ደርግና የስድሳዎቼ ግድያ (በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)
እነሆ ሕዳር አስራ አራት ትናንት አለፈ፡፡ ዝምተኛው፣ ደም አፋሳሹ፣ ደም አፍሳሹ ሕዳር 14 በሰንበት ዋለ፡፡ የዛሬ 45 ዓመት ግን የዋለው ቅዳሜ ቀን ነበር፡፡ በዚያን ዕለት የአገር ባለውለታዎች፣ የአገር አውራዎች፣ የጦርሜዳ ጀግኖች፣ የዲፕሎማሲ ጠበብቶች፣ የፖለቲካ አዋቂዎች በመቶ አለቆችና በሻለቃ መንግሥቱ ትዕዛዝ የተገደሉበት ዕለት ነበር፡፡
ጊዜው አሰቃቂ ነበር፡፡ የደርግ ንዑስ ደርግ አባላትን በፎቁ ላይ የሰበሰቡት ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹የዚህን ሽማግሌ ንጉስ አመራሮች እንግደላቸው ወይስ እነሱን እየቀለብን እንኑር›› እያሌ አማካሩ፡፡ አሳዛኙና ልብ ሰባሪው ነገር እነዚህ ንዑስ የደርግ አባላትም ሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ የሕግ እውቀት ኖሯቸው ፍትሐዊ ዳኝነት አለመስጠታቸው ብቻ አይደለም፡፡ ጠብመንጃቸውን ተማምነው እንግደላቸው ወይስ ይቅርብ እያሉ የሚወስኑባቸው የአጼ ኃ/ሥላሴ ባለሥልጣናት ስብሰባው ከሚካሄድበት ፎቅ ምድርቤት ውስጥ ሆነው ውሳኔውን እያደመጡ ነበር፡፡
እጅ በማውጣት የሚወሰነው የሞት ፍርድ እየተከናወነ ነው፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ‹‹አክሊሉ ሃብተወልድ ይገደል የምትሉ›› ሲሉ ግርርር ብሎ ንዑስ ደርግ እጅ ያወጣል፡፡ ‹‹ጀኔራል ከበደ ይገደሉ የምትሉ›› ሲሉም እንዛው፡፡ አስገራሚው ነገር እነዚህ ንዑስ የደርግ አባላት አብዛኞቹ ባለሥልጣናቱ ምን ወንጀል እንደሰሩ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊትም የት እንደነበሩ ምን ሥራ እንደነበራቸው አለማወቃቸው ነው፡፡
የሆነው ሆኖ ግድያው ተከናወነ፡፡ ስድሳ ሚኒስትሮችና የጦር መሪዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ በአንድ ቀን፣ ተገድለው በአንድ ቦታ ተቀበሩ፡፡
በመግደል ሥልጣን የጀመረው የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ደርግ ሲገድልና ሲያስገድል ኖረ፡፡ ፍትሕ በጠብመንጃ እጅ ውስጥ ወደቀች፡፡ በተለይ ሕዳር 14-1967 ዓ.ም የተከናወነውን ግድያ ታሪክ በጥቁር መዝገብ ዘግቦታል፡፡
አብዛኞቹ የደርግ ባለሥልጣናትም ይፀፀቱበታል፡፡ ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ እኛና አብዮቱ በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ከሁሉም የሚፀጽተኝ ነገር የአጼ ሃይለሥላሴን ባለሥልጣናት (60ዎቹን) መግደላችን ነው›› ብለው ይገልጹታል፡፡ የኮሎኔል መንግሥቱ ምክትል የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ ደግሞ ልብ በሚነካ አገላለጽ ይፀፀታሉ፡፡
‹‹‘ኢትዮጵያ ትቅደም! ያለምንም ደም!’ ብለን በተነሣን ማግሥት… እነዚያ ለሀገራቸው የለፉትንና የደከሙትን አዛውንቶች መጦር ስንችል ገደልናቸው›› ይላሉ፡፡
ይህንን ግድያ የማይፀፀትበት ብቸኛ ሰው መንግሥቱ ኃይለማርያም ብቻ ነው፡፡ ‹‹የ60ዎቹ ግድያ የተፈጸመው በንዑስ ደርግ ግፊት ነው›› በማለት ነበር ትክክለኛ ግድያ መከናወኑን በመጽሐፋቸው የገለፁት፡፡
ከተገደሉት ከፍተኛ የአገር ባለውለታዎች መካከል፣ ዲፕሎማቱና ፖለቲከኛው አክሊሉ ሃብተወልድ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደሚገደሉ ሲያውቁ እንዲህ አሉ፡፡
“እኛን በመግደል ኢትዮጵያን ከድህነቷ የምታወጧት ከሆነ ድርጊታቹሁን እንደ ታላቅ በረከት በፀጋ እንቀበላለን”
ይህ ከሆነ እነሆ 45 ዓመታት ሄዱ!
የእነዚህ ሰዎች ገዳዮችና በቀጥታ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የጨፈጨፉት መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን በዚምቧብዌ በምቾት ይኖራሉ፡፡