ ክርስቲያኑና በመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ያላሰለሰ ድጋፍና ጥረት የቀረበለትን ሕጋዊ ጥያቄ በአዎንታ በመቀበል በዓለ ጥምቅተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ስም በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ ውሳኔውን ያሳለፈ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ጉባኤን ከልብ እናመሰግናለን፡፡
በመጨረሻም፤
በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ፍጹም የኾነ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመከባበር በዓል ኾኖ ሕዝባችንን አንድ አድርጎና አስተሳስሮ የቆየ የአንድነታችን ማሕተም ስለኾነ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ዕሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥብቅ አደራችንን በአጽንዖት እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.
(ምንጭ ሐራ ተዋህዶ)