የቅዳሜው የኢሕአዴግ ስብሰባ ለውሕደት ወይስ ለሌላ ውጥረት? | (በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)
በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ ገዥ ፓርቲ ሆኖ የተተራመሰ የፖለቲካ ድርጅት እንደ ኢሕአዴግ አላውቅም፡፡ በውህደት ምክንያት እየተናቆረ ነው፡፡ እንዲህ በሀሳብ መከራከራቸው ጥሩ ነው፡፡ ግን ሁለቱም ወገኖች (ውህደት ያስፈልጋልና ጊዜው አሁን አይደለም የሚሉት) አንድ ጠረጴዛ ላይ ውይይትና ክርክር ሲያደርጉ አይታይም፡፡
ይህንን ውይይት ለማድረግ የድርጅቱ ሊቃነመናብርት ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተገናኝተው ነበር፡፡የደረሱበትና የተወያዩት ነገር ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ ለመወያየት ዛሬ ረቡዕ ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም ምክንያቱ እስካሁን ባልታወቀ ሰበብ ወደ ቅዳሜ ተራዝሟል፡፡ ኢሕአዴጎች ተሸዋውደው ካልሸወዱን በስተቀር የቅዳሜው ስብሰባቸው አንድም የዕርቅ ወይም የፍቺ ነው የሚሆነው፡፡
በባለፈው ነሐሴ በአራተኛ አጀንዳ ይዘውት የነበረውን የኢሕአዴግ ውህደት ሳይነጋገሩበት በቅርቡ ተመልሰን እንመክራለን ብለው አልፈውት ነበር፡፡ አሁን በቅርቡ የተባለው ነገር ሳይደረግ አራተኛ ወር እየገባ ነው፡፡ ስላልተግባባ ወደ ስብሰባ መግባት ሳይችል ቀርቷል፡፡
በኢሕአዴግ ቤት ውስጥ ውህደትን በተመለከተ የተለያየ አቋም እንዳለ ግን መረዳት ከባድ አልሆነም፡፡ ኦዲፒ ለሁለት እንደተከፈለና ሰሞነኛው የአቶ አዲሱ አረጋ ከኃላፊነት መነሳትም የዚሁ ቀጣይ ክፍል መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አንደኛው ወገን (በሊቀመንበሩ የሚመራው) ውህደቱን በፍጥነት ለማከናወን እተሯሯጠ ነው፡፡ ሌላኛው ወገን ደግሞ (በምክትል ሊቀመንበሩ የሚመራው) ውህደቱን ለማዘግየት እየሠራ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡
ሕወሓት በይፋ ይህንን ውህደት ‹መንቦጫረቅ ነው› ብሎ በዚህ ወቅት እንዲህ ወዳለ ፖለቲካ እንደማይገባ በግልጽ አስረድቷል፡ የፖለቲካ አንድነት፣ የውሳኔ ሕብረትና የርዕዮተዓለም ተመሳስሎሽ በሌለበት ሁኔታ የሚደረግ ውህደት ‹መቦጫረቅ ነው› ሲል ኮንኖት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የደኢሕዴን ነገር እስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡ ስብሰባ አድርጎ ያሳለፈው ውሳኔ የለም፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ የሚገኙት የደኢሕዴን አመራሮች አንደኛውን የኦዴፓ ክንፍ (እንዋኸድ የሚለውን) ደግፈው በየሚዲያው ላይ መግለጫ እየሰጡ ነው፡፡ ይህ የድርጅታቸው አቋም ይሁን የግላቸው አመለካከት እስካሁን ግልጥ ያለ ነገር የለም፡፡
በይፋ የኢሕአዴግን ውህደት ደግፈው መቆሙ እስካሁን የተረጋገጠው የአማራ ክልሉ ገዥ ፓርቲ አዴፓ ነው፡፡ አዴፓ ምን ጥቅም እንደሚያገኝበት፣ የክልሉን ሕዝብ ውህደቱ እንዴት እንደሚጠቅመው ተንትኖ እስካሁን ባያቀርብም ውህደቱን ግን ተቀብሏል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ እንደ አዲስ የተወለደውን የአማራ ብሔርተኝነት ጉዳይ ወደጎን ብሎ ወደ ውህደት መግባቱ ትልቅ ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡
ለማንኛውም የዚህ ሁሉ አለመግባባት መጨረሻው ምን ይሆናል የሚለው በመጪው ቅዳሜ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በሠላም ለመፍታት ከተስማሙ ለአገርም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በተቀረ ተሸነጋግለው ሊሸነግሉን ቢወጡ ሌላ ውጥረት ነው፡፡