Connect with us

ስለሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ትዝብት

ስለሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ትዝብት
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ስለሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ትዝብት

በደቡብ ቴሌቪዥን የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት የአንድ ወገንን የምርጫ ምልክትን መሠረት አድርጎ ሲሰጥ እንደነበር ታዝበናል፡፡

በሕግ የተቀመጠው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ሊኖር የሚገባው የመራጮች ብዛት1500 ሲሆን በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ከእጥፍ በላይ የሚሆኑ መራጮች ተመዝግበው ተገኝተዋል፡፡

በአብዛኛው (82%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የአንድ ወገን ሃሳብን የሚያራመዱ ተወካዮች ብቻ መገኘታቸውን፤ በጣም ጥቂት በሆኑ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችም የሀገር ሽማግሌዎችም በታዛቢነት መገኘታቸውን መታዝብ ተችሏል፡፡

በዚህ የህዝበ ውሳኔ ሂደት ድምፅ አሰጣጥ ምሥጢራዊነት ያልተጠበቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ታይተዋል፤ ይህም መራጮች ከአንድ በላይ እየሆኑ የምሥጢር የድምፅ መስጫ ድንኳኖች ውስጥ በመግባት ምልክት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፤

(ሙሉ መግለጫው እነሆ)

ሕዳር 10 ቀን 2012 ዓም የተካሔደውን የሲዳማ ህዘብ ወሳኔ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ የተሰጠ መግለጫ

ሕዳር 12 ቀን 2012 ዓም

1. መግቢያ
በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲሁም መጭውን የ2012 ዓም አገራዊ ምርጫ ለመደገፍ፣ ለወደፊትም በምርጫ ጉዳይ የተቀናጀ እና ዘለቄታዊነት ያለው ተሳትፎ የሚያደርግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያቀፈ ጥምረትን የማቋቋም አስፈላጊነት የተገነዘቡ ከ60 በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበራት በግንቦት ወር 2011 ዓም “የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ” የተሰኘውን ህብረት እንዲያደራጁ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ፎረምን፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕን፣የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበርን፣ የክርስቲያን የበጐ አድራጐት እና ልማት ማህበርን፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅትን፣ የኢትዮጵያ ሲቪክ ኢንድ ቮተርስ ኢዱኬሽን አክተርስን እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ኔትዎርክን በአባልነት ያቀፈ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም ኮሚቴው እንቅስቃሴውን በማድረግ ላይ ይገኛል።

በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ በመተዳደሪያ ደንቡ ከዘረዘራቸው ዓላማዎቹ መካከል በምርጫ ሂደት የመራጮችን ተሳትፎ ለማድረግ፣ የሲቪክ እና የምርጫ ትምህርት ማካሄድ፣ አባላቱ በሁሉም የምርጫ ሂደቶች እና በህዝበ ውሳኔዎች የክትትል እና የትዝብት ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የማንቀሳቀስ እና የመደገፍ፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ ማደራጀት፣ መሰነድ እና ማጋራት እንዲሁም ማዘጋጀት እና ማሰራጨት ጥቂቶቹ ናቸው።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ከግንቦት 2011 ዓም ጀምሮ ካከናወናቸው ዋናዋና ተግባራት መካከል

– የጥምረቱን የመመስረቻ እና የመተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅቷል፤
– ከ2012 እሰከ 2014 ዓም የሚመራበትን የምርጫ ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅቷል፤
– ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ቁጥራቸው ወደ 100 ለሚጠጉና ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እንዲሁም

ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ለተውጣጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች በአመራር በምርጫና በግጭት አፈታት ዙርያ ስልጠናዎችን ሰጥቷል፤በተጨማሪም በየአሰልጣኞች ስልጠን ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለምርጫ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥምረቱን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ለማስመዝገብ እንዲሁም ለ2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግ ጐን ለጐን ህዳር 10 ቀን 2012 ዓም ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ከዲሞክራታየዜሽን እና ከሰባዊ መብት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን በማንቀሳቀስ በህዝበ ውሳኔው ላይ በታዛቢነት ተሳትፏል፡፡
ጥምረቱ በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ለመሳተፍ እንዲወስን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ህዝበ ውሳኔዎችን መታዘብ ጥምረቱ ከተቋቋመባቸው ዓላማወች ዉስጥ አንዱ ስለሆነ ነዉ፡፡

የጥምረቱ አስተባባሪ ኮሚቴ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ለመታዘብ የቅድመ ህዝበ ውሳኔ ትዝብት (pre-referendum Observation) ላይ ለሚሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አባላት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያዎች አማካኝነት ሥልጠና በመስጠት ከህዳር 4 ጀምሮ 16 ታዛቢዎችን ያሰማራ ሲሆን ህዳር 7 እና 8 2012 ዓ.ም ለተንቀሳቃሽ እና ተቀማጭ ታዛቢዎች በሐዋሳ ከተማ በሳውዝ ስታር ሆቴል ስልጠና በመስጠት በ24 ወረዳዎች በሚገኙ 162 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በተዘዋዋሪ ታዛቢዎች፣ 39 ምርጫ ጣቢዎችን በቋሚነት በድምሩ 201 ጣቢያዎች ላይ ጥምረቱ ታዛቢዎችን በማሰማራት የህዝበ ውሳኔውን መታዘብ ችሏል፡፡ ጥምረቱ ከተዘዋዋሪ እና ተቀማጭ ታዛቢዎች በተጨማሪ መቀመጫውን በሓዋሳ ከተማ ያደረገ 16 አባላት ያሉት Election Situation Room በማቋቋም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን የመከታተል እና የማስተባበር ስራ አከናውኗል፡፡
ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት የሚሸፍነው ጥምረቱ ታዛቢወችን ባሰማራባቸው የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ብቻ ነው፡፡

2. ጥምረቱ መረጃ ለማሰባሰብ የተገለገለባቸው ዘዴዎች

የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔን ለመታዘብ የተገለገለባቸውን ዘዴዎችና ናሙና አሰባሰብ መንገዶችን በተመለከተም ጥምረቱ የረዥም ጊዜ ታዛቢዎች (Long Term Observers) እና የአጭር ጊዜ ታዛቢዎች (Short Term Observers) አሰማርቷል፡፡ ዘዴው የረዥም ጊዜ ትዝብት (Pre Referendum Observation) ፤ውሳኔ ህዝብ የተሰጠበት ቀን፤(ballot day) እና ድኅረ ውሳኔ ሕዝበ ትዝብትን (Post Referendum Observation) ያጠቃልላል፡፡ የሕዝበ ውሳኔው በሚሰጥበት ዕለትም ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች (Mobile Observers) እና ተቀማጭ ታዛቢዎችን በማሰማራት መረጃ አሰባስቧል፡፡

2.1. የረዥም ጊዜ ትዝብት

ጥምረቱ 16 የረዥም ጊዜ ታዛቢዎችን በማሠማራት በ- 6 -ወረዳዎች በሚገኙ 147- የምርጫ ጣቢያዎች ቅድመ ሕዝበ ውሳኔ የመታዘብ ሥራ አከናውኗል፡፡ የረዥም ጊዜ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ የብዙኃን መገናኛ ከሕዝበ ውሳኔው ጋር በተያያዘ ያሠራጯቸውን ዘገባዎችንም ተከታትለዋል፡፡ የረጅም ጊዜ ትዝብት ዘዴን በመገልገል የፖሊቲካው ዐውዱ ምን እነደሚመስል እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔ ዝግጅትን ከምርጫ ቦርድ ፤ከዞኑ አስተዳደር፤እና ከጸጥታ አካላት ዝግጅት አንጻር ታዝቧል፡፡

2.2. የአጭር ጊዜ ትዝብትን በተመለከተ፡-
ጥምረቱ ኅዳር 10 ቀን 2012ዓ.ም ተዘዋዋሪና ቋሚ/ ተቀማጭ ታዛቢዎችን በማሠማራት ሕዝበ ውሳኔውን የመታዘብ ሥራ አከናውኗል፡፡ በ24 ወረዳዎች ሁለት፤ ሁለት አባላት ያላቸው የተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ቡድኖችን በማሠማራት 162 የምርጫ ጣቢያዎችን ሸፍኗል፡፡

በሐያ አራቱም ወረዳዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ቢያንስ አንድ ቋሚና አንድ ተንቀሳቃሽ ታዛቢ ቡድን በመመደብ በየወረዳው የሚገኙ በአማካይ ከአምስት እስከ ሰባት የሚደርሱ የምርጫ ጣቢያዎችን ለመታዘብ ነበር የታቀደው፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በጠቅላላው በ201 የምርጫ ጣቢያዎች ቋሚና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎችን በመመደብ ተልዕኮውን ፈጽሟል፡፡

3. ቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ትዝብት

ጥምረቱ ከኅዳር 4-9/2012 ዓ.ም በተመረጡ ስድስት ወረዳዎች (ወንዶ ገነት፣ ሸበዲኖ፣ ሐዋሳ፣ ዳሌ (ይርጋ ዓለም)፣ አለታ ወንዶ (ጩኮ) ዳሌ ሚንሽ) የረዥም ጊዜ ታዛቢዎች ቡድን 15 አባላት ያሉት 6 ቡድኖችን በማሠማራት አጠቃላይ የፖሊቲካ ዐውድ፣ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ካደረገው ዝግጅት እንዲሁም ከዞኑ አስተዳደር አሰተዳራዊ ድጋፍ ዝግጅት እና የጸጥታ ዝግጅት አንጻር ትዝብት አካሂዷል፡፡

4.1. የፖሊቲካው ዐውድ

ታዛቢ ቡድኑ ትዝብቱን ማካሄድ ከጀመረበት ከኅዳር 04 ቀን 2012 ጀምሮ እስከ ድምፅ ቆጠራና ውጤት ማሳወቅ ድረስ ፖሊቲካዊ ዐውዱ የተረጋጋና ሰላማዊ እንደነበር ታዝቧል፡፡

3.2. የሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት

ሀ. ከምርጫ ቦርድ ዝግጅት አንጻር
ቡድኑ በ 6 ወረዳዎች የሚገኙ 147 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የነበረውን ዝግጅት ታዝቧል፡፡ በዚህም መስረት የሚከተለውን መረጃ አግኝቷል፡-

– በሕግ የተቀመጠው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ሊኖር የሚገባው የመራጮች ብዛት1500 ሲሆን በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ከእጥፍ በላይ የሚሆኑ መራጮች ተመዝግበው ተገኝተዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ጥምረቱ ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ ጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ በማሳወቅ መፍትሔ እንዲፈለግ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

– ለመራጮች በማያመቹ ሥፍራዎች፤ መንገድ የሌለባቸው፣ በዛፍ ጥላ ሥር፣ የተከፈቱ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን ታዝቧል፡፡
– የሕዝብ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን በተመለከተ ሥልጠናና ግንዛቤ የተሰጣቸው ቢሆንም ከአበል ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው

መሆኑንና በተሠማሩባቸው አካባቢዎች በሚገኝ ኅብረተሰብ ላይ በምግብና በመጠለያ እንዲደገፉ መገደዳቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡

– ከሎጂስቲክ አንጻር በአንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የኮሮጆና የመራጮች የምርጫ ካርድ እጥረት ይታይ የነበረ ሲሆን በምዝገባ ሂደትም ሆነ በሕዝበ ውሳኔው ዕለት የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት እንዳይፈጠር ምርጫ ቦርድ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ጥምረቱ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ለ. ከዞኑ አስተዳደር አንጻር
የዞኑ አስተዳደር ከምርጫ ቦርድ ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን አስተዳደራዊ ድጋፍ በመስጠት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም ተገቢውን የጸጥታ ኃይል በማሰማራት የህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም የተሳካ እንዲሆን ጥረት ማድረጉን ታዝበናል፡፡ ሆኖም በታዘብናቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የአስተዳደርና የፖሊስ አካላት
በምዝገባ ወቅት ከተፈቀደላቸው የስራ ድርሻ ውጪ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራት ሲፈጽሙ ተስተውሏል፡፡

ሐ. የጸጥታ አካላት
የጸጥታ አካላት ሕዝበ ውሳኔው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ታዝበናል፡፡

መ. የመራጮችና የሲቪክ ትምህርት ዝግጅት
የመራጮችና የሲቪክ ትምህርት ዝግጅትን በተመለከተ በቂ ዝግጅት አለመደረጉንና ትምህርቱም ለኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ አለመሰጠቱን ታዝበናል፡፡ በደቡብ ቴሌቪዥን የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት የአንድ ወገንን የምርጫ ምልክትን መሠረት አድርጎ ሲሰጥ እንደነበር ታዝበናል፡፡ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት በሲዳምኛ ቋንቋ ባለመሰጠቱ ትምህርቱ ለመራጩ ሕዝብ በበቂ ሁኔታ አለመድረሱን መታዘብ ተችሏል፡፡

ሠ. የሕዝበ ውሳኔ ቅስቀሳ
የታዛቢ ቡድኑ የመታዘብ ሥራውን ባከናወነባቸው ቀናት የአንድ ወገን ያመዘነበት የምርጫ አጀንዳ የሚያንጸባርቁ ማስታወቂያዎች ተለጥፎ ከማየት በስተቀር በተፎካካሪ ወገኖች መካከል የተጋጋለ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የአዳራሽ ክርክርም ሆነ በሰላማዊ ሰልፍ አሊያም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሐሳብ ልውውጥ አለመደረጉን ታዝቧል፡፡

ረ. የድኅረ ሕዝበ ውሳኔ ትዝብት
ቡድኑ የድኅረ ውሳኔ ትዝብት በሐዋሳ ከተማና ዙሪያ አካሂዷል፡፡ በዚህም የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መለጠፍ መጀመራቸውን መመልከት ተቸሏል፡፡

4. የህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን

4.1.የህዝበ ውሳኔ ጣቢያ የሚከፈትበት ሰዓት አከባባር
ጥምረቱ ተዘዋዋሪ እና ቋሚ ታዛቢዎችን ባሰማራባቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አብዛኞቹ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎቸ የአትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አሰፈጻሚዎች መመሪያ 4.5.3 በሚያዘው መሰረት ከጠዋቱ 12 ሰአት ተከፍተዋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ሰዓት አስቀድመው የተከፈቱ የነበሩ ሲኖሩ፤ ዘግይተው የተከፈቱ ጥቂተ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ታዝቧል፡፡

4.2. የህዝበ ውሳኔ ጣቢያ አከፋፈት ሂደት/ ሥነ ስርዓት አከባበር
አብዛኛዎቹ (73.2%) የድምጽ መስጫ ጣብያዎች አከፋፈት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች መመሪያ 4.5.3 ላይ የተቀመጠውን ሂደት/ ሥነ ስርአት የተከተሉ መሆናቸውን መታዘባቸውን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከላይ የተጠቀሰው መመሪያ የተደነገገውን የህዝበ ውሳኔ ጣቢያ አከፋፈት ሂደት ስርዓቱን አለመከተላቸውን ታዝበናል፡፡፡

4.3. በድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን የሚያራምዱ ተወካዮች መገኘት
በአብዛኛው (82%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የአንድ ወገን ሃሳብን የሚያራመዱ ተወካዮች ብቻ መገኘታቸውን፤ በጣም ጥቂት በሆኑ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችም የሀገር ሽማግሌዎችም በታዛቢነት መገኘታቸውን መታዝብ ተችሏል፡፡

4.4. የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ ሂደት/ ሥነ-ሥርዓት አከባባር
አብዛኛዎቹ (81.4%) የምርጫ ጣብያዎች አከፋፈት ለምርጫ አከፋፈት የተቀመጠውን ስነ ስርአት የተከተሉ መሆናቸውን ነገር ግን አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አስቀድመው በመከፈታቸው
ስርአቱን ስለመከተላቸው መታዘብ አልተቻለም፡፡

4.5. የአስፈጻሚዎችን የሙያ ብቃት በተመለከተ፡-
አልፎ አልፎ በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠበቀባቸውን ብቃት ያላሳዩ አስፈጻሚዎች እንደነበሩ መታዘብ ቢቻልም
አብዛኛዎቹ (73.7%) የምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫውን የማስፈጸም ብቃት ማሳየታቸውን መታዘብ ተችሏል፡፡

4.6. የህዝበ ውሳኔው ድምፅ መስጫ ጣቢያ የሚዘጋበት ሥነ-ስርአት
የምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አሰፈጻሚወች መመሪያ 4.5.5 (ሀ) እና (ለ)የህዝበ ውሳኔው አስፈፃሚ ኃላፊ የድምፅ መስጫ ጣቢያ ህዳር 10 ቀን/2012 ዓ.ም ልክ ከከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ እንደሚዘጋ ይፋ እንዲያደርግ ግዴታ ከመጣሉም በላይ በህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለው የመጨረሻው ድምፅ ሰጪ ድምፅ እስኪሰጥ ድረስ የመጠበቅ ግዴታን ይጥልበታል፡፡ ጥምረቱ ትዝብቱን ባካሄደባቸው አብዛኞቹ (83.3%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ የተዘጉ ሲሆን፣ ጥቂቶቹ ግን ከ12፡00 ሰዓት በፊት አንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እኩለ ቀን ላይ፣ ከቀኑ 10 እና 11 ሰዓት ላይ መዘጋታቸውን፤ እንዲሁም በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች በድምፅ መስጫው መዝጊያ ላይ ጥቂት መራጮች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንደነበሩ መታዘብ ችለዋል፡፡

4.7. የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ቆጠራ

በአመዛኙ (85.2%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ድምጽ አሰጣጡ እንደተጠናቀቀ ቆጠራ ተጀምሯል፡፡ በብዙ ምርጫ ጣቢያዎች ቆጠራው እኩለ ቀን ላይ የተካሔደባቸው የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ የትዝብቱ ግኝቶች ያሳያሉ፡፡

5. በአጠቃላይ የህዝበ ወሳኔ ሂደቱ ላይ የተስተዋሉ ጠንካራ ጎኖች

– ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያለው መራጭ ወጥቶ ያለምንም የጸጥታ ችግር ህዝበ ውሳኔው በሰላም መጠናቀቁን መታዘብ ችለናል፡፡
– በቅድመ ህዝበ ውሳኔ ትዝብት የምርጫ አስፈጻሚዎች በተመደቡባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ችግር እንዳለባቸው የገለጹ ቢሆንም በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተሠማሩ አስፈጻሚዎች ሙያዊ ብቃት የነበራቸው መሆኑን ታዝበናል፡፡
– በዚህ የህዝበ ውሳኔ የትዝብት ሂደት ጥምረቱ ካሰማራቸው 147 ታዛቢዎች መካከል 38 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 5 አካል ጉዳተኞች በተዛቢነት መሰማራታቸውን በጥንካሬነት ታይቷል፡፡

– በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ለአረጋውያን፣ ህፃናትን ለያዙ መራጮች እና ለነፍሰ-ጡሮች ቅድሚያ ይሰጥ የነበረ መሆኑ፤
– በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መካከል ይታይ የነበረው መናበብና መተባበር ጠንካራ መሆኑ በጥንካሬነት የሚጠቅሱ ናቸው፡፡

የተስተዋሉ ክፍተቶች
– በዚህ የህዝበ ውሳኔ ሂደት ድምፅ አሰጣጥ ምሥጢራዊነት ያልተጠበቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ታይተዋል፤ ይህም መራጮች ከአንድ በላይ እየሆኑ የምሥጢር የድምፅ መስጫ ድንኳኖች ውስጥ በመግባት ምልክት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፤
– ጣት ላይ የሚቀባ ቀለም እጥረት የታየባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው፣
– ድምፅ ሰጥተው የጣት ቀለም ሳይቀቡ የወጡ መራጮች እንደነበሩ ታዝበናል፣
– በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ከቆጠራው መጠናቅቀ በኹላ በፍጥነት አለመለጠፋቸው፣
– በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት የአንድ ወገን ተወካዮች ብቻ መሆናቸው፣
– ለምርጫ ዕድሜአቸው ያልደረሱ የሚመስሉ ታዳጊዎች ድምፅ መስጠታቸውን ታዝበናል፡፡

6. ማጠቃለያ
ከዚህ በላይ የቀረበ ሪፖረት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት- ለምርጫ የሲዳማ ህዝብ ውሳኔ አካሔድን በሚመለከት ያዘጋጀው የመጀመሪያ ደርጃ ሪፖረት( preliminary report) ሲሆን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ዝርዝር መረጃወችን ያካተተ፤ ከዚህ ከተካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የተቀሰሙና ለመጭው የ2012 ዓ.ም አገራዊ ምርጫ ጠቃሚ ትምህርቶች ሊቀሰምባቸው የሚችሉ፤ የምርጫ አሰተዳደሩን ለማሻሻል የሚረዱ ተሞክሮዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን ያካተተ ሪፖርት በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያወጣል፡፡

ጥምረቱ ከሲዳማ ህዘብ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ እለተ እና ማግስት የታየው ሠላማዊ ሁናቴ የሚያስድስት እና የሚያበረታታ መሆኑን እየገለጸ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህ ሠላማዊ ሁኔታ በዘላቂነት እንዲቀጥል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲውጡ ጥሪውን ያቀረባል፡፡ በዚህም አጋጣሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እና በድምፅ መስጠት ሒደቱ ላይ የተሳተፉ አካላት ሁሉ እስካሁን ለነበረው አበረታች የምርጫ ሂደት ላሳዩት የአፈፃፀም ሰኬት አድናቆቱን ያቀርባል፡፡

ህዳር 12/2019 ሓዋሳ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top