የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አንጋፋና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በባህር ዳር ምክክር አደረጉ፡፡
አንደኛው አማራ ኪነ ጥበብ ጉባኤ ለበርካታ አንጋፋዎች እውቅና ሰጥቷል፡፡
****
የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች በባህር ዳር ከተማ ውይይት አካሄዱ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጥቅምት 22 እስከ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው አንደኛው የአማራ ኪነ ጥበብ ኩነት ከአራት መቶ ያላነሱ ወጣትና አንጋፋ የኪነ ጥበብና የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ታድመዋል፡፡
በአማራ ክልላዊ መንግስትና በኮኮብ ማስታወቂያ ትብብር በጥረት ድጋፍ የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አዳራሽ ሙሉ ቀን ሲመክር ውሏል፡፡ ውይይቱ ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ የነበረ ሲሆን ከመረጃ ምንጮቻንን ባገኘነው መረጃ መሰረት ባለሙያዎች የአማራ አንድነት ተጠብቆ እንደ ቀድሞ በሀገር ህልውና ላይ ያለውን ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ሰፊ ምክክሮች የተደረጉበት ነው፡፡
በምሁራን የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት በተደረገበት በዚህ ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና የጸጥታና ደህንነት ሰላም ቢሮው ሃላፊው አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የታደሙበት ነው፡፡
እሁድ ጥቅምት 23 ቀን ባለሙያዎቹ በአማራ ክልል የሚሰሩ የኢንዱስትሪ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኘተዋል፡፡ ምሽት በዩኒሰን ሆቴል በተካሄደው ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ለበርካታ አመታት ከአማራ ህዝብ አብራክ ወጥተው ለሀገር ኩራትና ጌጥ ለሆኑ አንጋፋ ባለሙያዎች ስለአበረከቱት ሀገራዊ ቱሩፋት እውቅና ተችሯቸዋል፡፡
በእውቅና አሰጣጡ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት፣ የሙዚቃ ባለሙያው ሙላቱ አስታጥቄ፣ ሰዓሊ ዘሪሁን የትምጌታ፣ ድምጻዊ አለማየሁ እሸቴ፣ ሃያሲው አስፋው ዳምጤ፣ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፣ ደራሲ የዱር ፍሬ ይፍሩና ፕሮፌሰር አዱኛ ተሸልመዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በሙያቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና የተቸራቸው ደግሞ አርቲስት ችሮታው ከልካይ፣ አርቲስት ስዩም ተፈራ፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ ደራሲ አንዳርጌ መስፍን፣ ተዋናይ ተክሌ ደስታ፣ አርቲስት ጌትነት እንየው፣ ደራሲ ጌታቸው በለጠን ጨምሮ በርካታ ለሀገር ብዙ የሰሩ ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዕለቱ ለመምህር ታዬ ቦጋለ ሽልማት የተበረከተ ሲሆን መምህር ታዬ ቦጋለም ለታዳሚው አማራ ሜዳ ላይ መቆም የለበትም ኢትዮጵያን ለማዳንም ሆነ ራሱን ለመከላከል መደራጀት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዝግጅቱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ባለሙያዎቹ ለክልሉ ህዝብና ለሀገር የሚሰሩትን ስራ አጠናክረው የሚያስቀጥሉበት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ፎቶውን ያገኘነው ከአማራ ብዙኃን የፌስቡክ ገፅ ነው።