Connect with us

በኅዳሴ ጉዳይ የጋራ መግለጫ ወጣ

በኅዳሴ ጉዳይ የጋራ መግለጫ ወጣ
Photo: Whitehouse

ዜና

በኅዳሴ ጉዳይ የጋራ መግለጫ ወጣ

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፤

የግብፅ፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የዩናይትድ ስቴትስና የዓለም ባንክ የጋራ መግለጫ

የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም ልዑኮቻቸው ከዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትርና ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ጥቅምት 26/2012 ዓ.ም. ተገናኝተዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ አሞላል እና ማንቀሳቀስ (ኦፕሬሽን) ላይ አጠቃላይ፣ የትብብር፣ የተቀናጀ፣ ዘላቂና ሁሉም ተጠቃሚ ለሚሆኑበት ስምምነት እንዲሁም ይህንን ፅኑ አቋማቸውን በ2008 ዓ.ም. የመርኆች መግለጫ መሠረት ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ግልፅ ሂደት ለመፍጠር ቁርጠኛነታቸውን ሚኒስትሮቹ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በውኃ ሚኒስትሮቻቸው ደረጃ የሚካሄዱ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማድረግ የደረሱበትን ስምምነት አስታውሰዋል። የዓለም ባንክና ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንዲሰጡና በየስብሰባዎቹ ላይም በታዛቢነት እንዲገኙ ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል። ሚኒስትሮቹ በተጨማሪም ስምምነቱን እስከ ጥር 6/2012 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ለመሥራት፣ እንዲሁም ኅዳር 28/2012 ዓ.ም. እና ጥር 4/2012 ዓ.ም. ሂደቱን ለመገምገምና ለመደገፍ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ በሚደረጉ ሁለት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ተስማምተዋል። እስከ ጥር 6/2012 ዓ.ም. ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ የ2008 ዓ.ምቱ የመርኆች መግለጫ አንቀፅ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ስምምነታቸውን ሲያጠናቅቁ ለግብፅ፣ ለኢትዮጵያና ለሱዳን ሕዝቦች የአባይን የጎላ የልማት ትርጉም፣ የወሰን ተሻጋሪ ትብብርን አስፈላጊነት እና ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን የጋራ ፍላጎት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

________________________________________________

ማስታወሻ

1. በዚህ ትርጉም ውስጥ ቀኖች ወይም ዓመቶች የተጠቀሱት በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ነው።

2. የ2008 ዓ.ምቱ የመርኆች መግለጫ አንቀፅ 10 ትርጉም እንደሚከተለው ይነበባል፤

“10. አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት መርኅ፤

ሦስቱም ሀገሮች በመርኆች መግለጫው አተረጓጎም ወይም አተገባበር ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመልካም መንፈስ መርኅ ላይ ተመሥርተው በውይይቶች ወይም በድርድሮች ለመፍታት ቁርጠኛ ናቸው። ወገኖቹ አለመግባባቶቹን በውይይት ወይም በድርድር ለመፍታት ሳይቻላቸው ቢቀር ግልግል ወይም አሸማጋይ ሊጠይቁ ወይም ለርዕሳነ ብሄሮቻቸው ወይም ለጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸው ሊያሳውቁ ይችላሉ።”

3. ከላይ የተቀመጡት ትርጉሞች ሁሉ የቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት የአማርኛ ክፍል ግርድፍ ትርጉሞች ናቸው። ለትክክለኛ መረጃ ማስረጃነት ካልሆነ በቀር በህጋዊ ሰነድነት ሊቀርቡ አይችሉም።

VOA Amharic 

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top