የኢሚግሬሽን፣ የዜግነትና የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ የመልካም አስተዳደር ዕቅድ አውጥቶ በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲተገበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡
ኤጀንሲ በፓስፖርት አቅርቦት ዕጥረት እየተስተዋለ ያለበትን የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊት ለመታገል የመልካም አስተዳደር ዕቅድ አውጥቶ በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲተገብር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኤጀንሲውን የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በገመገመበት ወቅት አሳሰበ፡፡
ኤጀንሲው በበቂ መጠን ፓስፖርት ባለማሳተሙ በተፈጠረበት የፓስፖርት ዕጥረት አስቸኳይ ጉዳዮችን ከማስተናገድ ባለፈ አብዛኛው የአገልግሎቱ ጠያቂ የህብረተሰብ ክፍሎች በወረፋ በመመዝገብ በረጅም ቀጠሮ እንዲስተናገዱ እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሙጂብ ጀማል ያስረዳሉ፡፡
ለአስቸኳይ አገልግሎት መስፈርት የማያሟሉ ተገልጋዮች በአቋራጭ አገልግሎቱን ለማግኘት በኤጀንሲው አካባቢ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲከሰት ማድረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙ ሲሆን በተቋሙ እጅ ይገኝ ከነበረው 200,000 ፓስፖርት ላይ ተጨማሪ 1 ሚሊዮን እንዲታተም ከፈረንሳዩ ኦቨር ቱር ካምፓኒ ጋር ውል ተገብቶ 100,000 መረከባቸውን አብራርተዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ቀሪውን 900,000 እንደሚረከቡም የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ሌላ 1 ሚሊዮን ፓስፖርት እንደሚታተምም በማስረዳት ለተፈጠረው ችግር በቂ ፓስፖርት ማቅረብ መፍትሔ እንደሚሆን ነው አቶ ሙጂብ ጀማል ያስረዱት፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ፓስፖርት አገር ውስጥ ለምን እንደማይታተም፡ የፈረንሳይ ካምፓኒ ስራውን በብቸኝነት ለምን እንደያዘና ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ እንግልቶችን አስመልክቶ በርካታ ጥያቄዎችን ለኤጀንሲው አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በአገር ውስጥ ፓስፖርት ለማሳተም ማተሚያ ቤቶች የቴክኖሎጂና የዕውቀት ክፍተት ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር አዋጪም ባለመሆኑ በውጭ ካምፓኒዎች የህትመት አገልግሎቱ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
የፓስፖርት ህትመት የንግድ ስራ በመሆኑ የአውሮፓ ካምፓኒዎችም ስራውን በሞኖፖሊ ይዘው ስለሚሰሩና የፈረንሳዩ ካምፓኒም አሁን በስራ ላይ ያለውን ፓስፖርት ዲዛይን ሰርቶ የፈጠራ መብቱን በእጁ በመያዙ ህትመቱ በካምፓኒው ለረጅም ጊዜ ሲከናወን መቆየቱን አቶ ሙጂብ አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተፈጠረ ያለውን ረጅም ሰልፍ ለማስቀረት በአዲስ አበባ አራቱ መውጫ በሮችና በክልሎች 12 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በመክፈት ለችግሩ መፍትሔ እንደሚበጅም አቶ ሙጂብ አመልክተዋል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም ሆነ በፓስፖርት አቅርቦት ዕጥረት በተቋሙ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ድርጊቶች እየተከሰቱ በመሆናቸው የችግሮቹ መንስኤዎች ተለይተው የመልካም አስተዳደር ዕቅድ ወጥቶ በጥብቅ ዲስፕሊን እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡
(ምንጭ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት)