“ዲ`ፋክቶ መንግስት” – የህወሓት ህልም?
(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
ለዓመታት ሲነገረን የነበረው “የኢህአዴግ ውህደት” ዘንድሮ ቁርጥ ሆኗል፡፡ ነገሩ የምር መሆኑ እየገፋ ሲመጣ ደግሞ የኢህአዴግ የውስጥ ትግል ድርጅቱን ማዋሃድ ብቻ ሳይሆን እንዲፍረከረክም እያደረገው መሆኑ ተስተውሏል፡፡ በውህደቱ ዙሪያ ሰሞኑን ከሰማናቸው ጆሮ ጠገብ ወሬዎች ውስጥ የህወሓት (ትህነግ) ማፈንገጥ በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከኢህአዴግ መስራቾች አንዷና ዋነኛዋ የሆነቺው ህወሓት ከማንገራገር በዘለለ ማፈግፈግ መጀመሯና “ዲ’ፋክቶ መንግስት አቋቁማለሁ” ማለቷ ግርምትን ብቻ ሳይሆን በአንዳንዶች ዘንድ ከመርግ የከበደ፣ ከመርዶ ያልተናነሰ ድንጋጤ ፈጥሯል፡፡
ህወሓት ውህደቱን የፈራቺበት ምክንያት ቀደም ሲል ለእርሷ እንዲመች ተደርጎ የተዋቀረው ኢህአዴግ ፈርሶ ሁሉም ባለው ቁመና ልክ እንደሚወከል ስለምታውቅ ነው፡፡ ቀደም ሲል ኢህአዴግ በነበረው ድርጅታዊ አወካከል አራቱም ድርጅቶች እኩል ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ 5 ሚሊዮን ህዝብ የምታስተዳድረውን ህወሓትንና 40 ሚሊዮን ገደማ የሚያስተዳድረውን ኦህዴድን እኩል የሚያደርግ የተዛባ አወካከል እንደነበር ይታወቃል፡፡
ይህ ሁኔታ በአዲሱ ውህድ ፓርቲ እንደማይቀጥል ሲገባት ህወሓት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ጀመረች፡፡ አንዴ “ውህዱ ፓርቲ ፌዴራል ስርዓቱን አፍርሶ አሓዳዊ የመንግስት ስርዓትን ለማምጣት ነው” የሚል ወከባ ትፈጥራለች፡፡ በዚህ ወከባ “አጋር” ይባሉ የነበሩትን ፓርቲዎች ለማምታታት ብትሞክርም ለ29 ዓመታት ከሀገሪቱ ፖለቲካ የተገለሉት አጋሮች ግን “አንሰማሽም” የሚል ምላሽ በመስጠት የአዲሱ ውሁድ ፓርቲ አባልነታቸውን በየፓቲያቸው ጉባዔ አካሂደው በመወሰን በአቋማቸው ጸኑ፡፡ ቀጥላ “ሀገር ማዳን” በሚል ሰበብ መሰሎቿን ሰብስባ “የፌዴሬሽን ኃይሎች” የሚል ጎራ ለመፍጠር ብዙ ጥረት አደረገች፡፡ ይሄም ብዙ ርቀት ሊያስኬዳት እንዳልቻለ ስትገነዘብ 40 ገጽ ያለው ጽሁፍ አዘጋጀችና “ዲ’ፋክቶ መንግስት አቋቁማለሁ” የሚል እንቅስቃሴ ጀመረች ሲባል ሰማን፡፡
እዚህ ላይ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ትርጉም በተመለከተ ዊኪፔዲያ እንዲህ ይላል “በህገ መንግስት ላይ ከተቀመጠው ድንጋጌ ውጪ በመፈንቅለ መንግስት፣ በአብዮት፣ በወረራ፣ አሊያም ህገ መንግስትን በመሰረዝና በማገድ ስልጣን መያዝ ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡
በሌላ ሰነድ ላይ ደግሞ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት በሕግ ዕውቅና ሳያገኙ ሕግን፣ መንግስታዊ ተግባራትንና በህግ የተቋቋሙ የመንግስት ተቋማትን በተጨባጭ ሥራ ላይ የማዋል ተግባርን ይገልፃል” የሚል ትርጉም እናገኛለን፡፡ ተመሳሳይነት ቢኖረውም አንድ ተጨማሪ ብያኔ ልጨምር፡፡ “ዲ’ፋክቶ መንግስት ማለት ስልጣንን በሕጋዊ መንገድ ከያዙ አካላት ላይ በመንጠቅ ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝና ህጋዊ መንግስት የሚሰራውን ስራ መስራት ማለት ነው” የሚልም ትርጉም በተለያዩ ሰነዶች ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
ወደ ህወሓት የ“ዲ’ፋክቶ መንግስት” ጉዳይ እንለፍ፡፡ በህወሓት እየተነሳ ያለው ሃሳብ “በሀገሪቱ ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በትግራይ ክልል ምርጫ እናካሂዳለን፣ ከዚያም ‘ዲ’ፋክቶ መንግስት’ እንመሰርታለን” የሚል እንደሆነ ከተለያዩ የክልሉ የፖለቲካ ልሂቃን ሲነገር ተሰምቷል፣ በማህበራዊ ሜዲያም ይኸው ሲናፈስ ታይቷል፡፡ ይህንን ሃሳብ በሁለት ከፍለን – 1ኛ፡- “በትግራይ ክልል ምርጫ ማካሄድን” እና 2ኛ፡- “ዲ’ፋክቶ መንግስት መመስረትን” ነጣጥሎ ማየት ይቻላል፡፡
አሁን ባለው የሀገራችን ህገ መንግስት መሰረት ልክ ፓስፖርት እንደ መስጠት፣ ገንዘብ እንደማተም፣ ከመንግስታት ጋር የውጭ ግንኙነት እንደ ማድረግ፣ የመከላከያ ሰራዊት እንደ ማቋቋም፣ ዓለም አቀፍ ንግድ እንደማካሄድ ወዘተ. ማንኛውንም ዓይነት “ምርጫ ማስፈጸም” የፌዴራል መንግስት ስራ ነው፡፡ እናም በትግራይ ክልል ምርጫ እናካሂዳለን ማለት ህጋዊ መሰረት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ክልሎች የፌዴራል መንግስትን ሥራ መስራት አይችሉም፤ ፌዴራል መንግስትም የክልሎችን ሥራ ቀምቶ መስራት አይችልም፡፡ በዚህም መሰረት ትግራይ በራሷ ምርጫ ማካሄድ አትችልም፡፡ ፌዴራል መንግስት ከተስማማና ምርጫ ቦርድ እሺ ካለ ግን በትግራይ እውቅና ያለው ምርጫ አካሂዶ አሸናፊው ፓርቲ ወይም ጥምር ፓርቲዎች የክልሉን መንግስት ማቆም እንዲችሉ የማድረግ መንገድን በስምምነት መፍጠር ይቻላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ልብ አድርጉ “ግምት አለኝ” ነው ያልኩት፡፡ ይህንንም ግምት ለማስቀመጥ የፈለግኩበት ምክንያት “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል” እንዲሉ ሁኔታው ቢያስጨንቀኝ አንዳች መላምት ለማመላከት በማሰብ ነው እንጂ ትክክለኛ መንገድ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡
ህወሓቶች “በትግራይ ዲ’ፋክቶ መንግስት እንመሰርታለን አሉ” የሚለውን ስሰማ በጭንቅላቴ ያቃጨለው “እነዚህ ሰዎች ከምራቸው ነው? ወይስ በዶ/ር ዓብይ በመንግስት ላይ ጫና ፈጥረው ለመደራደር? እንመስርትስ ቢሉ በየትኛው መንገድ ማሳካት ይችላሉ?” የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ህወሓቶች ህጋዊውን መንገድ ትተው በጉልበት “ዲ’ፋክቶ መንግስት” እንመሰርታለን ካሉ ግን በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ህዝብ፣ በመቀጠልም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ “ይህንን ማድረግ አትችሉም” ብሎ እንደሚከለክላቸው አምናለሁ፡፡
የህዝቡ ክልከላ ወዶና ፈቅዶ ባጸደቀው ህገ መንግስት ላይ በተጻፉት ድንጋጌዎች አማካይነት የሚንጸባረቅ ነው፡፡ ክልከላው የሚፈጸመው ደግሞ በሀገሪቱ መከላከያ ኃይል አማካይነት ነው፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ህዝብ በህገ መንግስቱ አማካይነት በሰጠው ስልጣን መሰረት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ይጠብቃል፣ ያስከብራል፡፡ እናም ህወሓት የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ ካላሰበች በስተቀር “ዲ’ፋክቶ መንግስት” የመመስረቱ ህልም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ ትክክለኛ መንገድም አይደለም፡፡
ህወሓት የምትፈልገው የትግራይን ክልል በመገንጠል “ሀገረ ትግራይን” መመስረት ከሆነ (እኔ ባላምንበትም) በሀገሪቱ ህገ መንግስት በአንቀጽ 39 ላይ በተቀመጠው የህግ አግባብ መሰረት መጠየቅ መብቷ ነው፡፡ ዱሮም ይህ አንቀጽ የተቀመጠው ለህወሓት “የክፉ ጊዜ” መሹለኪያ ተብሎ መሆኑን አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ግን ግን ባኮረፍን ቁጥር እንገንጠል የምንል ከሆነ ነገሩ ሁሉ የእቃቃ ጨዋታ እንጂ ሀገርና ህዝብ የመምራት ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የሚያዛልቅም፣ የሚያዋጣም፣ የሚጠቅምም ሆኖ አይታየኝም፡፡
እንደኔ እንደኔ ለትግራይም፣ ለኢትዮጵያም የሚበጀው መንገድ “ዲ`ፋክቶ ስቴት” ማቆም ሳይሆን ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም የተለያዩ ፖለቲካዊ መድረኮችን በመፍጠር አጀንዳ ቀርፆ መደራደር፣ መደራደር፣ መደራደር፣ … ብቻና ብቻ ነው፡፡ ባደጉትና በሰለጠኑት ሀገሮች ያሉ ፖለቲከኞች የሚያደርጉት ይህንን ነው፡፡
ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡