Connect with us

ባንኮችን ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተያዙ

ባንኮችን ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተያዙ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ባንኮችን ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተያዙ

የተሰረቁ ቼኮችን እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡  በወንጀል ፈፃሚዎቹ ሊወሰድ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል፡፡

ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እየተፈፀመ ስለ መሆኑ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ የምርመራና የክትትል ቡድን በማዋቀር ምርመራው እንደተጀመረ በኮሚሽኑ የከባድ ሌብነትና ዘረፋ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡

በወንጀሉ ተጠርጥረው የተያዙት ከ70 በላይ ግለሰቦች ከተለያዩ የግል ተቋማት ቼኮችን በመስረቅ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ የግል ባንክ ደንበኞች የባንክ ሂሳብ ውስጥ 60 ሚሊዮን 843 ሺ 601 ብር ወጪ አድርገው መውሰዳቸው በምርመራ ተረጋግጧል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ ወጪ ተደርጎ ሊወሰድ በሂደት ላይ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለና ከተጠርጣሪዎቹ እጅ የተለያዩ የባንክ ቼኮች እንዲሁም ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች እንደተያዙ የገለፁት ኢንስፔክተር ያሬድ በተጠርጣሪዎቹ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ የተገኘ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲታገድ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት ከኢትዮ ቴሌኮም ፣ ከባንኮች ፣ ከወረዳ አስተዳደር ፣ ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ፅ/ቤት እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት አንዳንድ ሰራተኞች ተባባሪ የሚሆኗቸውንና መረጃ የሚሰጧቸውን ሰራተኞች ለእኩይ ተግባራቸው በመመልመል ነው፡፡

ቼክ ተሰርቆባቸው 5 ሚሊዮን ብር ከባንክ ሂሳባቸው ወጪ የተደረገባቸው አቶ እያሱ ተቋመ እና በሀሰተኛ የውክልና ሰነድ 700 ሺ ብር የተወሰደባቸው ወ/ሮ ፍቅርተ ሀይሉ እና ባለቤታቸው አቶ ልዑል አዲሱ ስለ ተፈፀመባቸው ወንጀል በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
(ምንጭ :-አ/አ ፖሊስ ኮምሽን)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top