ተቀማጭነታቸው በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሆኑ አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ፣ አድማስ የአማራ ማህበራት ስብስብ የተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች እልቂት እንዲፈጠር የቆሰቀሰው ግለሰብ ለፍርድ ይቅረብ አሉ፡፡(ሙሉ መግለጫው ተያይዟል)
………
የህግ የበላይነት ሳይረጋገጥ አገርና ኢኮኖሚን መገንባት አይቻልም
ኖቬምበር 10 ቀን 2019 ዓ.ም.
አገራችን ኢትዮጵያ ለሃያ ሰባት አመታት በከፋፋይ የዘዉግ ፖለቲካ ስርአት ስትማቅቅ ቆይታ የዛሬ 19 ወራት አካባቢ የፖለቲካ ሽግግር እንደጀመረችና ይህም ሽግግር ለኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ ተስፋን እንዳስጨበጠ ይታወቃል። ይሁንና ከዚህ ተስፋ ጎን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩና የሽግግር ሂደቱን የተገዳደሩ ችግሮች ህዝቡን ስጋት ዉስጥ ሲከቱት መቆየታቸዉም እሙን ነዉ። በተለይ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የመጥፋቱ ጉዳይ ዋነኛዉ ተግዳሮት ሆኖ እስካዛሬ ዘልቋል። ይህ ተግዳሮት፣ የህዝቡን የእለት ተእለት ህይወት ከማስተጓጎል አልፎ፣ የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከፍተኛ የንብረት ዉድመት አስከትሏል፤ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ለአሰቃቂ ጉስቁልና ዳርጓል። ተሻለዉ ሲባል እያገረሸ፣ እዚህ በረደ ሲሉት እዚያ እየፈነዳ ያስቸገረዉ የሰላም መደፍረስ፣ ባሁኑ ሰአት፤ ከአንድ አመት ተኩል በፊት የፈነጠቀዉን ተስፋ አደብዝዞት ይገኛል።
የሰላም ችግር ፈጣሪዎቹ የታወቁ ናቸዉ። በአንድ በኩል ህወሃት ወያኔና በእሱ አገዛዝ ወቅት ልዩ ተጠቃሚዎች የነበሩ ሃይሎች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የለዉጡን አቅጣጫ እነሱ ብቻ በሚፈልጉት አቅጣጫ ለማስቀየስ፣ ያ ካልተቻለ ደግሞ ለማደናቀፍ የቆረጡ ሃይሎች ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ሃይሎች በተናጠልም ሆነ በተቀናጀ መንገድ ለሚያካሂዱት ሰላምን የማወክና ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ያላሰለሰ ተግባር፣ መንግስት የሚሰጠዉ የለዘበ ምላሽ የሚመጥንም የሚያስተምርም ባለመሆኑ እንዲያዉም እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ከጊዜ ወደጊዜ የልብ ልብ እያገኙ ለመሄዳቸዉ ሰሞኑን አገሪቱ ዉስጥ የተፈጠረዉ የሰላም ቀዉስ በቂ ማስረጃ ነዉ።
ሰሞኑን በአገራችን የተከሰተዉ፣ የ86 ወገኖቻችንን ህይወት የቀጠፈዉና፣ የብዙ ንብረት መዉደም ምክንያት የሆነዉ አመጽ የህዝብን ትእግስት አሟጦ፣ መንግስት የሚወስደዉን ቆራጥና አስተማሪ እርምጃ ብቻ የሚጠብቅ እንዲሆን አድርጎታል። ህወሃት ወያኔ በሃያ ሰባት አመታት አገዛዙ ወቅት የዘራዉ ከፋፋይ ዘር እስካሁን ለቀጠለዉ የሰላም መደፍረስና ተያያዥ ጥፋት ትልቅ ድርሻ እንዳለዉ የሚካድ ባይሆንም፣ ለዉጡ ከተጀመረ ከአንድ አመት ተኩል በኋላ እንደብቸኛ ተጠያቂ ምክንያት አድርጎ ማቅረቡ በአሁኑ ሰአት አሳማኝነቱ እየመነመነ ሄዷል። በሽግግርም ወቅት ቢሆን አስተማማኝ የሆነ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር የወቅቱ መንግስት ዋና ሃላፊነት ነዉ። መንግስት ህግና ስርአትን ለማስከበር ከሃይል እርምጃ በፊት የማስተማር፣ የማወያየትና የመመካከር ስራ ላይ ማተኮሩና መስራቱ አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለለየላቸዉ የሰላም አዋኪዎችና የጥፋት ሃይሎች በተደጋጋሚ የሚያሳየዉ ትእግስት በዉድ የዜጎች ህይወት እየተመነዘረ ከሆነ ለትእግስቱም ሆነ ለአመራሩ የሞራል ልዕልና ሊኖረዉ አይችልም።
ስለሆነም፣ ከጥቅምት 12 ሌሊት ጀምሮ ከሳምንት በላይ የቆየዉና ቢያንስ የ86 ኢትዮጵያዉያኖችን ህይወት የቀጠፈዉን አመጽ፣ መንግስት በተለመደዉ የለዘብተኛ አቋም ሊያልፈዉ አይገባም ብለን በጽኑ እናምናለን። መንግስት አመጹን የቀሰቀሱና የፈጸሙ ግለሰቦችንና ሃይሎችን በቁጥጥር ስር አዉሎ ለፍርድ ከማቅረብ የተለየ አማራጭ አለዉ ብለን አናምንም። ይህ አመጽ በይዘቱ የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ በእብሪትና በማንአለብኝነት ላይ የተመሰረተ፣ ተራ የዉንብድና ወንጀል ስለሆነ መንግስት በምክክርና በሽምግልና ጊዜ ማባከኑን ትቶ ለአመጸኞች ትምህርት ለህዝብ መረጋጋት ሊሰጥ የሚችል ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በአንክሮ እንጠይቃለን።
መንግስት የሚጠበቀዉን ህጋዊ እርምጃ ሳይወስድ ቢቀር፣ ዜጎች ፍትህን በእጃቸው ውስጥ ሊያስገቡ የሚገፋፉበት ሁኔታ ስለሚፈጥር፣ መጭው ጊዜ የበለጠ አስቸጋሪና አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል መንግስት ግንዛቤ ዉስጥ እንዲያስገባዉ እናሳስባለን። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአገር ዉስጥ ሰላም በአስቸኳይ ካልተረጋገጠ፣ ስርአት አልበኝነትን የሚጠቀሙ የዉጭ ኃይሎች መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኙ ያለንን ስጋት እናሳዉቃለን።
ባለፉት 19 ወራት መንግስት ለአገር አንድነት፣ ለመብት መከበር፤ ለነጻነት መስፈን ያሳየዉን ቀናኢነት እናደንቃለን። የአገሪቱን ፖለቲካና አስተዳደር ወደ ዲሞክራሲና የሰለጠነ አሰራር ለማሸጋገር፣ ኢኮኖሚዉን ወደ እድገት ሃዲድ ለመመለስ የወሰዳቸዉን እርምጃዎችና ያደረጋቸዉን ጥረቶችም ልብ እንላለን። ይሁንና መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር እነዚህ መልካም ጅማሮዎች ስር እንዲሰዱና እንዲያድጉ የሚያስችላቸዉን ሰላም ማምጣት ካልቻለ፣ ሁሉም መልካም ስራ በአሸዋ ላይ እንደተሰራ ቤት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ከዚህ አንጻር፦
1. የሰሞኑ እልቂቱ እንዲፈጠር አመጹን የቆሰቆሰዉ ግለሰብ ለረጅም ጊዜ በትእግስት የታለፈና ከተመሳሳይ ተግባር ለመታቀብ የማይችል መሆኑን ያረጋገጠ ስለሆነ በቁጥጥር ስር ዉሎ ለፍርድ እንዲቀርብ፤
2. ከግለሰቡ ጋር ለዚህ ወንጀል ጠንሳሽና አስፈጻሚ የሆኑ ግለሰቦች እንዲሁ በቁጥጥር ስር ዉለዉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፤
3. ሆን ብለዉም ይሁን ደንታ በማጣት ለሁከትና ለህዝብ የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የሚሆኑ ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች ላይ አስፈላጊዉ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
4. መንግስት የሰላም ችግሮች ከመፈጠራቸዉ አስቀድሞ የደህንነት ስጋት ያለባቸውን ቦታዎች በመለዬትና የጸጥታ ሃይሎችን በማሰማራት አመጸኞች ሊፈጥሩት የሚችሉትን ጥቃት ቀድሞ የማምከንና ህዝብን የማረጋጋትን ስራ እንዲሰራ፤
5. ኢትዮጵያዉያን በማንኛዉም የአገራቸዉ ምድር ተነቀሳቅሰዉ የመኖር፣ የመስራትና ንብረት የማፍራት መብታቸዉን የክልልና የፌዴራል መንግስቶች ከቃላት ባለፈ በተግባር እንዲያረጋግጡ፤
6. የህግ የበላይነት ከማስከበሩ ጎን ለጎን ከዚህ በፊት የነበሩት ስርአቶች በማህበረሰቡ መካከል ጥለውት ያለፉት ጥላቻ፣ መቃቃር፣ መከፋፈልና አለመተማመን ይለዝብና በጊዜ ሂደት ይሽር ዘንድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የሰላምና የእርቅ ጉባዔ በመላው ሀገሪቱ እንዲደረግ፤
7. ተገቢነት ያላቸው የህዝብ ጥያቄዎች የህግ አግባብን ተከትለው በሰላምና፣ በሰጥቶ መቀበል ድርድርና በአስቸኳይ የሚፈቱበት መደላድል እንዲፈጠር፤
8. በዚህ አጋጣሚ ሰፊው የአገራችን ህዝብ በማህበራዊ ሚዲያዎች በማር ቀብተው የሚቀርቡለትን የተጋነኑ ወሬዎች፣ ከፋፋይና እርስ በእርስ የሚያጋጩ የሃሰት ዜናዎችና ትርክቶችን እንደወረደ መቀበሉን ትቶ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ዜናዎችና ዘገባዎችን እንደ መረጃ ምንጭነት አንዲጠቀም፣ የዚህ ኣይነት ኣፍራሽ ተግባራትን የሚፈጽሙ ግለሶቦችና የዜና ተቋማትም ለፍትህ ኣካላት በማጋለጥ የራሱን አስተዋጽኦ አንዲያደርግ፤ እያሳሰብን፣
በመንግስት በኩል ለሚወሰዱ አስተማሪና ቆራጥ ህጋዊ እርምጃዎች ያለንን ሙሉ ድጋፍ ከወዲሁ እናሳዉቃለን። ይሁንና መንግስት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሀላፊነቱን ሳይወጣ ቀርቶ፣ ለብዙዎች መሞት፣ መጎዳትና መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠያቂ ሳይሆኑ ቢቀሩ፣ ከአገር ዉጭ የሚኖረዉም የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ በመንግስት ላይ ያለው እምነትና ተስፋ የበለጠ እንደሚመናመንና ለሞቱት፣ ለተጎዱትና ለተፈናቀሉት ወገኖቹ ያለውን አጋርነት ለማሳዬት ሲል ወደተለመደው የተቃውሞ ዘመቻ ውስጥ እንደሚገባ ያለንን ስጋት እናሳዉቃለን።
ኢትዮጵያ አገራችን በክብር ለዘላለም ትኑር!!
አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ፣ አድማስ የአማራ ማህበራት ስብስብ
Zemecha18@gmail.com / info@tibibir.org
202-627-0130 / 773-341-8511
አለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ቪዥን ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ አድቮኬሲ ኔትወርክ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ሲቪል ካውንስል
መግለጫ፤
1. አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት የሚገኙ እና በከተማ ደረጃ የተዋቀሩ ግብረሀይሎችን በአለምአቀፍ ደረጃ የሚያስተባብር የጋራ ስብስብ ነው።
2. የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ቁጥራቸው 27 የሚደርሱ በኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብትቶች መከበር ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ማህበረሰባዊ ድርጅቶችን ያካተተ የጋራ መድረክ ነው።